በኒውጀርሲ ሰማይ ላይ የታዩት ምስጢራዊ ድሮኖች የኢራን እንዳልሆኑ ተገለጸ

ፔንታጐን በአሜሪካዋ ኒውጀርሲ ግዛት አካባቢ የታዩት ድሮኖች ከኢራን የጦር መርከብ የተነሱ እንዳልሆኑ አስታውቋል። በቅርብ ሳምንታት በኒውጀርሲ ሰማይ ላይ በርካታ ድሮኖች የታዩ ሲሆን አንዳንድ ድሮኖች ወታደራዊ ካምፖች እና የተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጎልፍ መጫወቻ አካባቢ ታይተዋል።

የአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑት ጄፍ ዳን ድሩ “ከፍተኛ አመኔታ ካላቸው” ምንጮቼ ሰማሁ ብለው ድሮኖቹ ከኢራን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረው ነበር። የኒው ጀርሲው ሪፐብሊካን ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ድሮኖች አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ከሚገኝ የኢራን የጦር አውሮፕላን የተነሱ ናቸው ብለዋል።

“መርከቧ የምትገኘው በዩናይትድ ስቴትስ ምሥራቃዊ ጠረፍ አካባቢ ነው። ወደ ምናየው እና የምንሰማው ነገር ሁሉ ድሮኖች ለቀዋል” ሲሉ የኮንግረስ አባሉ ባለፈው ረቡዕ ተናግረው እንደነበር ይታወሳል። “ከፍተኛ አመኔታ ካላቸው ምንጮቼ ያገኘሁት መረጃ ነው። በቀላሉ የምወስደው ጉዳይ አይደለም።” ነው ያሉት

እንዲሁም አሜሪካ ድሮኖቹ ተኩሳ እንድትጥላቸው ምክረ ሐሳብ ሰጥተዋል። ነገር ግን የፔንታጐን ምክትል ፕሬስ ሴክሬታሪ ሳብሪና ሲንግ የሰውየው አስተያየት ውሃ የሚያነሳ አይደለም ሲሉ አጣጥለውታል።

ሳብሪና በሰጡት መግለጫ “በዩናይትድ ስቴትስ ምሥራቃዊ ጠረፍ ምንም ዓይነት የኢራን የጦር መርከብ የለም። ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ድሮኖችን እየተኮሰ ያለ መርከብም የለም” ብለዋል።

በተጨማሪም ፔንታጐን በመጀመሪያ ዙር ምርመራ ድሮኖቹ “ከውጭ ሀገር አሊያም ከሌላ ቦታ የመጡ አለመሆናቸውን” ማወቅ ችሏል ይላሉ። ቫን ድሩ ከፔንታጐን ምላሽ በኋላ በቀጣዩ ቀን ፎክስ ኒውስ ላይ ድጋሚ ቀርበው “እውነታው እየተነገረን አይደለም” ብለዋል።

ፔንታጎን “የአሜሪካ ሕዝብ እንደ ሞኝ ነው የሚመለከተው” ሲሉ የመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ወርፈዋል። ሌላኛው የኒውጀርሲ ሴናተር ዲሞክራቱ ሪቻርድ ብሉሜንታል “አስፈላጊ ከሆነ” ድሮኖች ተመትተው ይጣሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ የሆኑት ጆን ኪርቢ “የተባሉት ድሮኖች ብሔራዊ አደጋ ስለመደቀናቸው ምንም ማስረጃ የለም” ሲሉ ከዋይት ሐውስ መግለጫ ሰጥተዋል። አያይዘውም አብዛኛዎቹ ድሮን እየተባሉ ሪፖርት የሚደረጉ በራሪዎች ሰዎች የሚያበሯቸው አነስተኛ አውሮፕላኖች ናቸው ብለዋል።

መብረር በማይፈቅድባቸው ቦታዎች እስካሁን ምንም የድሮን በረራዎች አልታዩም። ኪርቢ ጨምረው ኮንግረሱ የድሮን ቁጥጥርን በተመለከተ ጠበቅ ያለ ሕግ እንዲያወጣ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል በኒውዮርክ ከተማ ብሮንክስ በተባለው ሥፍራ በርካታ ድሮኖች ሐሙስ ዕለት ሲበሩ መታየታቸውን አንድ የፖሊስ መኮንን ተናግረዋል። በቅርቡ ዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል ጣቢያዎች አካባቢ ምንነታቸው ያልታወቁ ድሮኖች መታየታቸው አይዘነጋም።

ኤፍቢአይ ኒውጀርሲ አካባቢ ፒካቲኒ አርሰናል በተባለው ወታደራዊ የምርምር ጣቢያ እና ቤድሚኒስተር በተባለችው ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የትራምፕ ጎልፍ መጫወቻ አካባቢ የታዩትን ድሮኖች እየመረመረ እንደሆነ አስታውቋል። የዩኤስ ፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር ደግሞ በቤድሚኒስተር እና በፒካቲኒ አካባቢ ለጊዜው ድሮን ማብረር የሚከለከል እግድ አውጥቷል ሲል የዘገባው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You