ከአንድ ዓመት በፊት ልክ በዛሬው ዕለት 31ኛው የአዲስ አበባ ከንቲባ ይፋ ሆነ። ከንቲባው የኬሚካል መሀንዲሱ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ነበሩ። ሹመታቸው ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በደግም በመጥፎም ፣በስኬትም በነቀፌታም መነጋገሪያ ሆነዋል።
ከመሀንዲሱ መኖሪያ ቤት ኪራይ ጀምሮ ትላልቅ አገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ከንቲባውንና ካቢኔያቸውን አበጀህ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ለአዲስ አበባ ከንቲባ መሆን የለብዎትም እስከሚለው ትችቶችን አስተናግደዋል።
ሹመታቸውን የሚቃወሙ ወገኖች የከተማዋ ተወላጅ ስላልሆኑ ከተማዋን ለማስተዳደር የውክልና ጉድለት አለባቸው፣ ብሔር ዘመም አቋማቸው የበርካታ ብሔረሰቦች መናገሻ የሆነችው አዲስ አበባን ካለ አድልዎ ለመምራት ያላቸው አቋም አጠራጣሪ ነው፣የሚሉ አነጋገሮች በሹመታቸው ማግስት ተደምጠዋል።
በሌላ ወገን ሹመታቸውን የሚደግፉ ሰዎች ደግሞ የሥራ አፈጻጸም ችሎታቸው እንጂ ብሔራቸው ከጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም። ተሰናባቹ ከንቲባን ጨምሮ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች ለበርካታ ተከታታይ ዓመታት አዲስ አበባን አስተዳድረዋል። ኢንጂነር ታከለም ከዚህ የተለየ አይሆንም ሲሉ ጥብቅና ቆመውላቸዋል።
ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው “አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ፣ የሁላችንም ከተማ ናት ብዬ አምናለሁ። ከኢትዮጵያዊነት አልፎም የአፍሪካዊነት መገለጫ ናት፤ ምክንያቱም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫም ናትና። ይህ እምነቴ ዛሬ የመጣ ሳይሆን ከልጅነቴ ጀምሮ አብሮኝ ያደገ ነው” ሲሉ ለተቃዋሚዎቻቸው ሀሳብ እንዳይገባቸው በመናገር አተካሮ ሳያበዙ ወደ ቤት ስራቸው ገብተዋል።
መሀንዲሱ ከንቲባ ካቢኔያቸውን በአዳዲስና በወጣት አመራሮች ባወቀሩ ማግስት ለዓመታት ህገወጥ የሆኑ አሰራሮችን ወደ ማስተካከል ስራ ገብተዋል። የመጀመሪያ ስራቸው ከ6 እስከ 20 ዓመት በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ መሬቶችን ወደ መሬት ባንክ የማስመለስ ስራ አንዱ ነው። በመቀጠልም በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ የከተማ አስተዳደሩ ቤቶችን ከህገወጦቹ በመንጠቅ አቅም ሌላቸውና ለደሃ ነዋሪዎች የማስተላፍ ስራ ሰርተዋል።
ሌላው የከተማዋ አወዛጋቢ ጉዳይ የከተማዋ የገቢ አሰባሰብ ነው። የኢትዮጵያና የአፍሪካ ትልቁ የገበያ ሥፍራ መርካቶ ነው። ይሁን እንጂ ህገ ወጡና ህጋዊው የማይለይበት ሁኔታ ነበረ። አዲሱ ከንቲባና ካቢኔያቸው ይህን የማስተካከል ጥረት አድረገዋል። ይህን ከግንዛቤ በማስገባት ህገ ወጡን የማስተካከልና አላግባብ የተጣለውን ግብር የማንሳት ስራ ሰርተዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረውን አስተሳሰብ በመተው፣ በቴክኖሎጂና በአቅም ላይ ብቻ የተወሰነ የታክስ ማሻሻያ አድርገዋል። አስተዳደሩ በስድስት ወራት 20 ነጥብ7 ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ ዕቅድ አውጥቶ 18 ነጠብ 8 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል። ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር 3ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ብልጫ በማሳየት መሻሻልን አሳይቷል።
ሌላው የኢንጅነሩ ካቢኔ የቤት ስራ የስራ አጥ ወጣት ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ባይባልም ጅምር ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። የከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶች የ2 ቢሊዮን ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቦ ፈንዱን ተግባራዊ ለማድረግ በ100 ወረዳዎች የነዳጅ ማደያዎችን ገንብቶ ለተደራጁ ወጣቶች ማስተላለፍ፣ በ116 ወረዳዎች የተሰሩ የሸቀጣሸቀጥ ሱቆችን መገንባት፣ ያገለገሉ 300 የከተማ አውቶቡሶችን በመጠቀም ተንቀሳቃሽ የምግብ እና መጠጥ መሸጫ፣ በከተማዋና በዙሪያዋ ባሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሰሩ ማድረግና በሌሎች ዘርፎች ወጣቶችን የማሠማራት እቅድ ተይዞ ነበር።
የኢንጅነር ታከለ ኡማ በመልሶ ማልማት ፕሮግራም ከዚህ ቀደም ነዋሪዎችን አፈናቅሎና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን አናግቶ ይከናወን የነበረውን ግንባታ አካሄድም ቀይሯል። የትኛውም ግንባታ ሲካሄድ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎችን አካትቶ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ፣ በሚፈጠረው የሥራ ዕድልም ነዋሪዎች ተቋዳሽ መሆን እንዳለባቸው አቅጣጫ አስቀምጧል።
መልሶ የሚለማው ሕንፃ ብቻ ሳይሆን፣ ሰውም መሆን እንዳለበትም አቋም ይዟል። የአዲስ አበባ ከተማ አብዛኛውን ውኃ የሚያገኘው ከኦሮሚያ አጎራባች አካባቢዎች ነው። ከዚህ በኋላ አስተዳደሩ በኦሮሚያ አጎራባች ከተሞች ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እንደሚሰራም አመላክቷል።
ሌላው አዲሱ የታከለ ኡማ አስተዳደር የቢሮ ሀላፊዎችን ብቻ ሳይሆን ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ የተለያየ የአቅም ደረጃ ባላቸው አመራሮች ቀይሯል። መዋቅሩን ከማስተካከል ባለፈም የከተማ አስተዳደሩ፣ ተደራራቢ ሥራዎችን የሚያከናውኑ በርካታ መሥሪያ ቤቶች እንዲታጠፉ አድርጓል።
በከተማዋ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን ነዋሪዎች ለማቋቋም የጀመረውን ፕሮግራም፣ ቀደም ሲል ከያዘው 123 ሺህ በተጨማሪ 200 ሺህ ነዋሪዎችን ከተማ አስተዳደሩ አካትቷል። ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የማንሳትና መልሶ የማቋቋሙ ስራ ሰርተዋል። የማህበራዊ ትረስት ፈንድ አቋቁመው ስራ አስጀምረዋል። የጎዳና ተዳዳሪዎች እንዲያገግሙ የማድርግ ስራ ተጀምሯል።
ከዚህም በተጨማሪ በከተማዋ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ይፋ ተደርገዋል። የመጀመሪያው ፕሮጀክት 56 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውና 29 ቢሊዮን ብር የሚፈጀው የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው። በ50 ቢሊዮን ብር እና በ36 ሄክታር መሬት ላይ ለመገንባት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የአዲስ አበባ ለገሃር የተቀናጀ የመኖሪያ አገልግሎት ሌላው ትልቁ ፕሮጀክት ነው። በኢትዮጵያ መንግስት እና በዱባዩ ኤግል ሂልስ ትብብር ተግባራዊ ይሆናል። በእነዚህና ሌሎች በከተማ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ጅምር አዲሱ ካቢኒ የራሱን አስተዋጾ አድርጓል።
የከተማ አስተዳደሩ ሌላው የተከተለው አዲስ አሠራር በመኖሪያ ቤት አቅርቦት መስክ ነው። የተጀመሩ የ20/80 ፕሮግራም 95ሺ832 ቤቶች እና 38ሺ240 የ40/60 ቤቶችን በአፋጣኝ በማጠናቀቅ ለቆጣቢዎች ለማስተላለፍ አቅዶ ነበር። በከተማው ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ 51 ሺ229 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ አውጥቷል።
ይሁን እንጂ በርካታው የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ የወጣበት የኮዬ ፈጬ ሳይት የኦሮሚያን ድንበር ታልፎ የተገነባ ነው በሚል ውዝግብ ዕጣ የወጣበት ቤትን የማስተላለፉ ሂደት ቆሟል። ጉዳዩን የሚፈታ አጣሪ ኮሚቴ ቢቋቋምም ችግሩን እስካሁን አልፈታውም። በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ አላግባብ መታዋቂያ ሰጥተዋል ከሚለው ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተደማምሮ ኢንጅነር ታከለ ኡማን እና ካቢኔያቸውን ፈትኗል።
በኮዬ ፈጬ ጉዳይ ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ ወገኖች በሚነሱ ጥያቄዎችም ከንቲባውና ካቢኔያቸው ተፈትኗል። በቀጣይም የከተማውና የኦሮሚያ ክልል ጥያቄን አጣጥሞ መሄድም ትልቅ የቤት ስራው እንደሚሆን ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2011
አጎናፍር ገዛሀኝ