አዲስ አበባ፡- ‹‹ፍትሕ ሆይ ከወዴት አለሽ?›› በሚል ርዕስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም የተስተናገደው የጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያሳረፈው ውሳኔ ታግዶ እንዲቆይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አዘዘ።
አጣሪ ጉባዔው ለፌዴራል ፍርድ አፈፃፀም ዳይሬክቶሬት ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም በላከው ደብዳቤ ግልባጭ እንደተመለከትነው፤ ጉዳዩን አይቶ ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስ በፍርድ አፈፃፀም በኩል በፍ/ አ/መ/ቁ 32438 የተጀመረው አፈፃፀም ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የጌትእሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ድርጅት እህት ኩባንያ በሆነው በላቦራ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ የማኔጂንግ ዳይሬክተሩና የምክትል ዳይሬክተር ዋና አማካሪ ዶክተር አሰፋ አዳነ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ዶክተር በዕውቀቱ ታደሠና ባለቤታቸው ወይዘሮ መሠረት በረደድ ሕዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም በቢሾፍቱ ቀበሌ 01 የሚገኘውን ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ በ22 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግዢ ፈፅመው ፋብሪካው የነበረበትን ሰባት ሚሊየን ብር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዕዳን ጨምሮ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የተጠራቀሙ ውዝፍ የግብር ዕዳዎችን ወደራሳቸው አዙረው መክፈል ቢጀምሩም ሻጮች ግን ሊያሰሯቸው አልቻሉም።
እንደ ዶክተር አሰፋ ገለጻ፤ የግዢና ሽያጭ ውል ሲታሰር የፋብሪካውን ሙሉ በሙሉ ባለንብረትነት ለማስተላለፍ የሚያስችል ሆኖ ገዢዎች ለፋብሪካው ዕድሳት አድርገው ምርት ሲጀምሩ ሻጮች ውሉ እንዲፈርስላቸው ጠይቀዋል። በገዢና በሻጭ መካከል ተደርጎ የነበረው የንብረት ክርክርም በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ሲታይ ቆይቷል። በመጨረሻም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአንድ ዳኛ የሐሳብ ልዩነት በአብላጫ ድምጽ ውሳኔ ተሰጥቶታል።
ችሎቱ፤ ውሉ እንዲፀና ነገር ግን ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ያረፈበት 3 ሺህ 15 ሜትር ካሬ ይዞታ ለሻጮች እንዲመለስና በተያያዘ ባልተጠየቀ ዳኝነት 17 ሚሊየን 699 ሺህ 952 ብር ከነወለዱ ገዢዎች በአንድ ጊዜ እንዲከፍሉ የወሰነ ሲሆን፤ ይህም ሲሰላ 39 ሚሊየን ብር የሚደርስ ነው::
በአጠቃላይ ውሳኔው ገዢዎች ፋብሪካውን እንዲመልሱ፣ የሻጮችን የባንክ ዕዳ እንዲከፍሉ የሚያደርግና ባልተገባ መንገድም የሚያበለጽጋቸው ነው። በዚህ መልኩ ሀብትና ንብረታቸው ላይ ከተወሰነ በኋላ ደግሞ ችሎት ሳይደፍሩ ‹‹ችሎት በመድፈር›› ወንጀል ተከስሰው ባልና ሚስትን ጨምሮ ስድስት የቤተሰብ አባላት እስር ቅጣት እንደተወሰነባቸው ዶክተር አሰፋ ተናግረዋል።
ውሳኔው ከተወሰነ በኋላ ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም የፍርድ አፈፃፀም አካላት ለርክክብ ፋብሪካው ባረፈበት ቦታ ላይ ተገኝተው እንደነበረ ዶክተር አሰፋ ጠቅሰው፤ ፋብሪካውና ቦታው በአንድ ላይ በመሆኑ ምክንያት ርክክቡ ሊደረግ እንዳልቻለ፤ በድጋሚ ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ርክክብ ሊፈፅሙ ቢሞክሩም ልኬት ከተጀመረ በኋላ ፍርድ ላይ የተወሰነውና መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ልዩነት ስላለው ፍርድ አፈፃፀም ላይ የነበሩት አካላት ተቸግረው መመለሳቸውን አስረድተዋል።
ፍርድ አፈፃፀም የውሳኔውን ተግባራዊነት ሊያረጋግጥና ርክክብ ሊያደርግ በስፍራው ከመገኘቱ አስቀድሞ ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ውሳኔው እንዲታገድ አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን ዶክተር አሰፋ ገልፀው፤ በመጨረሻም ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም ውሳኔው እንደታገደ ፤ለዚህም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በጋዜጣው ላይ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰፊው በማስረጃ ተደግፎ የቀረበው ዘገባ የራሱ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ጉባዔው ለዳይሬክቶሬቱ በላከው ደብዳቤ አስፈላጊው ማጣራት እስኪደረግ ውሳኔው ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ በማስተላለፉ ሰነዶች ተመርምረው፣ ፋብሪካው ያረፈበት ቦታ ላይ በመገኘት፣ የአካባቢውን ሰዎች፣ ገዢና ሻጮችን በማነጋገር እንዲሁም ሌሎች ማስረጃዎችን በመመርመር ትክክለኛ ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ዶክተር አሰፋ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2011
ፍዮሪ ተወልደ