ከሦስት ወራት በፊት መጋቢት 20 ቀን 2011 ዓ.ም በታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ «ዓመታትን የዘለቀው የላስቲክ ቤት ነዋሪዎች እሮሮ» በሚል ርዕስ በሰንጋ ተራ 9 ዓመታትን በላስቲክ ቤት ውስጥ ያሳለፉ ሰዎችን ሕይወት የተመለከተ ዘገባ አቅርቦ ነበር። በወቅቱ አዲስ ዘመን ያናገራቸው የልደታ ክፍለ ከተማ አመራሮችም ችግሩን ለመፍታት እንደሚጥሩ ተናግረው ነበር። ክፍለ ከተማው ቃሉን ጠብቆ በላስቲክ ቤት ነዋሪ ከሆኑት መካከል ለ30 ዎቹ 10/90 ኮንዶሚንየም ቤት ሰጥቷል።
ከአንድ ወር በፊትም ለ35 የላስቲክ ቤት ነዋሪዎች የቀበሌ ቤቶችን ለመስጠት የዕጣ አወጣጥ ሥነሥርዓት ሲደረግ አዲስ ዘመን በቦታው ተገኝቶ ሁኔታውን ተከታትሏል።
አዲስ ዘመን በዚህ ሳያበቃ የቀበሌ ቤቶቹ በዕጣ የተሰጧቸው የላስቲክ ቤት ነዋሪዎች ያሉበት ድረስ በመሄድ እንዴት ዓይነት ቤቶች እንደተሰጧቸው ተመልክቷል። በዕጣ ቤት ተሰጣቸው የተባሉት ሰዎች ቤቶቹን ለማየት ቦታው ድረስ ሲሄዱ ፈጽሞ ያልጠበቁት ነገር እንደገጠማቸው ለአዲስ ዘመን ገልጸዋል።
በሰንጋ ተራ መልሶ ማልማት ቦታ ዘጠኝ ዓመታትን ላስቲክ ቤት ውስጥ የኖሩት የሁለት ልጆች እናት ወይዘሮ ጥሩነሽ ፍቃዱ ቤት ተብሎ የተሰጣቸው ጣሪያና ግድግዳ የሌለው ዘጠኝ ዓመት ፈርሶ የተቀመጠ ባዶ መሬት መሆኑን ይገልጻሉ። እርሱንም ከግራና ቀኝ ካሉት ነዋሪዎች አንደኛው ቦታውን አልፈው ሰርተውበታል የሚሉት ወይዘሮዋ የቀረው ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር እንኳን የሚሆን ቦታ አይደለም ብለዋል።
የተሰጣቸውን ባዶ መሬት እያሳዩ «ይህንን ባዶ መሬት ቤት ነው ብለህ አትኖርበትም። እንኳን የሰው ልጅ ውሻ እንኳን አይተኛበትም። ላስቲክ እንኳን ወጥሬ ልጆቼን ሰብስቤ እገባበታለሁ የምልበት ቦታ አይደለም።» ሲሉ ይገልጹታል።
ለክፍለ ከተማው ቅሬታ ሳቀርብ የክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ሲሳይ «ለእናንተ ጣሪያና ግድግዳ ያለው ቤት እንዴት ይሰጣችኋል? የላስቲክ ቤት ነዋሪዎች የድሃ ድሃ ተብላችሁ ነው ይህንም ታግለን የሰጠናችሁ በጣም ትቀልዳላችሁ።
የምትወስጂ ከሆነ ውሰጂ፤ ብትፈልጊ አትውሰጂ፤ አልፈልግም ብለሽ ፈርመሽ ውጪልኝ» ብለውኛል የሚሉት ወይዘሮ ጥሩነሽ ፍቃዱ እኔ ቤት የመገንባት አቅሙ ቢኖረኝ ኖሮ ሜዳ ላይ ከስምንት ዓመት በላይ እተኛለሁን? ሲሉ ይጠይቃሉ።
ዘጠኝ ዓመታትን በላስቲክ ቤት መጠለያ ውስጥ መኖራችንን በሚገባ በመግለጽ ለሚመለከተው አካል ለማድረስ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለሰራው ዘገባ እጅግ በጣም አድርጌ አመሰግናለሁ በማለት ሀሳባቸውን መግለጽ የጀመሩት አቶ ጌታቸው ከበደ፣ 20 እና 30 ሺ ብር አውጥተን ቤት መገንባት የምንችልበት አቅም ቢኖረን ኖሮ ዘጠኝ ዓመት ሙሉ ችግሮች ተጋፍጠን ሜዳ ላይ የምንኖርበት ምክንያት አይኖርም ነበር ብለዋል።
ቤቶቹ የፈራረሱና የሚጠገኑ መሆናቸውን አስቀድመው ነግረውናል፤ የሚሉት አቶ ጌታቸው ዕጣ ወጥቶ ሄደን ስናይ ያገኘነው ባዶ መሬት ነው። ሊያውም ሁለት በሁለት ሜትር ወይም ሁለት በሦስት የሆነ አልጋ እንኳን የማያዘረጋ ነው። በዚያ ላይ ከሽንት ቤት ጋር የተያያዘ ወይም ሽንት ቤት አቋርጦት የሚሄድና የሚፈልቅበት ስፍራ ሆኖ ነው ያገኘነው፤ እኛ በዚህ ደረጃ አልጠበቅንም ነበር ብለዋል።
አቶ ጌታቸው «የቤት ዕጣ የወጣልን ከአንድ ወር በፊት ቢሆንም አሁንም ጎርፉን ችለን ለዓመታት በኖርንበት ላስቲክ ቤት ውስጥ እየኖርን ነው። ከሰላሳ አምስቱ ሰዎች አራትና አምስት ሰዎች ናቸው ቤት የደረሳቸው። የአብዛኞቹን አይቻለሁኝ ወንዝ ዳር፣ ሜዳና ሽንት ቤት የሚፈስበት ኦና መሬት ነው የተሰጣቸው።
አሁን ደግሞ የላስቲክ ቤታችሁን አፍርሳችሁ የሰጠናችሁ ባዶ ቦታ ላይ ላስቲክ ወጥራችሁ ኑሩ ነው እየተባልን ያለነው» ሲሉ እየተደረገ ያለው ነገር እጅግ ግራ እንዳጋባቸውና እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
በመኪና አደጋ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ባለቤታቸው ጋር ለዓመታት ላስቲክ ቤት ውስጥ የኖሩት አቶ ተስፋዬ በቀለም ውሃ የሚያልፍበት ምንም ነገር የሌለው ባዶ መሬት ተሰጥቷቸዋል። ከተሰጠን ቦታ አሁን እየኖርን ያለንበት ላስቲክ ቤት ይሻላል የሚሉት አቶ በቀለ፣ የተሰጡን የቤት ቁጥር የሚጠቀስላቸው ነገር ግን ቤት የሌላቸው ባዶ መሬቶች ናቸው። እኛ ቤት የመስራት አቅም የለንም ብለዋል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ እንድሪስ በዕጣ አወጣጥ ሥነሥርዓቱ ወቅት ስለቤቶቹ ሁኔታ ሲናገሩ «ክፍለ ከተማው ላይ ያለውን ሙሉ አቅም አሟጠን ጥገና ሊደረግላቸው የሚገባ ሰላሳ አምስት የፈራረሱ ቤቶችን ሰጥተናቸዋል። ነዋሪዎቹን ፣ ወረዳውንና ሌሎች የልማት አካላቶችን አስተባብሮ አስፈላጊ የሆነውን ድጋፍ በማድረግ ጥገና ተደርጎላቸው ሊኖርባቸው የሚችሉ እንዲሆኑ ታስቦ የተደረገ ነው።» ብለው ነበር።
ለልደታ ክፍለ ከተማ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ለአቶ ብሩክ ከድር «የቤት ቁጥር ያለው ነገር ግን ባዶ መሬት በቀበሌ ቤት ስም መሰጠት ነበረበትን?» በሚል አዲስ ዘመን ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ «በእኛ ክፍለ ከተማ 19 ሺህ ገደማ የቀበሌ ቤቶች አሉ። እነዚህ ቤቶች ረጅም ዓመታት በመቆየታቸው ግማሾቹ ፈርሰዋል፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ለኑሮ አመቺ ባልሆነ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ናቸው።
የሰጠናቸው ቤቶች ይዞታቸው ቢፈርስም የቤት ቁጥር አላቸው፤ ሙሉ ለሙሉ ያልፈረሱም አሉ። እነዚህን ቤቶች እንደ አማራጭ ስንሰጣቸው እንደግፋችኋለን ብለን ነው። ለምሳሌ በክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ ሥራን በማስተባበር በጥገና ጭምር እገዛ እናደርጋለን ብለናል። ቤቶቹ በተለያየ ምክንያት የፈረሱ ቢሆኑም የቀበሌ ቤት መሆናቸውን የሚያሳይ የቤት ቁጥር አላቸው» ብለዋል።
«የምንቀበለው እውነታ ሰዎቹ መደገፍ አለባቸው። እኛ እንደ ክፍለ ከተማ በወጣቶች በጎ ፍቃድ እንቅስቃሴ ብዙ ቤቶች አስጠግነናል። ሙሉ ለሙሉ አቅም ለሌላቸውም የጉልበትና የቁሳቁስ ድጋፍ እናደርጋለን። ያለው የድህነት ደረጃ ጥልቅ ስለሆነ ፍላጎቱም ከፍተኛ ነው። ያን ተከትሎም ችግር አልፈታችሁልንም የሚለው ቅሬታ ሰፊ ነው።
በ2011 ዓ.ም ብቻ ከ155 ቤቶች በላይ ጠግነናል፤ በያዝነው ክረምትም መቶ ቤቶችን የመጠገን ዕቅድ ይዘናል። ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢ ነው። ጉዳያቸውን በልዩ ሁኔታ አይተን ምላሽ ለመስጠት ጥረት እናደርጋለን ብለዋል»።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2011
የትናየት ፈሩ