– እስካሁን ከ360 በላይ የኃይል መሙያ ማሽኖች ተተክለዋል
አዲስ አበባ፡- የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የኃይል መሙያ ማሽኖች (ቻርጅ ማድረጊያ ስቴሽኖች) እጥረት ለመፍታት እንደሀገር እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በሀገሪቱ ውስጥ ቁጥራቸው መበራከቱን ተከትሎ ጊዜያዊ ችግር ተብሎ የሚጠቀሰው አንደኛው የኃይል መሙያ ማሽኖች ችግር ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት እንደ መንግሥት የኤሌክትሪክ መኪና አስመጪዎችና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች የቻርጅ ማሽን እንዲተክሉ የሚገደዱበት አሰራር ተበጅቷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ360 በላይ ማሽኖች የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ስቴሽኖች መተከላቸውን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ቁጥሩን ከፍ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስርም ከ70 በላይ በሪልእስቴትና መሰል ህንጻዎች ስርና ሆቴሎች ውስጥ የኤሌክትሪክ መኪኖች የቻርጅ ማድረጊያ ፈጣን ማሽኖች እንዲተከሉ መደረጋቸውን አመላክተዋል፡፡
ከሪል እስቴት ጀምሮ እስከ መኪና ማቆሚያዎች ድረስ ፈጣን ቻርጅ ማድረጊያ ማሽኖች እንዲተክሉ እየተደረገ መሆኑን አቶ በርኦ ገልጸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚሰሩ በህንጻዎች ስር ፣ ሆቴሎች ውስጥ የቻርጅ ማሽኖች እንዲተከሉ በቁርጠኝነት እየተሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
ሀገርን ከማልማትና የተሻሉ አማራጮችን ከመፍጠር አንጻር ከአዲስ አበባ ባሻገርም በሌሎች ከተሞች የኮሪደር ልማቶች እየተከናወኑ መሆኑን የጠቆሙት አቶ በርኦ፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የቻርጅ ማድረጊያ ጥያቄም ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተሳስሮ የሚመለስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ወደ ክልል ከተሞች የኤሌክትሪክ መኪኖች ቻርጅ ማድረጊያ ማሽኖች በኮሪደር ልማቱ በማካተት እየተተከሉ እንደሆነና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለዚህ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ከመገጣጠም ባለፈ የቻርጅ ማድረጊያ ማሽኖች እየተተከሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ሀዋሳ ላይም እንዲሁ በመጠኑ ሥራው እየተከናወኑ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በክልሎች እየተበራከቱ ሲሄዱ የኮሪደር ልማቱ አካቷቸው የሚሰሩ መሰረታዊ ሥራዎች እንዳሉ የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ተሽከርካሪዎች በሚቆሙባቸው ቦታዎች ሁሉ ቻርጅ ማድረጊያ ማሽኖች እንዲተከሉ በአሰራር የተቀመጠ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እውን እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሁለተኛው የኮሪደር ልማት የኤሌክትሪክ መኪናዎች ኃይል መሙያ 54 ቻርጅ ማድረጊያ ስቴሽኖች እንደሚኖሩ የገለጹት አቶ በርኦ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የባትሪ ቻርጅ ፍላጎት ከአንድ ሺህ 100 በላይ መሆኑንና ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ 54 ስቴሽኖች እንደሚገነቡ ታስቦ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም