አዲስ አበባ፡- በሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ያለውን የጅግጅጋ ከተማ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክትን በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።
በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ ሻፊ አህመድ (ኢ/ር) ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ ሁለት አቅጣጫዎች በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱ 30 ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ ይገነባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የገለጹት ።
የኮሪደር ልማቱ የመንገድ መሰረተ-ልማት ፣ መብራት ፣ የቴሌኮም መስመሮች ፣ ፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች፣ የአዳዲስ ቤቶች ግንባታና እድሳት ፣ የመዝናኛ ስፍራዎች እንዲሁም የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ፣ የአረንጓዴ ልማትና ሌሎች ሥራዎችን የሚያካትት መሆኑን ከንቲባው ተናግረዋል።
በሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የሚተገበረው የጅግጅጋ ከተማ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ብዙ ወሳኝ የቴክኖሎጂ ልማቶችንም በውስጡ ያከተተ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባው፤ የፕሮጀክቱ ወጪ ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመዋል።
የልማት ሥራዎቹ በተቀመጠላቸው አቅጣጫና የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቁ የከተማዋን ገፅታና ውበት በማሻሻል በኩል የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እና የከተማዋን ኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን የሚያስችል ነው ብለዋል።
የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች የኮሪደር ልማቱ የሚያስገኛቸውን ጠቀሜታዎች በመገንዘብ ለልማቱ አስፈላጊውን ትብብር እያደረጉ እንደሚገኙ የተናገሩት ከንቲባው፤ በቀጣይም ህብረተሰቡ በልማቱ የፈረሱ አካባቢዎችን መልሶ በፍጥነት በማልማት ለኮሪደር ልማቱ ስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ የመገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም