ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ተፈናቅለው ወደ ቀያቸው የተመለሱ ዜጎችን ለማቋቋም የቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ክልሎች ሃላፊነታቸውን በተገቢው ሁኔታ መወጣት እንደሚገባቸው የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አስታወቁ።
በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አስመራ ጃራ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ከቤኒሻንጉል ጉምዝና ከኦሮሚያ ስድስት አጎራባች ወረዳዎች የተፈናቀሉ 157ሺ ዜጎች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ቤት የተቃጠለባቸው እንዲሰራላቸው ፤ መሬታቸውና ንብረታቸው የተወሰደባቸው እንዲመለስላቸውና የፌዴራል መንግስት የሚያቀረበው እርዳታ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እንዲቀርብ በሁለቱ ክልሎችና መንግስት መካከል ስምምንት ተደርጓል።
ምክትል አስተዳዳሪው የተገባው ቃል ሙሉ ለሙሉ ባለመፈጸሙ ተፈናቃዮች ወደ ኦሮሚያ ክልል አንገር ሸንኮራ አካባቢ ተመልሰው እየመጡና ድንበር አካባቢ እየቀረቡ መሆኑን፣ ተፈናቃዮቹ የተቃጠለባቸው ቤት እንዳልተሰራላቸው፣ እንዲሁም የተዘረፈባቸው ንብረትም እንዳልተመለሰላቸውና አልፎ አልፎ እርዳታ በወቅቱ እንደማይቀርብላቸው ተናግረዋል።
ለቅሬታ አቅራቢዎቹ ከመንግስት ጋር በመነጋገር ችግሩን እንደሚፈቱ በመግለጽ ለክልሉ መንግስት ደብዳቤ መጻፋቸውን ያነሱት ምክትል አስተዳዳሪው፤ የክልሉ መንግስት በሀላፊዎች ደረጃ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጋር ተወያይቶ ችግሩን በጋራ ለማስተካከል እንደሚሰራ እንደገለጸላቸው፤ ችግሩ በዞን አቅም የሚፈታ ባለመሆኑ ሁለቱ ክልሎችና የፌዴራል መንግስት በትኩረት መስራትና ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
‹‹ የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደረገው ስምምነት መሰረት የኦሮሚያ ክልል መንግስት የሁለቱን ክልል ወረዳዎች የሚያገናኝ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር መንገድ እየሰራ ነው። ሌሎች ወረዳዎችንም የሚያገናኝ መንግድ ለመስራት ጨረታ አውጥተናል። የሁለቱን ክልሎች ልማት ለማፋጠን በሁለቱም ክልሎች ጽፈት ቤት ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል። በጤና፣ በትምህርትና በልማት ሁለቱ ክልሎች በጋራ መስራት ስለሚገባቸው ጉዳዮችም የወለጋና አሶሳ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ጥናት እያደረጉ ነው››ሲሉም አስተዳዳሪው ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት ዞኑ ሙሉ ለሙሉ ሰላም ነው ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው፤ ህብረተሰቡም ልማቱን እያፋጠነ ጸጥታውን እያስጠበቀ ነው ብለዋል። አልፎ አልፎ በነቀምት አካባቢ ችግሮች ቢፈጠሩም እየተፈቱ ናቸው። የዞኑ ሰላም እደሚወራው አይደለም ብለዋል።
‹‹ በዞኑ አልፎ አልፎ ሽፍቶች ነበሩ በህግ እየተጣራ ታስረዋል። የቀሩትም በራሳቸው ፍቃድ እጃቸውን ሰጥተዋል። ስልጠና በመውሰድም በፖሊስነት፣ የመንግስት ሰራተኛ የነበሩ ወደ ስራቸው፣ ግብርና መግባት የፈለጉም ስልጠና ወስደው ወደ ግብርና
በመግባት ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለዋል››ያሉት አስተዳዳሪው፤ ‹‹ በዞናችን የጽጥታ ችግር የለም። ህብረተሰቡም ከዚህ በኋላ የዞኑን ጸጥታ የሚያውክ ሽፍታ ነው፤ የእኛ ወገን አይደለም በማለት አውግዞታል። ከኦነግ ጋር በተያያዘ በፊት የነበረው ችግር አሁን የለም። ሰላምን መርጦ በሰላማዊ መንገድ ፖለቲካ እያራመደ ነው›› ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መሀመድ ሀመደኒል፤ አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያ ቀያቸው ተመልሰው የእርሻ መሳሪያዎችና ግብዓት ቀርቦላቸው እንደሌሎች ነዋሪዎች የግብርና ስራቸውን እያከነወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥቂት ተፈናቃዮች የተሰራላቸው ቤት ዝናብ እንደሚያፈስና የቤት ጥራት ችግር በመኖሩ እንዲስተካከል፣ እርዳታው ቢኖርም ክረምት በመሆኑ ከትራንስፖርት ችግር ጋር ተያይዞ ምግብ በወቅቱ እንደማይደርስና ይህን ችግር ለማስቀረት የማከዕል ማስተካከያ ለማድረግ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ