አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አሰሪዎችን ራዕይ የሚያሳካ ጠንካራ ተቋም እውን እንዲሆን እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን አስታወቀ። ኮንፌደሬሽኑ ትናንት ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ጋር ውህደት ለመፍጠር በሚያደርጋቸው ድርድሮች የሚወክሉትን ተደራዳሪዎች ሰይሟል።
የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ አሰሪዎችን መብት የሚያስጠብቅ አንድ ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር በኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን እና በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን መካከል የውህደት ድርድር ለመጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከዓለም የሰራተኞች ድርጅት በቀረበ ጥያቄና ምክረሃሳብ እንዲሁም ከኖርዌይ የአሰሪዎች ኮንፌደሬሽን በተገኘ ድጋፍ ሁለቱ ኮንፌደሬሽኖች ተዋህደው አንድ ጠንካራ የአሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ለመመስረት የሚያስችል ውህደት ለመፍጠር ተግባራዊ እርምጃዎች ተጀምረዋል።
የኮንፌደሬሽኖቹ ውህደት የአሰሪዎችን መብት በማስጠበቅ ለአገሪቱ እድገት ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ስለሚያደርግ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ለሕጋዊ ድርድርና ውይይት ዝግጁ መሆኑንም ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ኮንፌደሬሽኑ በትናንቱ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔው 25 አባላት ያሉትን የኮንፌደሬሽኑን ጠቅላይ ምክር ቤትና ሦስት አባላት ያሉት የቁጥጥር ኮሚቴ አባላትንም መርጧል።
የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን የአሰሪዎችን መብት በማስከበር ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የማይተካ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችል አሰሪዎች መፍጠርን ዓላማው አድርጎ በግንቦት ወር 2010 ዓ.ም የተቋቋመና በተለያዩ ዘርፎች ስር የሚገኙ የአሰሪዎች ፌደሬሽኖችን ያካተተ ጥምረት ነው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2011
አንተነህ ቸሬ