ኢትዮጵያ-በሌማት ትሩፋቱ በረከት

ኢትዮጵያ ምድረ-ለምለም ይሏት ድንቅ ሀገር ነች:: የተራራዎቿ ጉያዎች የተሸሸገ ፀጋ አላቸው:: ከዓመት ዓመት የሚፈሱ ወንዞቿ በበረከት ተሞልተዋል:: ንፁሕ አፈሯ የዘሩበትን ያበቅላል:: በወጉ እጅ ያልነካቸው ማዕድናት ተዝቆ የማያልቅ ሀብትን ሸሽገው ይዘዋል:: ኢትዮጵያ- ተፈጥሮን ከአዕምሮ ጥበብ አጣምራ፣ በተጓዘች ጊዜ ለዓለም ተዓምር ሊያስብሉ የሚቻላቸውን ድንቅ እሴቶች ማሳየት ብርቋ አይሆንም::

ይህች አገር ለዘመናት ከኋላዋ ሲከተላት የኖረው የድርቅና ረሀብ ታሪኳ በቀላሉ ሳይፈዝ ዓመታት ተቆጥረዋል:: እንዲያም ሆኖ ድንቅ ተፈጥሮዋ ዘወትር አብሯት ነው:: ዛሬም ይሁን ቀድሞ ‹‹ሁሉ በእጇ፣ ሁሉ በደጇ›› ስለመሆኑ ድፍን ዓለም አሳምሮ ያውቃል:: እንደ ጥንቱ ‹‹የዳቦ ቅርጫት›› ናት ባትባልም ፀጋ በረከቶቿን አላጣችም::

እነሆ! ይህች ድንቅ ሀገር ካቀረቀረችበት ቀና የሚያደርጋትን የትንሳዔ ጉዞ ጀምራለች:: በመዳፏ ያሉ በረከቶች ውሃ ያነሱ ይዘዋል፣ በምድሯ የፈሰሱ ሀብቶች ከልካቸው ሊገኙ ጊዜው ደርሷል:: ኢትዮጵያ ዛሬም ጥቁር አፈሯ ምግብ፣ ነፋሻ አየሯ መድኅን ሆኖ ሕዝቦቿን ጤና አውሎ ያሳድራል::

ሀገራችን ለግብርናው ልማትና ለእንስሳ ሀብት አመቺ የሚባልን ምኅዳር ተችራለች:: ያላትን ዕምቅ ሀብት በወጉ መጠቀም ላይ ግን ብዙ እንደሚቀራት ጥናቶች ያረጋግጣሉ:: መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በብሔራዊ ደረጃ የተመዘገበው ዓመታዊ የወተት ምርት 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሊትር ነው:: ዓመታዊው የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ደግሞ ከ66 ሊትር የበለጠ እንዳልሆነ ይታወቃል:: ይህ ማለት ለአንድ ሰው በዓመት ከሚያስፈልገው የወተት ድርሻ እጅግ አነስተኛውን መጠን የያዘ መሆኑን ያመላክታል::

ይህ እውነታ ኢትዮጵያ እንደ አማራጭ የተቀነባበሩ የወተት ተዋፅዖዎችን ከውጭ ሀገራት እንድታስገባ ያስገድዳታል:: በዚህ ምክንያትም በየዓመቱ ከ25 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታወጣለች:: በዕንቁላልና የዶሮ ሥጋ ምርትም ሀገራችን መልካም የሚባል ሀብትና ምቹ ሁኔታዎች አሏት ቢባልም ተጠቃሚ መሆን ግን አላስቻላትም:: ሀገራችን በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ናት:: በቂ ወተትና ተዋፅዖዎቹን የማግኘት ዕድሉን ግን ተነፍጋለች::

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዕንቁላል ጣይ ዶሮዎች መካከል 75 በመቶው ያህሉ በዓመት በአማካይ የሚጠበቅባቸውን ያህል አያስገኙም:: በሌሎች ሀገራት ግን የምርቱ ሂደት በዘመናዊ አሠራር በመታገዙ ከአንድ ዶሮ በዓመት 270 ዕንቁላሎችን ማግኘት ይቻላል:: ተጠቃሚዎቹም የዶሮ ሥጋን እንደልብ በመመገብ የሚያህላቸው የለም:: እነዚህና መሰል እውነታዎች ኢትዮጵያ ተዘናግታ ከቆየችባቸው ኋላ ቀር ልማዶች እንድትነቃ ደወል ሆኗል::

ሀገራችን ድንቅ የተፈጥሮ ሀብትና ምርት በእጇ እያለ በወጉ ያለመጠቀሟ ሐቅ ለዘመናት ዋጋ አስከፍሏታል:: እስከ አሁን እንደ ዕምቅ ሀብቶቿ ብዛት ያሻትን ያህል እጇን አልሰደደችም:: በእልፍ በረከቷና በደጇ ሞልቶ ሊፈስ በሚችል ፀጋዋም የበይ ተመልካች ሆና ቆይታለች:: አሁን ግን ይህ ታሪክ በ‹‹ነበር›› ሊሻር ጊዜው ደርሷል::

እነሆ! ዛሬ ሀገራችን የመሶቧ ሙላት ለሌሎች ጭምር እንዲተርፍ የለውጥ ጉዞ ጀምራለች:: በሌማት ትሩፋት መርሐግብር ያሏት ፀጋዋች በወጉ ተለይተዋል:: በዚህ ዘርፍ በሚመዘገቡ ውጤቶችም ኢኮኖሚውን ማሻሻል ከሚቻልበት አግባብ እየተደረሰ ነው:: በመርሐግብሩ ከእንስሳት፣ ከዓሣና ከማር ሀብት የሚገኘውን ፀጋ በወጉ በመጠቀም ኅብረተሰቡን መድረስ የሚቻልበት አሠራር ዕውን መሆን ጀምሯል::

አርብቶ አደሩን ከከተሜው ሳይለይ በአንድ ከሚያዛምደው የሌማት ትሩፋት ቆርሶ የማይጎርስ የለም:: ሁሉም በፀጋው በረከት እጁን ሰዶ ሊሳተፍ በገበታው ዙሪያ ተገኝቷል:: ብዙዎች በግልና በማኅበር ተደራጅተዋል:: ቀድሞ በዓይን ብቻ የሚያውቁት በ‹‹ነበር›› የሚሰሙት ትሩፋት ዛሬ ከሌማታቸው ተርፎ፣ ለሌሎች ጭምር ሊደርስ የገቢ ምንጫቸው ሆኗል::

አሁን በዘመናዊ የንብ ቀፎ በኪሎግራም ማር የሚቆርጡ፣ ከዶሮዎች በረከት በሺዎች ዕንቁላል የሚቆጥሩ፣ በወተት ምርታቸው አይብ ከቅቤ የሚዝቁ፣ በርክተዋል:: የሌማት ትሩፋቱ አንዱ መገለጫ ጥራትን ከፍጥነት እውን ማድረግ ነው:: ምርታማነትን በማዘመንም ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነትን ይተገብራል:: በኦሮሚያና ሲዳማ ክልሎች አካባቢዎችን በመንደር ከማደራጀት ባለፈ፣ ቴክኖሎጂን የመተግበር ሥራዎች ተከውነዋል:: በዚህም የተሻለ ገቢን ማሳደግና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ተችሏል:: በመርሐ ግብሩ የተለየ ትኩረት መኖሩ በኅብረተሰቡ አኗኗር ላይ መልካም የሚባል ለውጥን አምጥቷል:: ለዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋሙ ከሃያ ስድስት ሺህ በላይ የማምረቻ መንደሮች አስተዋፅዖ አበርክተዋል::

በሲዳማ ክልል በአንድ ዓመት ብቻ የዕንቁላል ምርት ቁጥሩ ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ወደ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ማደግ ችሏል:: በተመሳሳይም የሥጋ ምርት ከ94 ሺህ ቶን ወደ 122 ሺህ ቶን ከፍ ብሏል:: የኑሮ ውድነትን ለመቋቋምና ሕይወትን በተሻለ ለመምራት ዋነኛ መንገድ የሆነው የሌማቱ ትሩፋት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መታገዙ በርካታ ችግሮችን ለመቅረፍ ቀኝ እጅ እየሆነ ነው::

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው በ2017 በጀት ዓመት በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ሦስት ቢሊዮን 503 ሊትር ወተት ተገኝቷል:: 37 ነጥብ ስድስት ሺህ ቶን የዓሣ ምርትም ተመዝግቧል:: በተመሳሳይ በማር ምርት የተገኘው ውጤት 42 ነጥብ 19 ሺህ ቶን መድረሱን ያመላክታል::

በያዝነው ዓመት በወተት ምርት 12 ቢሊዮን 116 ሊትር ለማምረት ታቅዶ በአራት ወራት ውስጥ 3 ቢሊዮን 503 ሊትር ለማግኘት ተችሏል:: በዚህ ዘርፍ በኩል የሚኖረውን ምርታማነት ለማሳደግ የወተት ላም ዝርያን ማሻሻልና በመኖ አቅርቦቱ ላይ ትኩረት ማድረግ የሚጠበቅ ይሆናል:: የወተት የዶሮ፣ የእንቁላልና የዓሣ ምርቶችን ለማሳደግም በሀገር አቀፍ ደረጃ መርሐ ግብር ተቀርፆ መተግበር ጀምሯል:: በያዝነው ዓመት አራት ወራት በነበረው ክንውንም 37 ነጥብ ስድስት ሺህ ቶን የዓሣ ምርትና 42 ነጥብ 19 ሺህ ቶን የማር ምርት ማግኘት ተችሏል:: 2 ቢሊዮን 853 እንቁላልና 56 ሺህ ቶን የዶሮ ሥጋም የትሩፋቱ በረከት ሆኖ ተመዝግቧል::

የሌማት ትሩፋት ዋና ዓላማ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው:: ለተጠቃሚው የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥም ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታል:: ይህ ትሩፋት አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ከሸማቹ የማገናኘት ትሰስርም አለው:: እንዲህ ዓይነቱ እውነታ ሀብት በማሳባሰብ ረገድ ለሚኖረው ሂደት ጠቀሜታውን የጎላ ያደርገዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚሉት በቀጣዮቹ ዓመታት የሚተገበረው የሌማት ትሩፋት በወተት፣ በዶሮና በማር ምርቶች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል:: በዚህም የሥርዓተ ምግብ ችግሮች እንዲቀረፉና የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ዕድሉን ያሰፋል:: ወደውጭ የሚላኩ ምርቶችን በማበራከትም በውጭ ምንዛሪ የሚገቡትን አቅርቦቶች ለማስቀረት ያስቻላል ::

በሀገራችን መተግበር የጀመረው የሌማት ትሩፋት ‹‹ኢትዮጵያ›› ከሚለው ስም ቀጥሎ ስንጠራበት የኖርነውን ክፉ ስያሜ ከስሩ ነቅሎ የማስቀረት ኃይል አለው:: ሀገራችን የችግርና ረሀብ ምሳሌ ለምትመስላቸው ሁሉ ትሩፋቱ በአካል የሚታይ፤ በተግባር የሚፈተሽ ታላቅ በረከት ሆኖ ተረጋግጧልና::

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You