አዲስ አበባ፡– በአሜሪካ የሚኖሩ የኦሮሞ ልማት ማህበር አባላት አራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ለማህበሩ ድጋፍ አደረጉ።
የኦሮሞ ልማት ማህበር አባላት በሚኒሶታና በሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች ከሚኖሩ አባላቱ ያገኛቸውን የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች በትናንትናው ዕለት ተረክቧል። በዚህም የማህበሩ አባላት የሰባሰቧቸውን 139 ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችና 25 የፕላዝማ ማስተማሪያ ስማርት ቴሌቪዥኖች የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ከሰሜን አሜሪካ አባላቱ ተወካዮች የተረከቡ ሲሆን፤ አገር ውስጥ ያልደረሱትን ሦስት የተማሪዎች ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ አውቶቡሶችና 83 ቀሪ ላፕቶፖች ደግሞ ከትንሽ ቀናት በኋላ ለማህበሩ ገቢ የሚደረጉ ይሆናል።
በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት የማህበሩ የቦርድ ሊቀ መንበር አቶ አባዱላ ገመዳ፤ “ከዚህ ቀደም የነበረው ዲያስፖራ አገር ውስጥ የሚከናወኑ ነገሮችን በመቃወም ነበር የሚታወቀው፤ አሁን ግን በዓላማ አንድ በመሆናችን በሁሉም ነገር መተባበር ተጀምሯል” ብለዋል።
የኦሮሞ ልማት ማህበር ከመጀመሪያውም የፖለቲካ ዓላማ የሚስተናገድበት የአንድ ድርጅት ወይም ፓርቲ ሳይሆን ሁሉም ኦሮሞ የሚረዳዳበት ማህበራዊ ተቋም መሆኑን ያመላከቱት አቶ አባዱላ፤ የነበረውን የፖለቲካ ልዩነት በማስታረቅ የተጀመረው የመተባበርና የመደጋገፍ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መልካም ጅምር መሆኑን ገልጸዋል።
የልማት ማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ኢቲቻ በበኩላቸው ‹‹ድጋፍ ለማሰባሰብ ያካሄድነው ጉዟችን ተሳክቶልን ከአባላቶቻችን አመርቂ ድጋፍ አግኝተን ተመልሰናል” ብለዋል።
ከለውጡ ወዲህ በውጭ የሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት የልማት ተነሳሽነት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱንም አድንቀዋል። በመሆኑም አብዛኛው የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ወደ ሃገሩ ተመልሶ ኢንቨስት ለማድረግ የልማት ማህበሩንም ለመደገፍ ፍላጎት ያለው መሆኑን መረዳታቸውን ተናግረዋል።
በሰሜን አሜሪካ የኦሮሞ ልማት ማህበር ሰብሳቢ የሆኑትና ድጋፉን በተወካይነት ያስረከቡት አቶ ቡሊ በዳኔ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳዮች ተቀላቅለውብን በፖለቲካ አመለካከታችን ስለተለያየን ብቻ የህዝብን ኑሮ በሚያሻሽሉ የልማት ጉዳዮችም አንድ ላይ መስራት አልቻልንም ነበር፤ ይህ ግን የህዝብን ጥቅም የሚጎዳ አካሄድ ስለሆነ ከዚህ በኋላ የነበረው የፖለቲካ ልዩነት በመወገዱ በህዝብ ጥቅም ጉዳይ ላይ ተባብረው ለመስራት መወሰናቸውን አመላክተዋል። በኦሮሞ ልማት ማህበር አማካኝነት ለህዝብ የሚደረገው ድጋፍም ከዚህ በላይ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2011
ይበል ካሳ