•በእህት ድርጅቶች መካከል ከድርጅታዊ ዲስፕሊን ውጪ የሚወጡ መግለጫዎች ከኢህአዴግ መርህ ውጪ መሆናቸውን
•ክልላዊ ወቅታዊ ፖለቲካና ፀጥታ ሁኔታ ልዩ ትኩረት ይሻሉ
አዲስ አበባ ፦ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአስር ተከታታይ ቀናት ባደረገው ጥልቅ ግምገማ ባለ 6 ነጥብ የአቋም መግለጫን በማውጣት ተጠናቋል::
በመግለጫው እንደተመላከተው በእህት ድርጅቶች መካከል ከድርጅታዊ ዲስፕሊን ውጪ የሚወጡ መግለጫዎችና እየተደረሱ ያሉ ድምዳሜዎች ከኢህአዴግ መርህ ውጪ በመሆናቸው የትኛውም ዓይነት የሃሳብ ልዩነት ቢኖር በድርጅቱ ባህል መሠረት ማስተናገድ እንደሚገባ ተገልጿል።
ክልላዊ ወቅታዊ ፖለቲካና ፀጥታ ሁኔታ ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው በዝርዝር መገምገሙን ገልጾ፤ እንደ ሀገርና ክልል ከገባንበት ያለመረጋጋት ለመውጣት የድርጅቱ ውስጣዊ ጥንካሬ ወሳኝ ነው፤ አመራሮችም በከፍተኛ የሃላፊነት መንፈስ እና ህዝባዊ ውግንና መንቀሳቀስ የሚጠይቀን ወቅት ላይ መሆናችንን መተማመን ላይ ደርሰናል ብሏል።
እንደ መግለጫው በመብት ጥያቄ ሽፋን የሚደረጉ የትኛውንም ኢ-መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ስርዓት በማስያዝ የህዝቦችን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ እንዲሁም የህግ የበላይነትን ማስከበር ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ነው ያለው ማዕከላዊ፤ ኮሚቴው በዚህም ድምዳሜ ላይ መደረሱን ጠቁሟል።
በክልል የመደራጀት ጥያቄን በተመለከተ የህዝቦች ህገ-መንግስታዊ መብት ነው ያለው መግለጫው፤ ይህ ጥያቄ ሲነሳ የነበረው ከአንድ አካባቢ ብቻ ባይሆንም ጥያቄውን በጥናት ላይ ተመስርቶ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ድርጅቱ በአስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በወሰነው መሰረት በዝርዝር ህዝቡን ያሳተፈ ጥናት ተደርጓል ።
በጥናቱ የቀረቡ አማራጮችን በጥልቀት በመመርመር፣ የህዝቡን የጋራ ዘላቂ ጥቅም የሚያረጋግጠውን አማራጭ በመውሰድ የክልል አደረጃጀት ጥያቄዎች በሚመለሱበት አግባብ ላይ አቋም ወስዷል ብሏል ።
በክልላችን መላው ህዝብ ምክክርና ውይይት የሚያደርግበት ሆኖ በአንድ በኩል በጥናቱም የተገኘውን የክልሉ ህዝቦች አብሮ የመቀጠል ፍላጎትን ባከበረ በሌላ ጎኑ ደግሞ ጉባኤውን ውሳኔ ተግባራዊ ባደረገ መንገድ እና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ለመምራት ማዕከላዊ ኮሚቴው ተስማምቷል።
በእያንዳንዱ አካባቢ ያለውን የልማት ሁኔታ በተመለከተ በድርጅታችን መሪነት በክልላችን የተመዘገቡ የልማት ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው በተለያየ መልኩ የሚገለጽ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የመልካም አስተዳደርና የአመራር ሥርዓታችን ላይ የሚታዩ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው ተወስዷል። ከዚህም በመነሳት በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ ይደረጋሉ ብሏል መግለጫው::
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2011
እፀገነት አክሊሉ