የጋዜጠኛው ዘመን ተሻጋሪ ትዝታዎች

የዛሬው የሕይወት ገፅታ እንግዳችን ንጉሤ /ርተፈራ ናቸው። በርካታ ኢትዮጵያውያን በብስራተ ገብርኤል ራዲዮ ጣቢያና ብሄራዊ ራዲዮ ይሠሯቸው በነበሩ ዝግጅቶች ያስታውሷቸዋል። በተለይ በምርመራ ጋዜጠኝነት አያሌ ወንጀሎችንና ሕገወጥ ድርጊቶችን በመረጃ ከማጋለጥ አንስቶ መንግሥታዊ አሠራር ሥርዓቶች እንዲሻሻሉ ምክንያት ነበሩ። በጋዜጠኝነት ቆይታቸው ከሚጠቀሱት ዋና ዋና ሥራዎቻቸው መካከል «ከምናየውና ከምንሰማው» እንዲሁም «እኔም ለሀገሬ» በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች የሚያጠናቅሯቸው ዘገባዎች ይታወሳሉ።

የውጭ ጉዳይ የፍትህና የማስታወቂያ ቢሮ ሃላፊ ከመሆን ጀምሮ በልዩ ልዩ የመንግሥት ሃላፊነቶች አገልግለዋል። በሚዲያና ኮሙኒኬሽን አያሌ የጥናት ሥራዎችን አሳትመዋል፤ የፖፒዩሌሽን ሚዲያ ሴንተር በኢትዮጵያን 20 ዓመታት መርተዋል። «Innovative Media and Communication Strategy for Development» በሚለው የኢትዮጵያን ተሞክሮ በሚያጋራው ትምህርታዊ መፅሀፋቸው ይታወቃሉ። ከአንድ ሳምንት በፊት ደግሞ «ዞር ብዬ ሳየው« የሚል ባለ 413 ገፅ መፅሃፍ ለአንባቢያን አቅርበዋል።

ድል በርየሕይወት መጀመሪያ

ንጉሤ ዶ/ር በአዲስ አበባ ድል በር የካቲት 12 ቀን 1940 ዓ.ም ነው የተወለዱት። የያኔው ታዳጊ የአሁኑ የሀገር ባለውለታ እንዳሁኑ የከተማ ቤቶች ባልተሰገሰጉበት የኢትዮጵያ መዲና ከተፈጥሮ ጋር በጥብቅ ተወዳጅተው፣ በነፃነት ቦርቀው ነው ያደጉት። የትዝታ ማህደራቸውን መለስ ብለው ሲቃኙት ‹‹የጉለሌ አካባቢ አሁን ካለው አዲስ አበባ መልኩም፣ ሽታውም፣ ድምፁም እጅግ የተለየና እንደ አሁኑ በሕንፃ ጫካ ሳይሆን፣ በባሕር ዛፍ ጫካ የተሸፈነ ነበር›› ይላሉ። ንፁህ አየር ስበው ከምድር የተፈጥሮ ገፀ በረከቶች ጋር ተወዳጅተው ማደጋቸውን ሲናገሩ።

ምንም እንኳ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ እምብርት ብትሆንም እንደ አሁኑ በህንፃና አስፋልት ብዛት አልተጨናነቀችም ነበር። ለዚህ ነው ንጉሤ ዶ/ርከከተማ ይልቅ የገጠር ገፅታ የሚያይልበት ወቅት እንደነበርና በአእዋፋት ዝማሬ የታጀበ የልጅነት ጊዜ እንዳሳለፉ የሚገልፁት። ቤተሰቦቻቸው ገና በልጅነታቸው ተለያይተው ከእናታቸው ጋር ቢያደጉም አባታቸውን በቅርበት የማግኘት አጋጣሚው ነበራቸው። ይህ ደግሞ የሥነ ልቦና ጫና እንዳያድርባቸው ትልቅ እድል እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ።

‹‹እናቴ በኢኮኖሚ አቅም ደካማ በመሆኗ፣ በድህነት ምክንያት በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ባልፍም፤ የምኖረው ከእናቴ ጋር በመሆኑና፣ አባቴንም በቅርብ እያገኘኋቸው ስላደግሁ፤ በወላጆቼ መለያየት የልጅ አእምሮዬን የሚጎዳ የከፋ ችግር አልደረሰብኝም›› የሚሉት የዛሬው የሕይወት ገፅታ ባለታሪካችን የልጅነት ጊዜ አስተዳደግና የቀለም ትምህርት የቀሰሙበትን አጋጣሚዎች እንዲህ ባለ መልኩ አጫውተውናል።

ከቄስ ትምህርት እስከ ዩኒቨርሲቲ

ንጉሤ የዶ/ር የሙያና ሀገርን የማገልገል ጠንካራ ሥብእና የተገነባው በጊዜ ሂደት ውስጥ ባሳለፏቸው የመንፈሳዊና የቀለም ትምህርት ልምዶች ነው። እድሜያቸው እውቀትን የመገብየት ጥንካሬ ላይ ሲደርስ ቄስ ትምህርት ቤት ገቡ። ወደ አስኳላ የላኳቸው እናታቸው ወይዘሮ አስናቀች ኑሯቸውን ለመደጎም ከብቶችን በማርባት (የወተት ሽያጭ)፣ ለመብራት አገልግሎት የሚውል ነጭ ጋዝ ለመንደሩ ነዋሪዎች በማከፋፈል የሚታትሩ ጠንካራ ሰው ነበሩ።

‹‹ማንበብና መጻፍ የቻልኩት አቅራቢያችን በሚገኘው ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን አጠገብ የመምሬ ኃይለ ጊዮርጊስ ቄስ ትምህርት ቤት ገብቼ ነው›› ይላሉ፤ ጊዜውን መለስ ብለው እያስታወሱ። መምሬ ሃይለኛ እንደነበሩና ካጠፉ ከባድ ቅጣት ይቀጧቸው እንደነበር ይናገራሉ። በወቅቱ በቄስ ትምህርት ቤት መንፈሳዊ የሆኑ እንደ መልእክተ ዮሐንስን፣ ወንጌልን ወይም መዝሙረ ዳዊትን ያጠኑ ነበር።

የትምህርት ጉዟቸው ቀጥሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩት በቁስቋም መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ነው። በዚያ እንዲማሩ ያደረጉት ደግሞ እናታቸው ናቸው። ንጉሤ ዶ/ር ፤ ‹‹ለልጇ መልካምና የተሻለ የተባለውን ከማድረግ ወደኋላ የማትል ስለነበረችም፣ ሩቅም ቢሆን ቁስቋም ትምህርት ቤት አስገባችኝ›› ይላሉ፤ ለዛሬው የትምህርት ስኬታቸው የእናታቸው የቀደመ ደጀንነት ትልቅ አስተዋፆ እንደነበረው ሲያስረዱ።

ትምህርት ቤቱ ራቅ በማለቱ ንጉሤና ዶ/ር ጓደኞቻቸው በቀን ደርሶ መልስ 20 ኪሎ ሜትር ለመሄድ ይገደዱ ነበር። ለትምህርታቸው ከሚሰጡት ትኩረት ባሻገር አድካሚውን ጉዞ ተቋቁመው በመንገዳቸው የሚያጋጥማቸውን ተፈጥሮ (በእርሳቸው አበባል፤ ዳገት ወጥተው፣ ቁልቁለት ወርደው፣ አራት ወንዞች ተሻግረው፣ በጫካ ውስጥ አቆራርጠው) ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈው ነበር የተማሩት። ለተፈጥሮ በእጅጉ ቅርብ የነበችው አዲስ አበባም በመንገዳቸው ላይ ከሚበቅሉ የሾላ ፍሬ፣ በለስ፣ ቀጋና አጋም ታሽራቸው ነበር።

ይህ ከእናታቸው የምሳ አምስት እና አስር ሳንቲም ስጦታ ጋር ተደምሮ የጉዞውን አድካሚነት በጠንካራ ተማሪነት እንዲተኩት ሃይል ይሆናቸው ነበር። አዲስ አበባ ተወልደው በማደጋቸው ለከተሜነት ይቅረቡ እንጂ በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘውን የተፈጥሮ ፀጋ እዚሁ አግኝተውት ነበር። በዚህ ምክንያት ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› እንደሚባለው ብሂል የገጠር ሕይወትን በከፊል የማየት እድል አልተነፈጉም። ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት ሥነ ልቦና ጋር በእጅጉ አዛምዷቸዋል።

‹‹ቁስቋም ትምህርት ቤት የትምህርት አሰጣጡ ጥሩ ነበር›› ይላሉ፤ ተማሪዎች ከትምህርት ሰዓት ውጪ በነፃነት የሚጫወቱበትና የሚቦርቁበት ጥሩ የኳስ ሜዳ ያለው ትምህርት ቤት እንደነበር እያስታወሱ፤ በአንድ ክፍል ውስጥ እስከ 50 ተማሪዎች ሆነው ይማሩ እንደነበር እየገለፁ፤ እርሳቸው በትምህርታቸው ጎበዝ ቢሆኑም የደረጃ ተማሪ እንዳልነበሩ ይገልፃሉ። ሆኖም በታሪክ፣ በሒሳብ እና በአማርኛ ትምህርት ከክፍሉ ከፍተኛ ውጤት ከሚያመጡ ተማሪዎች አንዱ እንደነበሩ አይሸሽጉም። የንባብ ባህልን ያዳበሩት፣ መፅሀፍትን ጓደኛ ማድረግ የጀመሩት በዚያው ትምህርት ቤት ነበር። ልብ ወለድ የመፃፍ ሙከራም በዚያን ጊዜ ነበር የጀመሩት። ‹‹መጽሐፍ ለመግዛት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ እናቴን፣ ትምህርት ቤት፣ ‘መጽሐፍ ግዙ፣ ካለዚያ አትገቡም ተብለናል’ እያልኩ እዋሻታለሁ›› በማለት ለንባብ የነበራቸው ፍላጎት የት ድረስ እንደነበር ይገልፃሉ።

ንጉሤ ዶ/ር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በወቅቱ ዘመናዊ በነበረው ተፈሪ መኮንን ነው። በዚያ ልዩ የጋዜጠኝነት ክህሎት ለማዳበር መነሻ የሆናቸውን የክርክርና ውይይት ክበብ ከመቀላቀላቸውም ባሻገር ሙሉ በሙሉ በካናዳውያን ጄዚዊትስ የሚመራ የቀለም ትምህርት የመገበየት አጋጣሚው ነበራቸው። መንፈሳዊ ትምህርት (የወንጌል ጥናት) በጥልቀት እንዲረዱና የሕይወት አቅጣጫቸው እንዲቀየርም ምክንያት ነበር። ይህ መንፈሳዊ ጉዟቸው ተጠናክሮ ቀጥሎ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ ይበልጥ እንዲሳተፉ ከማድረጉም ባሻገር ለጋዜጠኝነት ሙያ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ሄደው እንዲማሩ ትልቅ የእድል በር የከፈተላቸው ነበር።

ንጉሤ የዶ/ር የትምህርት ጉዞ ቀጥሎ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይንስና ገቨርንመንት ዲፕሎማ እንዲሠሩ ምክንያት ሆነ። ትምህርቱን በማታው ክፍለ ጊዜ በማድረግ በወንጌላዊ ቤተክርስቲያን (ሳውዘርን ባብቲስት) መንፈሳዊ ትምህርትን ከመከታተል አልፎ የሥነ ፅሁፍና ሚዲያ (በተለይ ትርጉም ነክ የሆኑ) ፅሁፎችን በቀኑ ክፍለ ጊዜ ይሠሩ ጀመር። ይህ ልምዳቸው ለበለጠ ሃላፊነትና ትምህርት እንዲታጩ ምክንያት በመሆኑ ኬንያ ሄደው ‹‹የኦል አፍካን ኮንፍረንስ ኦፍ ቸርችስ ኮሙኒኬሽን ትሬዲንግ›› በሚባል ትምህርት ቤት ተማሩ።

ንጉሤ ዶ/ር ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በክረምት (በተለይ ተፈሪ መኮንን በነበሩበት ወቅት) በሂልተን የእንግዶችን ሻንጣ ተረክበው የሚያስተናግዱ ‹‹ቢል ቦይ›› የሚባሉ ሠራተኞች አስተባባሪ ሆነው ሠርተዋል። ይህ ምግባራቸው ለትምህርትና ሥራ ያላቸውን ጠንካራ እምነት የሚያሳይ ነው። ለዚህ ሥብእናቸው ግንባታ ከልጅነትም እናታቸውን በሥራ ማገዛቸው ምክንያት እንደሚሆን ይታመናል።

ብስራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ

ንጉሤ ዶ/ር በሕይወት መንገድ ላይ በዚህ አጭር ሀተታ ተዘርዝረው የሚያበቁ አያሌ ልምዶችን የመንፈሳዊ ሕይወትን ጨምሮ ለሀገር ክብርና ውለታ የሚመጥኑ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግበዋል። እርሳቸውም ‹‹ዞር ብዬ ሳየው›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት የግል ሕይወታቸውን በሚተርከው ዳጎስ ያለ መፅሀፋቸው ላይ በጥሩ የሥነ ፅሁፍ ሙያ ቅንብብ አድርገው አስፍረውታል። ከእነዚህ የሕይወት መንገድ ስኬቶቻቸው ውስጥ ሳይጠቀስ የማያልፈው ግን (በቀድሞው ብስራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ) ያሳለፉት የጋዜጠኝነት ሙያ ቀዳሚው ነው።

ንጉሤ ዶ/ር በብስራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ የጋዜጠኝነት ሙያን የጀመሩት ከፍሬ ነገሮች ማህደር የሚል ርዕስ ያለው ፕሮግራም በማሰናዳት ነበር። ወደዚህ ሙያ እንዲመጡ በኬንያ ወዳጅነት የመሠረቱት ጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ አማካኝነት ነበር። እርሳቸው ወደዚህ ራዲዮ ጣቢያ ከመምጣታቸው በፊት ሳውዘርን ባብቲስ ኮንቬንሽን የተለያዩ መንፈሳዊ ፕሮግራሞችን ሠርተዋል። እስከ 1967 ድረስ በመንግሥት ቀጥተኛ የደብዳቤ ጥሪ የፖለቲካ ተንታኝ (ኮሜነታተር ሆነው) እንዲያገለግሉ እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስ በዚያው ሙያቸው ቆይተዋል። ይህ ልምድ በሙሉ የጋዜጠኝነት ሙያዊ ሥነ ምግባር ለረጅም ዓመታት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ልምድ ያካበቱበትን አጋጣሚ ፈጠረ።

በዚህም በብስራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ ‹‹የሰዎችን ስሜት ይገዛሉ›› የሚሏቸውን ጉዳዮች በመምረጥ በርካታ ዝግጅቶችን ማሰናዳት ቻሉ። ታሪክ ከሚያወሳቸው ዘመን አይሽሬ ዐሻራዎቻቸው መካከል ‹‹የእስራኤልና የአረቦች ጦርነት መዘዝና አስከትሎ የመጣው የነዳጅ ዋጋ ቀውስ›› የሚዳስሰው ዝግጅት ይገኝበታል። በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት የፈነዳበትን ዓመት ከመስከረም አንድ ጀምሮ እስከ ጳጉሜን መጨረሻ ድረስ የቃኘ በሁለት ተከታታይ ፕሮግራም ማቅረባቸውንና የሕዝብን ስሜት ቆንጥጦ መያዙን በማስታወስ ይገልፃሉ።

ከዚህ ባሻገር ንጉሤ ዶ/ር ጆሮ ገብ የሆኑ የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ዝግጅቶችን ያሰናዱ ነበር። ከእነዚህ መካከል በሲ.አይ.ኤ. እና ኬ.ጂ.ቢ ማለትም በወቅቱ የሶቪየት ኅብረት የደህንነት ተቋም ላይ በተከታታይ ለአራት ሳምንታት ያቀረቧቸው ዝግጅቶች ይጠቀሳሉ። በጊዜው በሕዝብ ዘንድ መደነቅን ከመፍጠሩም ሌላ የወቅቱ የደርግ ሊቀ መንበር

መንግሥቱ ኃይለማርያም ቢሯቸው ድረስ ጠርተው እንዲያነጋግሯቸው ምክንያት ነበር። በኋላም በእሳቸው ትእዛዝ ብሥራተ ወንጌልን ለቅቀው ኢትዮጵያ ሬዲዮ እንዲገቡ ምክንያት የሆኑ በርካታ ዝግጅቶችም ሠርተዋል። እነዚህ የጋዜጠኝነት ሙያ ሥራዎች ንጉሤን ዶ/ር ከሕዝብና ከመንግሥት ጋር ከማስተዋወቃቸውም ባሻገር ለተሻለ ትጋትና ሃላፊነት እንዲነሳሱ መሠረት ሆነዋቸዋል።

ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር

ቀደም ብለን ለመግለፅ እንደሞከርነው ንጉሤ የዶ/ር የሕይወት መንገድ እንዲሁ በአጭር ሀተታ የሚቋጭ አይደለም፤ ዝርዝሩን አርሳቸው በመፅሀፋቸው ላይ በጥልቀት አስፍረውታል። ከሕይወት መንገዳቸው ውስጥ ለዚህ ትውልድ ጥሩ ስንቅ ከሚሆኑ አጋጣሚዎቻቸው መካከል ግን በማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ውስጥ ያሳለፉት የሥራ ዘመን ቀዳሚው እንደነበር ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡን ቃል ገልፀጸውልናል።

በደርግ ተወርሶ በኋላ ወደ መንግሥት ንብረትነት ከተዛወረው የቀድሞው ብሥራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያም በቀጥታ በደብዳቤ ነበር የተመደቡት። በሥራ ቆይታቸውም በሰዎች ሕይወት ላይ በጎ ተፅእኖዎችን የሚያሳድሩ ሥራዎችን ያከናውኑ ነበር። በጊዜው በማስታወቂያ ሚኒስቴር እየሠሩ ለልዩ ትምህርት ወደ ውጪ ሀገር ለመሄድ የውድድሩ አሸናፊ የነበሩ ቢሆንም በሀገር ባላቸው የሥራ ሃላፊነት ምክንያት እንዳይሄዱ መወሰኑን ይገልፃሉ። ይህ በሆነ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ ነበር የሶማሊያ ወረራ እና የእናት ሀገር ጥሪ ተልዕኮን ለመወጣት በተቋቋመ የኮሚቴ አባል ውስጥ የተካተቱት። ይህንን አጋጣሚ ንጉሤ ዶ/ር እንዲህ ያስታውሱታል።

‹‹ኢትዮጵያ ሬዲዮ እየሠራሁ የኢትዮ ሶማሌ ጦርነት በ1969 ዓ.ም በተቀሰቀሰ ጊዜ በየመሥሪያ ቤቱ፣ የእናት ሀገር ጥሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደርጎ ነበር›› የሚሉት ዶ/ር ንጉሤ ሀገሪቷን በጦርነቱ ወቅት ለማገዝ ገንዘብና ሌላም ቁሳቁስ ርዳታ ይሰበሰብ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ሬዲዮ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የማስታወቂያ ሚኒስቴር የእናት ሀገር ጥሪ ኮሚቴ ሰብሳቢና አስተባባሪ ሆነው መመረጣቸውና ማገልገላቸውን ይገልፃሉ።

ንጉሤ ዶ/ር እንደሚገልፁት ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችውን ወረራ መክቶ ለመመለስ እንዲቻል ሰፊውን ሕዝብ ለዘመቻ፣ ለገንዘብና ለቁሳቁስ ርዳታ መቀስቀስና ማስተባበር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አስራ ሁለት አባላት የነበሩበት የማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሚኒስቴ የፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር። በወቅቱ እርሳቸውም የዚሁ አባል ሆነው ከሌሎች የኮሚቴ አባላት መካከል አቶ ገዳሙ አብርሃ፣ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ዶክተር ላጲሶ ጌታሁን፣ የካሚ አባላት በምላሴ አርአያ፣ አቶ አበራ ለማ፣ አቶ አዲስ እንግዳና ሌሎችም ጋር መሥራታቸውን ይናገራሉ። የኮሚቴው አባላት የሆኑ ምድብ ሥራቸውን ሳያጓድሉ በተጨማሪ ከእናት ሀገር ጥሪ አንጻር ጽሑፎችን የማዘጋጀት፣ ቃለ መጠይቆችን የማድረግና ፕሮግራም የማዘጋጀት ኃላፊነት ተጥሎባቸው እንደነበር ይናገራሉ። ከዚህም የተነሳ አንዳንዶቻችን እስከ ካራማራ የኢትዮጵያ ድል ድረስ በጋዜጣ ላይ የሚወጡና በሬዲዮ የሚነበቡ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጽሑፍ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸው እንደነበር ይገልፃሉ። ጦር ግንባር ድረስ በመሄድና ለእናት ሀገሩ እየተዋደቀ የነበረውን ሠራዊት በማነጋገር የሚያበረታቱና ሞራሉን ከፍ የሚያደርጉ ፕሮግራሞች ይዘጋጁ ነበር። በሶማሊያ ወረራ ወቅት ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን አስከ ጦርነቱ ፍፃሜ በቅንነት ማገልገላቸው ለእርሳቸው ከፍተኛ ኩራት የሚፈጥርባቸው አጋጣሚ እንደሆነ ይገልፃሉ።

ለውጥን ያስከተሉ የምርመራ ዘገባዎች

ንጉሤ ዶ/ር በጋዜጠኝነት የሙያ ቆይታቸው ከሚታወቁባቸው በርካታ ዘገባዎች መካከል በምርመራ ጋዜጠኝነት የሠሯቸው ተጠቃሽ ናቸው። እርሳቸው መረጃዎችን አጠናክረው ብልሹ አሠራርን፣ ሌብነት (ሙስናን)፣ በሀገር ውስና በውጭ ሀገራት የተከናወኑ ማጭበርበሮችን እና ሌሎችም በርካታ ወንጀሎችን በማጋለጣቸው ምክንያት የሀገር ሀብትን በማዳን፣ ብልሹ አሠራር እንዲስተካከል፣ የመንግሥት አሠራር እንዲሻሻል ምክንያት ሆነዋል። እነዚህን ሥራዎች ‹‹ከምናየውና ከምንሰማው›› በሚል ርዕስ የሚሰናዱ ነበሩ።

በምርመራ ዘገባ ሥራ ንጉሤ ዶ/ር ከሠሯቸው ውስጥ በደርግ የተወረሱ ትርፍ ቤቶችን፣ የኢንዱስትሪና የፋይናንስ ተቋማትን በአንድነት ጠቅልሎ የሚያስተዳድረው የብሄራዊ ሀብት ልማት ሚኒስቴር ውስጥ የነበረ ዘረፋና ምዝበራን የተመለከተ ነበር። በጊዜው መሰናዶው አየር ላይ መዋሉ መሥሪያ ቤቱ እንዲፈርስ ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር በስሩ ታጭቀው የነበሩ ዘርፎች ራሳቸውን ችለው እንዲወጡ ከፍተኛ ምክንያት ሆኗል።

ሌላው ንጉሤ የዶ/ር ከፍተኛ የምርመራ ክንድ ያረፈበት ተቋም በወቅቱ በኢትዮጵያ የቤት እቃን ጨምሮ የኤክስሬ ማሽን የሚያስመጣው የሞዝቮልድ ኩባንያ ነበር። በዚህ ምርመራ ዘገባ ውስጥ ከኢትዮጵያ ‹‹በምን መልኩ›› የውጭ ምንዛሬ ይሸሽ እንደነበር ማጋለጥ ችለዋል። በተመሳሳይ የሲንጀር ኩባንያ ብዝበዛ ታሪክም ተመሳሳይ የውጭ ምንዛሬና የዘረፋ ታሪክን በማጋለጥና ርምጃ እንዲወሰድ ምክንያት በመሆን የተቋጨ ነበር። የቀድሞው አንጋፋ ጋዜጠኛ ንጉሤ ዶ/ር በዚህ ሳያበቁ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነትና የምርመራ ዘገባ ታሪክ ዛሬም ድረስ የሚወሱ በርካታ ዐሻራዎችን ማኖር ችለዋል። ከዚህ ወስጥ የሀላይ ደጌ የሠፈራ ፕሮግራምና የፈጠራ ትርክትን ያጋለጠው ምርመራ ዘገባ ተጠቃሽ ነው። በዚህ ሥራቸው በሥርዓቱ ለሞት የሚያደርስ ስጋት ደቅኖባቸው እንደነበር ይናገራሉ። ሆኖም እውነቱን ማጋለጣቸው ከሀገር ደህንነትና ሚስጢር አንፃር ልክ አለመሆኑን ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ሃይለማሪያም ቢሯቸው ድረስ ጠርተው ቢነግሯቸውና ቢያስጠነቅቋቸውም የመረጃው እውነትና የሌሎች ሃላፊዎች ጥፋት በመሆኑ በይቅርታ እንደታለፉ፤ ግለ ታሪካቸውን በሚዳስሰው ‹‹ዞር ብዬ ሳየው›› በሚለው ግለ ታሪካቸው ላይ በሰፊው አስፍረውታል።

አስራ ሁለት የሚደርሱ በሀገሪቱ ታሪክ ተፅእኖ መፍጠር የቻሉ የምርመራ ዘገባዎች ንጉሤ በዶ/ር ጥልቅ የምርመራ ብዕር የተዳሰሱ ናቸው።

የሥራ ዘመን ሃላፊነቶች

ንጉሤ ዶ/ር በሥራ ባሳለፉባቸው በርካታ አስርት ዓመታት ውስጥ ከጋዜጠኛ ባለሙያነት አንስተው ሀገራቸውን በተለያዩ ሃላፊነቶች ያገለገሉ የሀገር ባለውለታ ናቸው። የሥራ ድርሻቸውንና ያበረከቱትን አስተዋኦ በቀላሉ በዚህ ሀተታ ላይ ዘርዝሮ መጨረስ አስቸጋሪ ቢሆንም ዋና ዋናዎቹ ከዚህ እንደሚከተለው ይገለፃሉ።

አንጋፋው የቀድሞ ጋዜጠኛ ንጉሤ ዶ/ር በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከ1968 ዓ.ም እስከ 1972 ዓ.ም ከላይ የዘረዘርናቸውን በርካታ ሙያዊ ሃላፊነቶች ተወጥተዋል። ከዚያ በመቀጠል የምርት ዘመቻና የማዕከላዊ ፕላን ጠቅላይ መምሪያ ከ1971-1981 በልማት ነክ ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኃላፊ፣የሕዝብ ግኑኘነት ጉዳይ ኃላፊ፣ የምርት ዘመቻ በሚል ርዕስ የሚታተም መፅሄትን ለአራት ዓመታት በዋና አዘጋጅነት፤ እንዲሁም ከ1981 እስከ 85 ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የውጭ ጉዳይ፣ የፍትህና ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል። በዚህ ወቅት በተለይ መንግሥት የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ እንዲያወጣና ጽህፈት ቤት እንዲቋቋም እንዲሁም የጋዜጠኝነት ሙያ ሥልጠናና ትምህርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ እንዲጀመር ጥናታዊ ምክረ ሃሳብን ከመስጠት ጀምሮ አያሌ ሥራዎችን አከናውነዋል።

ንጉሤ ዶ/ር ለሁለት አስርት ዓመታት የፖፒዩሌሽን ሚዲያ ሴንተር መርተዋል። በፍቃዳቸው ሃላፊነታቸውን በመልቀቅ ጡረታ እስከወጡበት ገዜ አንስቶ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የቀሩና የማህበረሰብ ለውጥ እንዲመጣ የሞገቱ ሃሳቦች እንዲሰርፁ አስተዋኦ ነበራቸው። ለዚህ ሃላፊነት ያበቃቸው ያላቸው የሥነ ሕዝብና የኮሙኒኬሽን የረጅም ዓመታት ልምድ ሲሆን በኢትዮጵያ በገጠራማ አካባቢዎች ጭምር የሚሰራጩ ማህበረሰብ ተኮር ዘገባዎች እንዲሠሩ የበኩር አስተዋኦ ያደረጉ ጉምቱ ባለሙያ ናቸው።

ትውልዱ ምን ይማር?

ንጉሤ የዶ/ር ተፈራን ግለ ታሪክ የሚያወሳው ‹‹ዞር ብዬ ሳየው›› መፅሀፍ ከሳምንት በፊት በብሄራዊ ቲያትር ታላላቅ የኢትዮጵያ ባለውለታዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የሥነ ፅሁፍ ባለሙያዎች እና የልዩ ልዩ ሙያ ባለቤቶች በተገኙበት ነበር የተመረቀው። በወቅቱ የአንጋፋው ጋዜጠኛና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ምሁር ንጉሤ ዶ/ር ተፈራ የሕይወት ዘመን ሥራዎችን በሙያ ባልደረቦቻቸውና የቅርብ ወዳጆቻቸው በትውስታ ተዘክሮ ነበር።

እርሳቸውም ታሪካቸው በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃን የቀረበና በብዙ የተነገረ ቢሆንም አሁንም ከሕይወት መንገዳቸው መጪው ትውልድ ‹‹መማር የሚችላቸው ነገሮች ቢኖሩ›› በሚል ቅን እሳቤ ከጡረታ ዘመናቸው ተሻምተው ሶስት ዓመት የፈጀውን የመፅሀፍ ዝግጀት አጠናቀው ለንባብ እንዳበቁ ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀውልናል።

‹‹በዘመን መጨረሻ ከሚገጥም ፀፀት እግዚአብሄር ይጠብቅ›› ይላሉ ንጉሤ ዶ/ር የመፅሀፉ ለንባብ የበቃበትን ሌላኛውን ምክንያት ሲጠቁሙ። በመሆኑም ትወልዱ መማር የሚችልበት የሙያና የሕይወት ተሞክሯቸውን መፃፍ የማይችሉበት ጊዜ ሳይመጣ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ያደረጉት ጥረት መሆኑን ያስረዳሉ። ከፖፒዩሌሽን ሚዲያ ሴንተር በገዛ ፍቃዳቸው ደብዳቤ ፅፈው የተሰናበቱትም የግለ ታሪካቸውን የሚያትተውን መፅሀፍ ለማሰናዳትና ዐሻራቸውን ለማሳረፍ መሆኑን ይናገራሉ።

ንጉሤ ዶ/ር የአሁኑም የመጪውም ትውልድ የሚገጥማቸው እድሎች በሙሉ ለመጠቀም ማቅማማት የለባቸውም ይላሉ። በሕይወት መንገድ ላይ የሚገኙ መልካም አጋጣሚዎች መልሰን የማናገኛቸው በመሆናቸው አጋጣሚዎቹን ማባከን አይገባንም ይላሉ።

እርሳቸው ከብሥራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ ጀምሮ ለሙያቸው ሙሉ ጊዜ በመስጠታቸው አሁን ለደረሱበት ስኬት እንዳበቃቸው ጠቅሰው ትውልዱ በሙያው በእውቀት፣ በድፍረትና በትህትና ማገልገል እንደሚገባው ይገልፃሉ። ይህንን ማድረግ ከቻሉ ያስቀመጡትን የሕይወት ግብ በቀላሉ ማሳካት ቀላል መሆኑን ነው የሚመክሩት።

ንጉሤ ዶ/ር ተፈራ በሙያ መንገዳቸው ብቻ አይደለም ስኬታማነታቸው። በ1968 ዓ.ም ከባለቤታቸው ወይዘሮ ፀሀይ ካሳ ጋር ትዳር መስርተው ለ 49 ዓመታት ቆይተዋል። ሁለት ሴትና አንድ ወንድ እንዲሁም ሁለት የልጅ ልጆችን አፍርተዋል። ልጆቻቸው ልክ እንደ እርሳቸው ሁሉ ሀገራቸውን በተሠማሩበት ሙያ በማገልገል ላይ የሚገኙ ናቸው።

የዝግጅት ከፍላችን በዛሬው አትሙ ካሠፈራቸው መረጃዎች ባሻገር የባለታሪካችን ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ የሕይወት ልምድ፣ የሙያ አጋጣሚዎችና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በተጨማሪነት ለማወቅ የሚፈቅድ አንባቢ ከሰሞኑ ታትሞ ለንባብ የበቃውንና ግለ ታሪካቸውን በስፋት ያወሱበትን ‹‹ዞር ብዬ ሳየው›› መፅሀፍ እንዲያነብ እንጋብዛለን። ሰላም!!

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን እሁድ ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You