በየዓመቱ ህዳር መጨረሻ ላይ የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ዘንድሮም ለ19ኛ ጊዜ ሊከበር ሽር ጉድ ላይ ነን፡፡ ከሰማንያ በላይ የሆኑ ብሄረሰቦች በማንነታቸው አምረውና ደምቀው የሚታዩበት የአብሮነት መንፈስን የሚጭር ክብረበዓል ሆኖ ለብዙ ጊዜ ዘልቋል፡፡ ሀገርን ካስጌጡና ካስጠሩ መልከደማም ማንነቶች መሀል አንዱ የሆነው ይህ የብዙሀነት ቀን ዘንድሮም ባማረና በደመቀ መልኩ በተለያዩ መሪ ሃሳቦች ይከበራል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ መልከ ብዙ የብሄር እናት ናት፡፡ ብዙ ልጆችን፣ ብዙ መልኮችን፣ ብዙ ወግና ልማዶችን፣ እልፍ ሥርዓትና ባህል አቅፋ የያዘች ናት፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደሚባለው ቁርጥ እሷን መሳይ እልፍ መልከኛ ልጆችን ታቅፋለች፡፡ ይሄ የእናት ጉያ..ይሄ የእምዬ እቅፍ ልዩነት የለውም፡፡ በተለያዩ ብሄሮች፣ በተለያዩ ቋንቋዎች፣ እንዲሁም ከዚያም ከዚህም በበቀሉ ደም ግባቶች የቆነጀ የእናት ዓለም ክንድ ነው። በስብጥር መልኮች፣ በድብልቅ ቀለሞች እና በውህድ ዘዬዎች የበረታ የእናት ዓለም ጉያ ነው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ልጆቿን ለመታቀፍ፣ ልጆቿን ለመሰብሰብ ታክታ አታውቅም፡፡ ቢዘረጋ ከዚህ እስከዚያ የሚደርስ የርህራሄና የደግነት፣ የታሪክና የሥልጣኔ ክንድ አላት፡፡ እኛ እንዋደድ እንጂ፣ እኛ ልዩነታችንን ለውበት ውበታችንን ለአንድነት እንጠቀመው እንጂ የኢትዮጵያ መዳፍ ሰፊ ነው፡፡ እኛ ፍቅርን እንወቅ እንጂ፣ በምክክርና በንግግር ችግሮቻችንን እንፍታ እንጂ ጉያዋ ለሌሎች የሚበቃ ነው፡፡ እኛ በአንድ ሃሳብ፣ በአንድ ልብ እንቁም እንጂ ቤቷ..ሳሎኗ ሙሉ ነው።
በተለያዩ አበቦች ያጌጠ መስክ እንዴት ያለ ግሩም መልክ እንዳለው ለሁላችንም ግልጽ እውነታ ነው፡፡ የብሄር ብሄረሰብ ጽንሰ ሃሳብም እንደዚሁ ውበቱ ሀገርና ሕዝብ ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ በአንድ ዛፍ ላይ ያሉ የተለያዩ ቅርንጫፎች እንደሚያፈሩት አበባና ፍሬ ብሄር ብሄረሰቦችም ለሀገር እንደአበባውና ፍሬው ናቸው፡፡ ዛፉ አንድ ነው ቅርንጫፉ ግን ብዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ናት የብሄር ብሄረሰብ ስብጥሩ ግን የበዛ ነው፡፡
ተስፋዎቿ አብበው ሰላሳና ስልሳ መቶም ያማረ ፍሬ እንዲያፈሩ በህብረብሄራዊነታችን ስር ያለው የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህላችን መቀጠል አለበት፡፡ ለየትኛውም ሀገርና ሕዝብ ብዙሀነት በረከት እንጂ መርገምት የለውም። ለዛም ነው በብዙ ሃሳብና ፍላጎት ውስጥ በአንድነቷ የምትደነቅን ሀገር ይዘን የዘለቅነው። አሁናዊ የትርክት ተረቶቻችን ብዙሀነት የፈጠራቸው ሳይሆኑ በመነጋገር ማመንን ወደጎን ማለት ያመጣብን ጣጣ ነው፡፡ የትኛውም ቀዳዳ በምክክር የሚደፈን ነው፡፡ የትኛውም አባጣና ጎርባጣ በመተሳሰብ የሚቀና ነው፡፡
ተስፋ የአንድነት ቀለም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተስፋ የእኛ አንድነት ነው፡፡ የሀገራችን ቀና ማለት የእኛ ወንድማማችነት ነው፡፡ ያለን ነገር ከኢትዮጵያዊነታችን አይበልጥም፡፡ ለልጆቻችን ልናወርስ የምንችለው ትልቁ የሰውነት ውርስ በብዙሀነት ውስጥ አብሮነትን የማስቀጠል ጥበብን ነው፡፡ ፍቅርን አግንነን፣ አብሮነትን አስበልጠን እንደ አብረሃምና ሎጥ እኛ ወንድማማቾች ነን ልንባባል ይገባል፡፡ በዚህ ሃሳብ እና እውነት ውስጥ ነው ዋጋና ክብር የሚኖረን፡፡
ሰው በሀገር ሲጠራና ሀገር በሰው ስትጠራ አንድ አይነት አይደለም፡፡ ሰው በሀገር ሲጠራ እዛ ጋር ሙሉ መሆን ይጀምራል፡፡ ሰው ስሙን፣ እምነቱን፣ ክብሩን፣ ማንነቱን ሀገሩ ሲያደርግ ስልጣኔና ዘመናዊነት ዋጅተውታል እንላለን፡፡ ሰው በሀገሩ ሲጠራ የዜግነት ግዴታውን እየተወጣ ነው፡፡ ሀገር በሰው ስትጠራ ግን ብዙ ጊዜ ልክ አይመጣም፡፡
ብሄራችንን ታከን፣ የብቻ ታሪካችንን ተንተርሰን ሀገራችንን በእኛ ስንጠራ እዛጋ ስህተት እየሠራን ነው፡፡ በመሠረቱ ሰው በሀገር እንጂ ሀገር በሰው ተጠርታ አታውቅም፡፡ እናም መጠሪያ ስማችንን ከእኔነት ወደእኛነት፣ ከግለኝነትና ቡድን ወደብዙሀነት በመቀየር የህብረብሄራዊነት እድላችንን ወደ ድል መቀየር እንችላለን፡፡
ብዙ መልክ አንድ ስም የኢትዮጵዊነት የታሪክ መነሻ ነው፡፡ ብዙ ነን..ሰማንያ እና ከዛ በላይ ብሄረሰቦች፡፡ እልፍ ነን..የበዛንና የተትረፈረፍን..ይሄ ሁሉ የሃሳብና የኑባሬ ውህደት በሀገርና ሕዝብ ላይ የሚንጸባረቅ ነው፡፡ መልካም ሃሳብ መልካም ታሪክ መፍጠሪያ ነው፡፡ ለፍቅር እንጂ ለጠብ መቧደን አያምርብንም፡፡ በፍቅር ስም ለአንድነት በአንድነት ተቧድነን የጋራ ታሪክ ጽፈን ፊተኞች ተብለናል፡፡ ያን ደማቅ እድልና ድል ለመመለስ ለጥላቻ የተዘረጉ እጆቻችን፣ ለጠብ ያሞጠሞጡ አፎቻችን ፍቅርን መስበክ አለባቸው፡፡
አንዳንዶቻችን በሀገራችን የምንጠራ ነን አንዳንዶቻችን ደግሞ ሀገራችንን በማንነታችን የምንጠራ ነን፡፡ የሚልቀው እውነት ሰው በሀገሩ ሲጠራ የሚለው እውነት ነው፡፡ ከሀገር የቀደመ ነገር ሁሉ የውድቀት ምንጭ ነው፡፡ ከሕዝብ የበረታ ነገር ሁሉ መድረሻው ምንምነት ነው። ሀገር የሚያቆመው፣ አንድነት የሚፈጥረው ከሀገር ያልቀደመው ነገር ነው፡፡ እርሱ የሥልጣኔ መጀመሪያ ነው፡፡ ከሀገር የቀደመ ነገር እንዳይኖራችሁ ተጠንቀቁ፡፡
ሰው ራሱንም ሆነ ብሄሩን፣ ታሪኩንም ሆነ ምንነቱን ከሀገሩ ሲያስቀድም ያኔ ባለውለታነቱ ያበቃል፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን እስከዛሬ ድረስ በሥልጣኔና በታሪክ፣ በባህልና በወንድማማችነት ከፍ ብላ የታየችው ሀገራቸውን ባስቀደሙ ብሄር ብሄረሰቦች ነው፡፡ ዛሬም ካሉብን ወደፊትም ከሚኖሩብን ሀገራዊ ትርክቶችና ተረት ወለድ ጥላቻዎች እንላቀቅ ዘንድ ሀገሩን ያስቀደመ፣ ወገኑን ከፊት ያደረገ ፖለቲከና ፖለቲከኛ ያስፈልገናል፡፡
ብዙ ነን.. ከራሳችን አልፈን ለሌሎች የምንተርፍ፡፡ ብዙ ነን ጥበብን፣ ታሪክን፣ ጀግንነትን አጣምረን የያዝን፡፡ ልዩነታችን ውስጥ ብዙ የአንድነት መንፈስ፣ ብዙ የህብረብሄራዊነት ጌጦች አሉ፡፡ ልዩነታችን ውስጥ ሀገር የሚያሻግር፣ ትውልድ የሚቀርጽ የታሪክና የሥርዓት ጀብደኝነት አለ፡፡ ብዙሀነታችን ውስጥ እኛነትን የሚያወሳ፣ ግለኝነትን የሚኮንን የሥርዓትና የጨዋነት ልማድ አለ፡፡ እኛ ዝም ብለን ሀገርና ሕዝብ አልሆንም። ሌሎችን ባቀናና ባነቃ ባህልና ሥርዓት እሴትና ልማድ ውስጥ ሀገርና ሕዝብ የሆንን ነን፡፡
በልዩነታችን ብናጌጥ፣ በብዙሀነታችን ብንቆም ዓለምን የሚያስፈራ የሃይልና የለውጥ ባለቤቶች እንሆን ነበር፡፡ በወንድማማችነት ብንሰለፍ እንደጥንቱ ዘመን ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ብርሃን መሆን የምንችል ነበርን። ለመበርታት በፍቅርና በአብሮነት ለመቆም ያሉንን ግን ደግሞ መለስ ብለን ያላየናቸውንና ዋጋ ያልሰጠናቸውን ጸጋዎቻችንን መጠቀም አለብን። በእኔነት ያደበዘዝናቸውን የወንድማማችነት እሴቶቻችንን የመጪው ዘመን የትንሳኤ ማብሰሪያ እንዲሆኑን እንግለጣቸው፡፡
ሀገር መቼም አንድ አይነት ሆና አታውቅም..የአለም ታሪክ በመለያየት ውስጥ፣ በመደባለቅ ውስጥ የቆመ ነው፡፡ አንድ አይነት ብሄር፣ አንድ አይነት ባህል፣ አንድ አይነት ቋንቋ፣ አንድ አይነት ታሪክና ሥርዓት ያላት ሀገር የለችም፡፡ ሁሉም የዓለም ሀገራት በድብልቅልቅ ብሄርና ቋንቋ፣ በልዩ ልዩ ባህልና ወግ የተሰባጠረ ነው፡፡ ውበት ማለት በልዩ ልዩ ባህሎች መድመቅ ነው፡፡ ሥልጣኔ ማለት የብዙሀነትን ሃሳብና ፍላጎት በሠለጠነ መንገድ ማራመድ ነው፡፡ ዘመናዊነት ማለት በዚህ ልዩ ልዩ ባህልና ወግ መድመቅና መዋብ ነው፡፡
ልዩነት ጌጥ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ብዙ ሀገራት አሁናዊ ሥልጣኔአቸውን፣ አሁናዊ ልዕለ ሃያልነታቸውን ያገኙት ህብረብሄራዊነታቸውን ተጠቅመው ነው፡፡ መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም ሀገራት በህብረ ብሄራዊነት ስብጥር ውስጥ የቆሙ ናቸው፡፡ ተፈጥሮ ብዙሀነትን ካደለቻቸው ጥቂት ሀገራት መካከል ደግሞ በዋናነት እኛ ኢትዮጵያውያን እንጠቀሳለን፡፡ ልዩነት ውበት ነው.. በልዩ ልዩ ባህልና ወግ፣ ሥርዓትና ታሪክ መከበብ መታደል ነው፡፡ ይሄን ተፈጥሮ ያደለንን የብዙሀነት ልዩነታችንን በአግባቡ በመጠቀም ሀገራችንን ማሻገር ይኖርብናል፡፡
ለነውጥ ሳይሆን ለለውጥ፣ ለመገፋፋት ሳይሆን ለመተቃቀፍ ልንጠቀመው ግድ ይለናል። ለመለያየት ሳይሆን ለአንድነት፣ ለመራራቅ ሳይሆን ለመቀራረብ ልናውለው ይገባል፡፡ ልዩነት ከተጠቀምንበት ለውጥ ካልተጠቀምንበት ነውጥ ነው፡፡ ከተጠቀምንበት ወደሥልጣኔና ወደ ከፍታ ልንወጣጣበት እንችላለን፡፡ ካልተጠቀምንበት ደግሞ በልዩነታችን ቀዳዳ ውስጥ አፍራሽ አስተሳሰቦችን እያስገባን ልንበላላበት እንችላለን። መቼም የትም ልዩነት ጉድለት ሆኖ አያውቅም፡፡ ልዩነት ጌጥ ነው..ሀገር የምታምርበት፣ ትውልድ የሚቆነጅበት፣ ታሪክ የሚያብብበት ሥፍራ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ሲበረበር አንድ አይነት ግን ደግሞ ልዩ ውበትና ደም ግባት ይገኝበታል፡፡ ውበታችን በልዩነታችን ውስጥ ያካበትነው ባህልና፣ ልማድ፣ ወግና ሥርዓታችን ነው፡፡ ውበታችን በልዩነታችን ውስጥ ያገኘነው ፍቅርና መከባበር፣ መዋደድና መቻቻላችን ነው፡፡ ውበታችን በልዩነታችን ውስጥ የተወራረስነው የአብሮነት መንፈስ ነው፡፡ ውበታችን በብዙሀነታችን ውስጥ ማግረን ያቆምነው፣ አቁመን ያጸናነው ኢትዮጵያ የሚለው የጋራ ስማችን ነው፡፡ አንድ አይነት ውበት የለውም፡፡ ውበት ያለው በልዩነት ውስጥ ነው፡፡
በእኔና በእናንተ ልዩ መሆን ኢትዮጵያ ሀገራችን ሙሽራ ናት፡፡ ዛሬ ላይ በዚህ ልክ ባለታሪክ የሆንነው በልዩ ልዩ ትውፊታችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተሠራችው ከእያንዳንዳችን ባህልና ወግ፣ ሥርዓትና ታሪክ በተዋጣ ሃሳብ፣ በተዋጣ ጽናት፣ በተዋጣ እውቀት፣ በተዋጣ ገንዘብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን በዚህ ልክ የቆነጀችው በእያንዳንዳችን ብዙሀነት ተከባ ነው። መብዛታችን..የተለያየ መሆናችን የተለየችውን ሀገራችንን ፈጥሯታል፡፡ እናም ልዩነታችን ውበታችን ነው አልኩ፡፡
ኢትዮጵያን ካስጌጡ ጌጦች ውስጥ ሌላም ሊጠቀስ የሚችል እውነት አለ እርሱም አንድነታችን ነው፡፡ ከብዙሀነታችን ውስጥ በተወለደ አንድነታችን ከትናንት እስከዛሬ ብዙ ድሎች በጋራ አጣጥመናል፡፡ በልዩነታችን ውስጥ በተዋጡ የአብሮነት መንፈሶች ብዙ ተግዳሮቶችን በጋራ አልፈናል፡፡ አሁንም በልዩነታችን ውስጥ ያለውን አድነታችንን ለሀገር ክብር የምናውልበት ትክከለኛ ጊዜ ላይ ነን፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከፊቷ ብዙ ተስፋዎች አሏት፡፡ እኚህ ተስፋዎቿ እውን እንዲሆኑ የእኛ በአንድነት መቆም ዋጋ አለው፡፡
የሀገራችን ትንሳኤ እንዲመጣ፣ ጨለማዋ እንዲነጋ ሰላም ያለበት፣ ምክክር ያለበት፣ ፍቅር ያለበት፣ አንድነት ያለበት፣ ፈርሀ እግዚአብሄር ያለበት አብሮነት ያስፈልገናል፡፡ ሀገር በዜጎቿ የምትሠራ ናት፡፡ እኛ ደግሞ ሀገር ለመሥራት የሚሆን ብዙ ጥበብ ብዙ ማስተዋል ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ ከራሳችን አልፈን አፍሪካን የሠራን ሕዝቦች ነን፡፡ እጆቻችን ከእኛ ርቀው ለመላው ጥቁር ሕዝብ ባለውለታ ናቸው፡፡ እናም በአንድነት ከቆምን፣ ልዩነቶቻችንን አቻችለን መጓዝ ከቻልን አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ለመሥራት በቂዎች ነን፡፡
በብሄር የተለያየን ነን፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በባህል የተለያየን ነን፡፡ ይሄ ሁሉ ልዩነታችን ግን ኢትዮጵያ በሚል የጋራ መጠሪያ ታስሯል፡፡ እናም እንዲህ እላለሁ..እንኳንም ልዩ ሆንን..እንኳንም ተለያየን፡፡ እንዲህ ያማርነው ስለተለያየን ነው..ኢትዮጵያ በሚል የጋራ ስም የታሰርነው ልዩዎች ስለሆነን ነው፡፡ በተፈጥሮ እውነት በብዙ ልዩነት ውስጥ አንድ ነን፡፡ በብዙ አንድነት ውስጥ ልዩ ነን፡፡ ይቺን ነው ኢትዮጵያ የምላችሁ፡፡ ይቺን ነው ሀገሬ የምላት፡፡
በድብልቅ ውህደት ኢትዮጵያዊ ተብለናል። ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ፍልጥ የታሰረባት ገመድ ናት፡፡ ልጡ በአንድ ላይ አስሮናል፡፡ ልጡ ቢፈታ ፍልጡ ይበታተናል፡፡ ልጡ ቢላላ ፍልጡ ይመሳቀላል፡፡ እናም በኢትዮጵያዊነት ስምና ገመድ ነው እንዳንበታተን ሆነን የታሰርነው። ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ነው..በልዩነት ውስጥ ጸንቶ የቆመ፣ በልዩነት ውስጥ ጠብቆ የተገመደ..ማንም የማያላላው ስጋና ደም፡፡ የታሰርንበት የአንድነት ልጥ፣ የታሰርንበት የወንድማማችነት ገመድ እንዳይፈታ ልዩነታችንን ማክበር መቻል ይኖርብናል፡፡ የታሰርንበት የኢትዮጵያዊነት ገመድ፣ የተያዝንበት የመቻቻል ልጥ እንዳይላላ ልዩነታችንን እንደውበት አምነን መቀበል ይኖርብናል፡፡
ብዙሀነት ለሀገር ያለው ሁለንተናዊ ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በብዙ ነገር የተባረክን ሕዝቦች ነን፡፡ በእያንዳንዱ ብሄር ውስጥ ለሀገር የሚሆን ብዙ ነገር አለ፡፡ ያ ብዙ ነገር የሀገርን ቀዳዳ፣ የማህበረሰቡን ችግር የመፍታት አቅም አለው፡፡ ችግሮቻችን እንዲበልጡን እድል ካልሠጠናቸው በስተቀር አይበልጡንም። በዚህም በዚያም የምንሰማቸው ብሄር ተኮር እኩይ አስተሳሰቦች ሀገራዊ ችግር ከመፍጠር ባለፈ ጥቅም ስለሌላቸው ብዙሀነታችንን ለለውጥ መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ችግር ፈቺ አስተሳሰብ ይዘን የለውጥና የመፍትሄ አካል መሆን እንጂ በልዩነታችን ውስጥ ሰርገን እየገባን በምንፈጠራቸው ጥቃቅን የልዩነት በሽታዎች ወደ ፊት መሄድ አንችልም፡፡
ተስፋዎቻችን ያሉት መዳፋችን ውስጥ ነው። ከፍታዎቻችን በእያንዳንዳችን ጫንቃ ላይ የተቀመጡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሲባል አቤት የምንለው በጋራ ከሆነ በችግሯ ጊዜም በጋራ መቆም ይኖርብናል፡፡ ሕዝቦቿ በጋራ ያልቆሙባት ሀገር ታሪክ አይኖራትም፡፡ ታሪክ የሚፈጠረው ከአንድነት አብራክ ውስጥ ነው፡፡ የዓድዋ ታሪክ የመላው ኢትዮጵያዊ ታሪክ ነው፡፡ የዓድዋ ታሪክ የብሄር ብሄረሰብ ታሪክ ነው፡፡ የህዳሴ ግድባችን ብሄር ብሄረሰቦች በአንድነት ያቆሙት የጋራ ሀውልታቸው ነው፡፡
እናም በኢትዮጵያዊነት ገመድ እንዳንፈታ ሆነን ታስረናል፡፡ ልዩነታችን እንድንደምቅበት የተሰጠን እንጂ እንድንደበዝዝ የተሰጠን እንዳይደለ በማመን ለአንድ ዓላማ በአንድ እንቁም፡፡ ባለን አቅም ሁሉ በአንድ አቅፋ ለያዘችን ሀገራችን የምንለፋበት፣ የምንደክምበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ የሚጠቅመን ፍቅርና አብሮነት ብቻ ነው፡፡ ሀገራችንን የጋራ መጠሪያችን አድርገን ለትንሳኤዋ ብርሃን መሆን ይጠበቅብናል፡፡ የሀገራችን ትንሳኤ የእኛ ትንሳኤ ነው..ትንሳኤዋ እውን የሚሆነው ደግሞ በእኛ አብሮነት ነው፡፡ አብሮነታችን ሃይላችን ነው። ሃይላችን ደግሞ ከድህነት መውጫችን ነው፡፡ በልዩነታችን ተውበን፣ በብዙሃነታችን ደምቀን የሀገራችንን ትንሳኤ እውን እናድርግ ማብቂያዬ ነው፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን እሁድ ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም