ባለ ብዙ ፋይዳው በዓል

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ነገ በአዲሱ የደቡብ ክልል አርባምንጭ ከተማ በደማቅ ሥነሥርዓት ይከበራል:: ቀኑ እንደ ሀገር ሲከበር የዘንድሮው ለ19ኛ ጊዜ ነው:: በየዓመቱ በአደባባይና በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሥነሥርዓት የሚከበረው ይህ በዓል፣ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በባሕላዊ አልባሳቶታቸው፣ ዜማዎቻቸው፣ ውዝዋዜያዎቻቸው፣ ወዘተ… ደምቀው የሚታዩበት ነው::

በዓሉ በአደባባይ የሚከበር ከመሆኑ በተጓዳኝ ሲምፖዚየሞች፣ ስፖርታዊ ውድድሮችና የመሳሰሉት ሌሎች መርሐ ግብሮችም ይካሄዱበታል:: በዚህም ውይይቶች ይደረጋሉ፤ መልዕክቶች ይተላለፋሉ:: በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባሮች ላይም የጋራ ግንዛቤ ይያዛል::

ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት ያደረጉትን ተጋድሎ ተከትሎ እውን የተደረገው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የፀደቀበት ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓመተ ምሕረት የሚታወስበትን ይህን በዓል፣ የበዓሉ ባለቤቶች ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገመንግሥቱ ባስገኘላቸው ትሩፋት መሠረት ራሳቸውን ማስተዳደር፣ በራሳቸው ቋንቋ መማር መዳኘት፣ መተዳደር ያስቻላቸው መሆኑን በማሰብ፣ እንዲሁም የበይ ተመልካች ከመሆን ላወጣቸው ለእዚህ ታላቅ ቀን ትልቅ ስፍራ በመስጠት በድምቀት ያከብሩታል::

የአደባባይ በዓሉ በራሱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን በአንድ ቦታ ማገናኘት በማስቻል ይበልጥ እንዲታወቁ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፤ የአደባባዩ ዝግጅት ግን ቅምሻ ሊባል የሚችል ነው፤ ሙሉ ባሕሉን የማያሳይ እንደመሆኑ በዚህ መነሻ ተደርጎ ማኅበረሰቦቹ ያሉበት ቦታ ድረስ ዘልቆ በመሄድ ጊዜ ሰጥቶ ኢትዮጵያውያንን በሚገባ ለማወቅም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል::

በዓሉ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሙሉ በአንድ ታላቅ መድረክ የሚገናኙበት ነው:: በዚህ ታላቅ በዓል ላይ የማይታደም ብሔር ወይም ብሔረሰብ አይኖርም:: ኢትዮጵያዊ መልክ በሚገባ ይታይበታል ብሎ መናገር ያስችላል::

በቀበሌ በወረዳ በክፍለ ከተማ ወይም በዞን እያለ እንደ ሀገር የሚከበረው ይህ በዓል፣ በተቋማት ደረጃ በተለይ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ሲያከብሩት ቆይተዋል:: ይህም በዓሉ ከሳምንት ላነሰ ጊዜ እንዲከበር አድርጎታል:: እንደ ሀገር በዓሉ በሚከበርበት ከተማና ክልል ደግሞ አከባበሩ ይበልጥ ደማቅና ሰፊ ሲሆን፣ አቀባበሉ ቆይታውና ሽኝቱ ማንነትን ከማሳየት ባለፈ የኢትዮጵያውያንን ትስስር ለማጎልበት ትልቅ መሣሪያ በመሆን ላይ ይገኛል::

በዓሎቹ ሰፋፊ ሲምፖዚየሞች የሚካሄዱባቸው እንደመሆናቸው ከሕገመንግሥቱ በፊት የነበረውን የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ታሪክ ከሕገመንግሥቱ መምጣት በኋላ ያለውን ሁኔታ በሚገባ ሲያስቃኙ ቆይተዋል:: ይህ ብቻም ሳይሆን በቀጣይ በሀገር ግንባታ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚናም አመላክተዋል::

ለዓመታት በተካሄዱ በእነዚህ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሕሎችን የተመለከቱ ሲምፖዚየሞች ላይ ጥናታዊ ሥራዎች ወይም የውይይት መነሻ ጽሑፎች እየተዘጋጁ ውይይቶች ሲደረጉ ቆይተዋል:: የባሕል ዘርፉን የሚመራው አካል እነዚህን ሥራዎች በመሰነድ በኩል ምን ያህል እየሠራ ስለመሆኑ መረጃው ባይኖረኝም መድረኮቹ ለሥራው በእጅጉ የሚያስፈልጉ መረጃዎች የሚመረቱባቸው ስለመሆናቸው ግን መናገር ይቻላል::

ውይይቶቹ ማንነቶቹ እንዲጠበቁ፣ ይበልጥ ወጥተው እንዲታዩ ማድረግ ያስቻሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ አንድነታቸውን ይበልጥ እንዲያስተሳስሩም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ

መድረኮች ሆነው እንዲያገለግሉም እየተደረገ ነው::

በመድረኮቹ የቀረቡ ጥናታዊ ሥራዎችና የተካሄዱ ውይይቶችን የተመለከቱ ሰነዶች በሚገባ ተደራጅተው እንደ ቤተመጽሐፍት ባሉ ስፍራዎች ይቀመጣሉ ብዬ አስባለሁ:: ይህ መሆኑ ለቀጣይ ተመሳሳይ ጥናትና ምርምር ሥራዎች መነሻ ወይም ግብዓት በመሆን እንዲያገለግሉ ይጠቅማል:: እንደ ማመሳከሪያ ሰነዶች /ሪፈረንስ/ ሊያገለግሉ ይችላል::

እነዚህ ማኅበረሰቦች ማንነትና ማንነታቸውን ጠብቀው ራሳቸውንና ሀገራቸውን ከፍ ለማድረግ እያከናወኑ ያሉትን ጥረት ለመቃኘትም ያስችላሉ:: ይህን ሥራ በተለይ የበዓሉ ባለቤት የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚገባ ይሠራበታል ብዬም አስባለሁ፤ በዚህ ላይ ክልሎች እንዲሁም ዞኖች ዩኒቨርሲቲዎችም ጭምር ሊሠራበት ይገባል::

ይህን በዓል ለዓለም በሚገባ በማስተዋወቅ እንደሌሎች ባሕላዊ ቅርሶች ወይም የቱሪስት መዳረሻዎች ቱሪስቶች በስፋት የሚጎበኙት በዓል እንዲሆን ማድረግ ላይም መሠራት ይኖርበታል:: ቱሪስቶች እያንዳንዱን ብሔረሰብና አኗኗሩን በየቀዬው እየሄዱ መጎብኘታቸው እንዳለ ሆኖ ሁሉም ባሕል በአንድ ስፍራ ተሰባስቦ መገኘቱን እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ስለሚችሉም ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሠራበት መልካም ይሆናል::

አዘጋጅ ከተሞች ብቻም ሳይሆኑ ወደ ከተሞቹ በሚወሰዱ ጎዳናዎች የሚገኙ ከተሞችና አካባቢዎች የሚጎበኙበትን ዕድልም በዓሉ ሰፊ አድርጎታል:: የበዓሉ ተሳታፊዎች ጎብኚዎችም ናቸው:: ከተሞችም ከተሞቻቸውን እምቅ ሀብቶቻቸውን በማስጎብኘትና በማስተዋወቅ ልማታቸውን ለማፋጠኑ ተግባር ሊያውሉት ይገባል::

በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው ከየክልሎቹ የተውጣጣ ሕዝብ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል፣ ወዘተ ከፍተኛ አመራሮች፣ ወዘተ ናቸው በዓሉ በዋናነት ወደሚከበርባቸው ስፍራዎች የሚያቀኑት:: ይህ ሁሉ ማኅበረሰብ በዓል አክብሮ ብቻ የሚመለስ አይደለም:: ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት አካባቢውን ይጎበኛል፤ አካባቢውን የሚገልፁ ቁሳቁስ ይገዛል፤ እናም የበዓሉ ትሩፋት ብዙና ብዙ ነው፤፤

ይህን ውብ ኅብረብሔራዊነት በተለያዩ በዓላት ወቅት የምናገኘው ቢመስልም በዚህ መልኩ ማግኘት የሚቻለው በየዓመቱ በሚከበረው በዚህ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል እንደመሆኑ የኅብረብሔራዊነት ቀለምን በማስተዋወቅ ላይ ቢሠራ ተጠቃሚው ብዙ ነው፤፤ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሕላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር በሚገባ ይተዋወቅላቸዋል:: ቱሪስቶች በዝግጅቱ ዘና ከማለታቸው በተጨማሪ ለተጨማሪ ጥናትና ምርምር እንዲመጡ እድል የሚከፍትላቸውም ይሆናል::

የዘንድሮን ጨምሮ ለ19 ዓመታት በዓሉን ለማክበር በየክልሉ ከተሞች የተደረጉ ጉዞዎችና ቆይታዎች የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ማንነት በሚገባ ለማወቅ ከማስቻላቸውም በላይ ዝግጅቶቹ በየከተሞቹ ለተደረጉ የመሠረተ ልማት ለውጦች ያበረከቱት አስተዋፅዖም ሊነገርለት ይገባል:: በክልሎች የተገነቡ ግዙፍ ስታዲየሞች አንዱ ምክንያት ይሄው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ስለመሆኑ ይታወቃል:: ይህን ምክንያት በማድረግ ከተሞች ከፍ ባለደረጃ እየታደሱ፣ እየፀዱ፣ ወዘተ ያለበት ሁኔታም እንዲሁ የበዓሉ አዘጋጅ ሆኖ መገኘት እንዲናፈቅ ያደርገዋል::

የዘንድሮው 19ኛ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልም ብዙ የተደከመበት፣ ብዙ የሚጠበቅበት እንደሆነ ይታመናል:: የበዓሉ አዘጋጅ አርባምንጭ ከተማ በዓሉን ለማስተናገድ ስትሰናዳ ቆይታ እነሆ እንግዶቿን እየተቀበለች ትገኛለች:: ዛሬ በዋዜማውም እንግዶች የመቀበሉ ሁኔታ የሚቀጥል ሲሆን፣ የተለያዩ መርሐ ግብሮች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል:: መልካም በዓል ብለናል!

እስመለዓለም

አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You