*ለ‹አረንጓዴ አሻራ› መርህ ግብር ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፡– በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ይፋ የተደረገው የአራት ቢሊዮን ችግኝ መትከል መርሃግብር ወደ ትግበራ የተገባው አራት ነጥብ አራት ቢሊዮን ችግኝ መኖሩ ተረጋግጦ መሆኑ ተገለጸ። የዚሁ መርሃግብር አካል የሆነው ‹አረንጓዴ አሻራ› በሚል መርህ ሐምሌ 22 ቀን ለተያዘው እቅድም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተገለጸ።
በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጋሻው እና በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ላቀው አበጀ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤በጠቅላይ ሚኒስትር ይፋ የተደረገውና በመተግበር ላይ የሚገኘው የአራት ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ሂደት በመተግበር ላይ ሲሆን፣ ለዚህም ችግኝ በመቅረብ ላይ ይገኛል። በተለይ በሐምሌ 22 ቀን በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ‹አረንጓዴ አሻራ› በሚል መርህ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፤ የችግኝ ጉድጓድ ቁፋሮውም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
አቶ ተስፋዬ እንደገለፁት፤ በክልሎች ለችግኝ ተከላው የቦታ ዝግጅት ሲሰራ ቆይቷል። እንዲሁም የችግኝ መጠንንም የማቅረብ፣ ወደተከላ ቦታ የማድረስና ጉድጓድ የማዘጋጀት ሥራዎች እየተካሄዱ ናቸው።
እስካለፈው አርብ ድረስ የነበረው ሪፖርት የኦሮሚያ ክልል ወደ ግማሽ ቢሊዮን ሄክታር መሬት ላይ አንድ ቢሊዮን አካባቢ ችግኝ መትከሉን ለማወቅ መቻሉን አቶ ተስፋዬ ጠቅሰው፣ኦሮሚያ ክልል አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ችግኝ ማለትም እንደ አገር ከተያዘው ግብ 50 በመቶ ያህሉን ወስዶ በመስራት ላይም ያለ ክልል መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ተስፋዬ እንዳሉት፤ የአራት ቢሊዮን ችግኝ ተከላው ከመጀመሩ በፊት ወደ አራት ነጥብ አራት ቢሊዮን ችግኝ አካባቢ መኖሩ ተረጋግጧል።እነዚህ ችግኞች የሚገኙትም በመንግሥት እጅ ማለትም በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ተጠሪ ተቋማት፣ በክልሎች፣ በግብርና ሚኒስቴርና በክልሎች፣ በግል ሴክተር እንዲሁም በአርሶ አደሮች እጅ ነው።
የዚሁ እቅድ አካል የሆነው ደግሞ በሐምሌ 22ቀን በአንድ ቀን 200ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ‹አረንጓዴ አሻራ› በሚል መርህ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ይህ መርሃ ግብር ደግሞ ልዩ የሚያደርገው ብዙ ሕዝብ በማንቀሳቀስ ብዙ ችግኝ በአንድ ቀን መተክል እንደሆነ አስታውቀዋል።በዚህም ምናልባትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን ለማሻሻል ታልሞ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ከተያዘው የአራት ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል የሚተከለው ወደ ሦስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን አካባቢ ነው። እንደ አገር የሚተከለው ችግኝ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከሞላ ጎደል ይሸፍናል ተብሎ ይታሰባል። ተከላው የሚካሄደው ለእርሻ ቦታ ያልሆኑና የተራቆቱ የሚባሉ መሬቶች ላይ ነው። በነፍስ ወከፍ 40 ችግኝ የሚተከል ሲሆን፣ ይህም መትከል ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ለፍሬ እስኪበቃ የመንከባከብ ሥራ አብሮ በኃላፊነት የሚወሰድበት ነው።
አቶ ተስፋዬ፣«ለመርሃግብሩ የተያዘው በጀት ከተለያዩ አካላት የሚገኝ ሲሆን፣ ወደ 60 በመቶ ያህሉ ከሕዝብ ይሆናል። ይህም በጉልበት አሊያም በገንዘብም ሊሆን ይችላል። ከልማት አጋሮች 20 በመቶ ሲሆን፣ መንግሥት ደግሞ 20 በመቶ ይችላል ተብሎ ነው በስትራቴጂው ላይ የተያዘው» ሲሉ ተናግረዋል። የዘንድሮው የችግኝ ተከላው አገር በቀል ዛፎችን መተከልን እንደሚያበረታታም አብራርተዋል።
አቶ ላቀው በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ከተሞች አጠቃላይ 760 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ መያዙን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በጥቅሉ 2ሺ56 ከተሞች መኖራቸውንም ጠቅሰው፤ ከተማ ሲባል ደግሞ 50 በመቶ ያህሉን በንግድ የሚተዳደሩትን እንደሚጨምርና በተለይ ደግሞ ማዘጋጃ ቤትን መስርተው የሚንቀሳቀሱትን እንደሆነ አመልክተዋል።
እንደ አቶ ላቀው ገለፃ፤ በከተማው የሚተከሉ የዛፍ ዓይነቶች ሙያዊ እገዛ እየተደረገላቸው ነው። መሆን ያለበት ከአየር ንብረቱና ከመልክዓምድራዊ አቀማመጥ ጋር መጣጣም የሚችል የዛፍ ዓይነት ነው። ይህም በጋራ የሚሰራ ሲሆን፣ በክልሎችም ሥራው በመጠናከር ላይ ይገኛል።
ሁሉም ክልሎች ምን ያህል ችግኞች እንደሚተክሉም ግንዛቤው ስላላቸው ዝግጅቶቻቸውን በማጠናከር ላይ ይገኛሉ። በተለይ የሐምሌ 22ቱ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃግብርን በተመለከተ እያንዳንዱ ከተማ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ነው።
ለችግኝ ተከላው በአገር አቀፍ ደረጃ ተነሳሽነቱን የወሰዱት የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ትምህርት ሚኒስቴር ናቸው። እንደ አገርም ተቀናጅተው በማስፈፀም ላይ እንዳሉ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2011
አስቴር ኤልያስ