አዲስ አበባ፡- በክረምቱ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህር ቤቶችን መልሶ ለማደስ 150 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት በዘንድሮ የክረምት መርሃ ግብር በትምህርት ዘርፉ በርካታ ስራዎች የሚሰሩ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ በከተማዋ የሚገኙ ሁሉንም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ማደስ ይገኝበታል።
እንደ ምክትል ሃላፊው ገለፃ በዚሁ የክረምት መርሃግብር ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛና የመሰናዶ ትምህር ቤቶች ድረስ ያሉ 488 የከተማዋ ትምህርት ቤቶች ይታደሳሉ። ለዚሁ እድሳት ማከናወኛም ትምህርት ቢሮ 150 ሚሊዮን ብር በጀት በመያዝ ከከተማው የኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር ስምምነት አድርጓል።
በከተማው ኮንስትራክሽን ቢሮ በኩል በእድሳትና ጥገና፣ በኤሌክትሪክ ኢንስታሌሽን፣ በግቢ ማስዋብና የአጥር ስራ አራት ኮዶች ተከፋፍሏል ያሉት ምክትል ሃላፊው በነዚህ ኮዶች ውስጥ በተለቀቀው በጀት ስራዎች የሚከናወኑ ይሆናል። በአሁኑ ወቅትም የዋጋ ዝርዝር መግለጫ እየተሰራ ሲሆን ይህ እንዳለቀ በእያንዳንዱ ትምህርት የሚሰሩ ስራዎች ተለይተው ይከናወናሉ።
በእድሳቱ ሂደት ትምህርት ቤቶቹን የማዘጋጀት፣ የሰው ሃይላቸውን የማንቀሳቀስ ተግባር የትምህት ቢሮ ስራ እንደሆነም ምክትል ሃላፊው ገልጸው፤ የተቋራጭነት የማማከርና የግንባታ አስተዳደርን በሚመለከት ደግም የከተማው ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊነት መውሰዱን ጠቁመዋል።
በዚህ አጭር ግዜ ውስጥም ማጭበርበር የሌለበትና ጥራቱን የጠበቀ ስራ ለመስራት ታቅዷል የ2012 ዓም የትምህርት ዘመን ከመጀመሩ በፊትም የእድሳት ስራው ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ምክትል ሃላፊው ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚገኙ የመንግስት ትምሀርት ቤቶችን በራሱ አቅም እንደሚያድስ ከሳምንት በፊት የገለፀ ሲሆን በእድሳት ሂደቱ የግል ባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ የአሰራር ስርት በትምህርት ቢሮ በኩል መዘርጋቱ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2011
አስናቀ ፀጋዬ