አሜሪካዊው ባለሀብት እንዴት ተገደለ ?

የኒውዮርክ ፖሊስ የጤና ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ግድያ በተመለከተ ተጠርጣሪ ያለውን አንድ ጭምብል ያላደረገ ግለሰብ ሁለት ፎቶዎችን አውጥቷል። የዩናይትድ ሄልዝኬር ኃላፊው ብሪያን ቶምፕሰን ህዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም ማንሃተን ከሚገኘው ሂልተን ሆቴል ውጭ ጀርባው ላይ በጥይት ተመትቶ ህይወቱ አልፏል።

ገዳዩ የቶምፕሰንን ንብረት ሳይወስድ ከቦታው ሸሽቷል። ሟች አስቀድሞ በተደረገ ዕቅድ ዒላማ መሆኑን ፖሊስ ያምናል። መርማሪዎች ተጠርጣሪውን ለመከታተል ፊትን ለይቶ የሚያሳውቅ ቴክኖሎጂ እና በጥይቶቹ ላይ በምስጢር የተፃፉ መልዕክቶችን ተጠቅመው እየመረመሩ ነው። የግድያውን ምክንያት እስካሁን ይፋ አላደረጉም።

ጥቃቱ የተፈፀመው ጠዋት 1፡00 ሰዓት ገደማ በታይምስ ስኩዌር እና በሴንትራል ፓርክ አቅራቢያ በሚገኘው ማንሃተን ውስጥ ነው። ቶምፕሰን በዕለቱ በባለሀብቶች ኮንፈረንስ ላይ ተገኝቶ ንግግር እንዲያደርግ ቀጠሮ ተይዞለት ነበር። እንደ ፖሊስ ገለጻ ከሆነ፤ ተጠርጣሪው ጥቁር የፊት ጭንብል እና ቡናማ ወይም ክሬም ቀለም ያለው ጃኬት ለብሶ ቶምፕሰን ንግግር ያደርግበታል ተብሎ በሚጠበቅበት ሂልተን ሆቴል ደጃፍ ለአምስት ደቂቃ ያህል የጠበቀው ይመስላል።

በእግሩ በቦታው የደረሰው ቶምፕሰን ጀርባው እና እግሩ በጥይት ተመትቶ በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል ከደረሰ ከግማሽ ሰዓት በኋላ ህይወቱ ማለፉ ተነግሯል። የተጠርጣሪው መሳሪያ አልተኩስ ያለ ቢመስልም በፍጥነት አስተካክሎ መተኮስ መቀጠል መቻሉን የኒውዮርክ ፖሊስ ዲፓርትመንት (ኤንዋይፒዲ) የመርማሪዎች ዋና አዛዥ ጆሴፍ ኬኒ ገልጸዋል።

ከደህንነት ካሜራ ቀረጻዎች እንደተገኘ ተንቀሳቃሽ ምስል ከሆነ፤ ገዳዩ ሽጉጡ ላይ ድምጽ ማፈኛ እንደገጠመ የሚያሳይ ይመስላል ሲል ገልጿል። የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ ለኤምኤስኤንቢሲ እንደተናገሩት፤ ድምጽ ማፈኛ መጠቀም ታይቶ የማይታወቅ ነገር ነው። “ድምጽ ማፈኛ ከዚህ በፊት አይቼ አላውቅም። ይህ በእውነት ለሁላችንም አስደንጋጭ ነገር ነበር” ሲሉ የቀድሞው የኤንዋይፒዲ ባልደረባ ተናግረዋል።

መርማሪዎች ሽጉጡ ቢቲ ስቴሽን ስድስት 9 ነው ብለው እንደሚያምኑ ተዘግቧል። ይህ መሳሪያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዘመን የልዩ ዘመቻ ኃይሎች ይጠቀሙበት የነበረው የሽጉጥ አይነት ነው። ፖሊስ መሳሪያው የት እንደተገዛ ለማወቅ በኮነቲከት የሚገኙ የመሣሪያ መደብሮችን ጎብኝቷል ተብሏል። ከተኩሱ በኋላ ተጠርጣሪው በእግር ሲሸሽ በቪዲዮ ላይ ታይቷል። ባለስልጣናት ተጠርጣሪው የሊፍት ንብረት የሆነውን ኤሌክትሪክ ብስክሌት ተጠቅሟል የሚል እምነት መጀመሪያ ላይ ነበራቸው።

እስካሁን በቶምፕሰን ግድያ ዙሪያ የሚደረገው ምርመራ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመለየት ጥቂት ፍንጮች ላይ ብቻ ያተኮረ ሆኗል። ሐሙስ ዕለት ጭንብል ያላደረገ ግለሰብ ሁለት ፎቶዎችን ይፋ ያደረጉት ባለስልጠናት ኤንዋይፒዲ ከግድያው ጋር በተያያዘ “ለጥያቄ ይፈልገዋል” ብሏል።

የሕግ አስከባሪ ምንጮች ለሲቢኤስ እንደተናገሩት ከሆነ፤ ግለሰቡ በአካባቢው በሚገኝ ሆስቴል ውስጥ ለመግባት የሃሰተኛ መታወቂያ ተጠቅሟል ተብሎ ይታመናል። ጥቅም ላይ የዋለው ስም የእውነተኛ ሰው ነው ተብሎ አይታመንም። መርማሪዎች እንደሚያምኑት ግለሰቡ ከጥቃቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ከአትላንታ፣ ጆርጂያ ወደ ኒውዮርክ በአውቶቡስ እንደተጓዘ ስለምርመራው አጭር መግለጫ ያገኙ ግለሰብን ጠቅሶ ሲቢኤስ ዘግቧል። ግለሰቡ የአውቶቡስ ጉዞ መነሻው አትላንታ ይሁን መንገድ ላይ ይሳፈር ለጊዜው ግልጽ አይደለም።

ከተጠርጣሪው ጋር ተመሳሳይ አይነት ሰው ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም። ተጠርጣሪው ጥቃት ከማድረሱ ከደቂቃዎች በፊት በአቅራቢያው በሚገኝ ስታርባክስ ፎቶ መነሳቱን ፖሊስ ገልጿል። በምስሉ ላይ በጭንብል ቢሸፈንም ጭምብሉ በበቂ ሁኔታ ወደ ታች በመጎተቱ ዓይኖቹ እና የአፍንጫው ክፍል እንደሚታዩ የፖሊስ ምንጮች ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

ምስሉን ተጠቅመው መርማሪዎች በፊት መለያ ሶፍትዌር ማንነቱን ለመለየት እየሞከሩ ነው። ምንም እንኳን ገዳዩ የቶምፕሰንን ንብረት ሳይወስድ ቢሸሽም መርማሪዎች እስካሁን ስለ ግድያው ምክንያት አላወቁም።ፖሊስ በቦታው የተገኙ ሦስት የጥይት ቀለሃዎችን እና ሦስት ጥይቶች ላይ ዲኤንኤ ምርመራ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። “መካድ”፣ “መከላከል” እና “ማስቀመጥ” የሚሉት ቃላት በቀለሃዎቹ ላይ ተገኝተዋል ሲሉ ሁለት የሕግ አስከባሪ ምንጮች ተናግረዋል።

በተጠርጣሪው ማምለጫ መንገድ ላይ ተንቀሳቃሽ ስልክ ተገኝቷል። ፖሊስ ስልኩን “እየመረመርኩ ነው” ብሏል። በተጠርጣሪው ተጥሏል ተብሎ የሚታመን የቡና ኩባያም ለጣት አሻራዎች ምርመራ በሚል ወደ ኤንዋይፒዲ ወንጀል ላብራቶሪ ተልኳል። ቀደም ሲል ግለሰቡ ሲገባበት በነበረው በማንሃታን አፐር ዌስት ሳይድ በሚገኝ ቦታ ላይ ፍተሻ መደረጉን መርማሪዎቹ ገልጸዋል።

ቦታው በፍሬድሪክ ዳግላስ የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክት አቅራቢያ ሲሆን፤ ተጠርጣሪው ወንጀሉ በተፈጸመበት ዕለት ጠዋት 11፡00 ሰዓት ላይ ከቤት ውጭ በደህንነት ካሜራዎች ታይቷል ተብሏል። ግድያው የተፈጸመበት ጎዳና አቅራቢያው በሚገኘው ማሪዮት ሆቴል የሚገኘውን የቶምፕሰን ክፍል እንደሚፈትሽ ፖሊስ ተናግሯል።

ቶምፕሰን በአውሮፓውያኑ 2004 ከፕራይስዋተርሃውስኮፐርስ የአካውንቲንግ ድርጅት የአሜሪካን ትልቁን የግል መድን ተቋም ወደ ሆነው ዩናይትድሄልዝ ተቀላቅሏል። የቶምፕሰን ባለቤት ከኤምኤስኤንቢሲ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፤ ቀደም ሲል አንዳንድ ዛቻዎች እንደነበሩ ተናግራለች። ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥባለች።

“እሱ ሲያስፈራሩት የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንዳሉ መናገሩን አውቃለሁ” ብላለች። በቶምፕሰን የትውልድ ከተማ ማፕል ግሮቭ፣ ሚኒሶታ በ2018 በቤቱ አንድ አጠራጣሪ ክስተት ነበር ሲል ፖሊስ መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You