•500 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ይሸፈናል
ደብረ ብርሃን፡– የዞኑ ህዝብ ላቀረበው የሰላምና ደህንነት ጥያቄዎች ህዝብ ማዕከል ያደረገ ምላሽ ከመስጠት ጎን ለጎን ለልማት ስራዎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አስታወቁ።
ምክትል አስተዳዳሪው አቶ ብርሃኑ ታዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለይ እንደተናገሩት፤ ከህብረተሰቡ ጋር በተደረጉ የውይይት መድረኮች ህዝቡ ባነሣው ጥያቄ መሰረት የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥና ከልማቱ ተቋዳሽ ለማድረግ በስፋት እየተሰራበት ነው።
ሰላምን ለማረጋገጥና ህዝቡ የልማት ተቋዳሽ ለማድረግ 10 ቁልፍ ተግባራት መለየታቸውን የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፤ ከአስሩ ተግባራት መካከል የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የጸጥታ መዋቅሩ የሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ፤ ሁሉም የአካባቢው የህብረተሰብ ክፍሎች የልማት እንቅስቃሴዎችን ሳያቋርጥ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮችን በባለቤትነት ይዞ እንዲንቀሳቀስ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የሁሉም ወረዳዎች መዋቅሮች የሰላምና ደህንነት ጉዳዮችን ከልማት ጋር አስተሳስረው እያስኬዱት መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግሮችን ለመቅረፍ በሁሉም ወረዳዎች ስራ እድል ፈጠራ ተግባራት ያሉበትን ሁኔታ የመለየት ስራ ተሰርተዋል ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ የስራ እድል ፈጠራ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተሰምሮበት ወደ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል።
እንደ አቶ ብርሃኑ ማብራሪያ፤ የኑሮ ውድነት ለመቅረፍም የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶች ተነድፈው ወደ ትግባራ ተገብቷል። በአጭር ጊዜ ችግሩን ለማቃለል የመሰረታዊ ፍጆታዎች አቅርቦት በስፋት ካሉባቸው አካባቢዎች እጥረት ወዳሉባቸው አካባቢዎች እንዲሄድ እየተደረገ ነው። ለእጥረት መንስኤ እየሆነ ያለውን ህገ ወጥ ንግድና የሸቀጥ መከማቸትን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው። በረጅም ጊዜ ችግሩን ለማቃለል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በ2012 የምርት ዘመን 500 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን 16 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ግብ የተቀመጠ ሲሆን፤ ምርትና ምርታማነት አምና ከነበረበት በአማካይ በሄክታር 32 ኩንታል ወደ 33 ኩንታል በሄክታር ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ለዚህም አምና የነበረውን መልካም ተግባራት ለማስቀጠልና ድክመቶችን ለማረም እየተሰራ ነው። ለአርሶ አደሮቹ ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎች እየቀረቡ ነው።
የአረንጓዴ ልማት ስራ በዞኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰሩ ካሉ ስራዎች አንዱ መሆኑን ያብራሩት ምክትል አስተዳዳሪው፤ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር በሁሉም ወረዳዎች የችግኝ ተከላ ስራ በመከናወን ላይ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ብርሃኑ ማብራሪያ፤ ግብር ለአካባቢውና ለሀገር ልማትና ሰላም ወሳኝ በመሆኑ የግብር አሰባሰብ ስራው በትኩረት እየተሰራ ነው። ከሀምሌ 1 ጀምሮ እስከ ሀምሌ ሰባት 33 በመቶ የሚሆኑ የደረጃ“ሐ” ግብር ከፋዮች ግብር ከፍለው የንግድ ፈቃዳቸውንም አድሰዋል። ይህም ህብረተሰቡ መንግስት ዋስትናዬ ነው የሚል አስተሳሰብ ስለመያዙ ማሳያ ከመሆኑም ባሻገር ለሰላምም ወሳኝ ነው።
በሀገሪቱ የነበረው ሁኔታ በአካባቢው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ያስከተለው አሉታዊ ጫና የለም ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ የአካባቢው ህብረተሰብና የጸጥታ መዋቅሩ ለኢንቨስትመንቶች ልዩ ጥበቃ በማድረጉ ኢንቨስትመንቱ ላይ ያስከተለው ጫና የለም። የኢንቨስትመንቱን ፍሰት ለመጨመር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2011