ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከመጪው ጥር 11 ቀን 2017 ዓ.ም ከበዓለ ሲመታቸው በፊት ለጋዛው ጦርነት መፍትሄ ለመስጠት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተገልጿል፡፡ የዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ የጋዛን የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን መልቀቅ ስምምነት ላይ ለመምከር ወደ ኳታር እና እስራኤል መጓዛቸውን ሮይተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
በትራምፕ አስተዳደር የቀጣናው መልዕክተኛነት ስፍራን በይፋ የሚረከቡት ስቲቭ ዊትኮፍ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱራህማን አልታኒ ጋር ተወያይተዋል ነው የተባለው፡፡ ውይይቱ ኳታር ባለፈው ወር ከጋዛ አደራዳሪነት ራሷን ማግለሏን ካሳወቀች በኋላ ዳግም ወደ ድርድር ሚናው መመለሷን አመላካች መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የትራምፕ አስተዳደር የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ከቀጣናው መሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ፕሬዚዳንቱ ስልጣን ከያዙ በኋላ ጋዛን እና አካባቢውን ማረጋጋት ላይ እንዲያተኩሩ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከበዓለ ሲመቱ በፊት እንዲፈጸም ተስማምተዋል፡፡ የባይደን አስተዳደር የቀጣናው የትራምፕ መልዕክተኛ ከእስራኤል፣ ኳታር እና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር እየተወያዩ እንደሚገኙ እውቅናው እንዳለው ገልጾ፤ ጦርነቱን የሚያስቆሙ እና ታጋቾችን የሚያስመልሱ የትኛውንም አሜሪካ መር ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች እደግፋለሁ ብሏል፡፡
ሆኖም ተሰናባቹ እና አዲስ የሚተካው አስተዳደር በተኩስ አቁሙ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ያሰቡ አይመስሉም ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው፡፡ የትራምፕን ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በበጎ እንደሚመለከተው ያስታወቀው ሀማስ በበኩሉ፤ በዘመነ ትራምፕ በሚኖሩ የተኩስ አቁም ስምምነት ሂደቶች ዙሪያ ለመወያየት በቅርቡ አመራሮቹን ወደ ዶሃ እንደሚልክ አስታውቋል፡፡
ትራምፕ ከሰሞኑ “ታጋቾቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኜ ቢሮ ከምገባበት እኤአ ከጥር 20/ 2025 በፊት ካልተለቀቁ በመካከለኛው ምሥራቅ ከባድ ችግር ይፈጠራል ማለታቸውን ጠቅሶ አል ዐይን ዘግቧል፡፡
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም