
ዜና ትንታኔ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእ.ኤ.አ 2024 ምርጡ የአፍሪካ አየር መንገድ መሆኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ አየር መንገዶችን የሚገመግመው ስካይትራክስ ድርጅት በድረ ገጹ አሳውቋል፡፡ ይህንንም ሽልማት ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ማግኘቱን አመልክቷል። በዚሁ ዓመት አየር መንገዱ የአፍሪካ ምርጥ ቢዝነስ ክላስና ኢኮኖሚክ ክላስ እንዲሁም በአፍሪካ ለኢኮኖሚ ክላስ ተጓዦች ምርጥ የበረራ ላይ ምግብና መጠጥ አቅራቢነት በጥቅሉ አራት ሽልማቶችን አግኝቷል።
የአየር መንገዱ ለተከታታይ ዓመታት የከፍታ ማማውን አስጠብቆ የቀጠለውና ብዙ ሽልማቶችን ያገኘበት ምስጢር ምንድነው? አየር መንገዱ ስኬታማ መሆን ለሀገር ያለው ፋይዳ ምን ያህል ነው? ስንል የተለያዩ ምሁራንን አነጋግረናል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካይነት ኢትዮጵያ የምታገኛቸው ሽልማቶች ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ከመሆናቸውም ባሻገር እንደ ሀገር ታላቅ ኩራትም የሚሉት የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር መንገድ ሠራተኛ የሆኑት ኢንጂነር ሰለሞን ሁሉቃ፤ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያ ስም ይነሳ የነበረው ከድህነት ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡
ኢንጂነር ሰለሞን፤ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አደባባይ ሽልማት አገኘ ማለት ያገኘው አየር መንገዳችን ብቻ አይደለም፤ ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ራሷ ናት ይላሉ።
ሽልማቱ አየር መንገዳችን ትናንት በትጋትና በታታሪነት ባስመዘገበው ውጤት የመጣ ሲሆን፤ ለነገ ቱሪስቶችም ሆነ የተለያዩ መንገደኞች የኢትዮጵያን አየር መንገድ ምርጫቸው እንዲያደርጉ የሚጋብዝ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያን አየር መንገድ ብዙዎች ምርጫቸው አደረጉ ማለት ደግሞ ለኢትዮጵያ ገቢዋን የሚያሳድግ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ሌላው ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አምባሳር ጥሩነህ ዜና በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ ያገኘው ሽልማት በብዙ መንገድ የሚተረጎም መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢትዮጵያ እያበረከተ ያለው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡
አምባሳደር ጥሩነህ፤ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ውጤት እያሳየ ነው፡፡ ወደ ስምንት አስርት ዓመታት ያህል እድሜ ያስቆጠረ አየር መንገድ በአፍሪካ ውስጥ ምናልባት ከግብጽና ደቡብ አፍሪካ በስተቀር በወቅቱ ሌሎች ሀገሮች የራሳቸው አየር መንገድ አልነበራቸውም ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን ቀድመው የተመሰረቱ ሁለቱን ሀገራት ጨምሮ በአፍሪካ ካሉ አየር መንገዶች ሁሉ በልጦ እያንጸባረቀ ያለ ታላቅ አየር መንገድ መሆን ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሸለሙ ፋይዳ አንደኛ በገቢ ደረጃ ሲሰላ ለኢትዮጵያ የሚያስገኘው ገቢ ከፍተኛ ገንዘብ ነው፡፡ ይህም የሚሰላው በብዙ ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ከቱሪዝምም ሆነ ከሌላው ዘርፍ ከምታገኘው ገቢ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ በመሆኑ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡
ኢንጂነር ሰለሞን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስመ ጥር ሆነ ማለት የተለያዩ ሀገራት ተጓዦች በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲጠቀሙ ያደርጋል፡፡ አየር መንገዱ ተሸለመ ማለት ብዙዎቹ ተጓዦች በኢትዮጵያ አየር መንገድ እምነት እንዲያደርጉ አደረገ ማለት ነው ይላሉ፡፡
ተጓዦች የኢትዮጵያን አየር መንገድ ምርጫቸው የማድረጋቸው ምክንያት ሲገልጹም፤ ተጓዦች ምቾት ተሰምቷቸው እንዲጓዙ ስለሚፈልጉ ስመ ጥሩ የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተመራጭ ያደርጋሉ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ብዙዎች መረጡት ማለት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ሆነች ማለት ነውና በተዘዋዋሪ ገቢዋን ከፍ አደረገች እንደማለት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ኢንጂነሩ እንደሚሉት፤ አየር መንገዱ የኢትዮጵያውያን መገለጫ ብራንድ ነው፡፡ በመሆኑም በየመዳረሻው ኢትዮጵያን አስተዋዋቂና በኢትዮጵያ ላይ እምነት እንዲጣል ጉልህ ድርሻ አለው፡፡
አየር መንገዱ ለተከታታይ ጊዜ ለመሸለም ያበቃው ትልቁ ምክንያት በተቋሙ ከፍ ያለ ትብብር በመኖሩና ትልቅ መዋቅርም በመዘርጋቱ ነው ይላሉ። በመሆኑም አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ኩራት ነው ሲሉም ያመለክታሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ በተቋሙ ጥብቅ የሆነ የሥራ ባህል አለ፤ መንግሥት ሲቀያየር እንደሌሎቹ ተቋማት የሚለዋወጥ አይደለም፡፡ መንግሥት ተቀያየረ አልተቀያየረ ሥርዓቱ ሳይፋለስ ሥራውን በአግባቡና በእኔነት ስሜት የሚሠራ ተቋም በመሆኑ ወጥነት ያለው ነው፡፡ ምክንያቱም አየር መንገዱ በየሥርዓቱ የራሱን ጥንካሬ ይዞ እየተጓዘ ያለ ተቋም ነው፡፡
እንደ አየር መንገድ ተቋም አመርቂ ሥራ ሰርቶ ስመ ጥር ተቋም ለመሆንና ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆን የግድ ነው የሚሉት ኢንጂነር ሰለሞን፤ እንዲያውም በአየር መንገዱ የሚሰጥ ስልጠና እኔ ባለሁበት ተቋምም እንዲሰጥ ፍላጎት አለኝ ብለዋል። ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ በአየር መንገዱ ውስጥ የሚሰጡ ስልጠናዎች በአግባቡ ወስዶ ለቦታው ብቁ ሆኖ መገኘት የግድ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አምባሳደር ጥሩነህ፤ ልክ እንደ ኢንጂነሩ ሁሉ አየር መንገዱ የሚያስገኘው ገቢ ከፍ ማለቱ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ በከፍተኛ ደረጃ የሚያንጸባርቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ከአፍሪካ ሀገሮች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የሚነጻጸር የለም። አየር መንገዱ ሳያቋርጥ ለተከታታይ ዓመታት የሚሸለምና ትርፋማ እየሆነ የመጣ ነው፡፡ የአፍሪካ አየር መንገዶች የኢትዮጵያን ያህል ውጤታማ ሊሆኑ ቀርቶ ጥቂት ትርፍ ማምጣታቸው ብቻ እንደ ትልቅ ዜና የሚቆጠርላቸው መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያሰበ ያለውን እየተገበረ የሚገኝ ነው። ከሌሎች አየር መንገዶች ጋር በመተባበር፣ በመቀናጀትና ግማሹን ደግሞ በግዥ በመውሰድ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችን አየር መንገድ ለማስፋፋት ነው። ይህ ጥረቱ ደግሞ በጣም የሚያስገርም ነው ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
የአየር መንገዱ መሸለም ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ጎን ለጎን ሌላም ፋይዳ አለው ሲሉ ጠቅሰው፤ በተለይም መንግሥት የሚመራው ይህ ግዙፍ ተቋም ባስመዘገበው አመርቂ ውጤት ተከታታይ የሆነ ሽልማት ማግኘቱ ወደግል ይዛወር እያሉ የሚወተውቱትን የዓለም ባንክና ምዕራባውያኑን ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵ አየር መንገድ በመንግሥት እጅ የሚተዳደር ሆኖ በአፍሪካ ከዚያም አልፎ ከብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተወዳድሮ ብልጫ ያገኘ ተቋም መሆን ችሏል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ተቋሙን ያቋቋመው መንግሥት ሲሆን፤ ንብረትነቱም የመንግሥት በመሆኑ መንግሥት እንዲህ አይነት ውጤታማ ሥራ መሥራት አያስችለውም የሚለውን አባባል ሽልማቶቹ በይፋ ውድቅ ማድረጋቸውን ያስመሰከሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ መንግሥት እየመራ ያለው አየር መንገድ ውጤታማ ከመሆኑም ባሻገር የትኛውም አካል የመሰከረለት ስለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ስለሆነ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አምባሳደር ጥሩነህ እንዳሉት፤ አየር መንገዱ ብዙ ፈተናዎችን አልፎ እዚህ ደርሷል፡፡ ሌሎቹ እንደ እሱ ለምን ውጤታማ አልሆኑም ብሎ ማሰብም ጥሩ ነው፡፡ እንዴት አድርገን እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ አዋጭና ስመ ጥር መሆን እንችላለን ከተባለ ብዙ ርቆ መሔድ ሳያስፈልግ የኢትዮጵያውያን ኩራት ከሆነው አየር መንገድ ብዙ ነገር መማር ይቻላል፡፡ ፈለጉንም መከተል ሕዝብንም ሀገርንም በጣም ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከስምንት አስርት ዓመታት በፊት በአጼ ኃይለ ሥላሴ የተመሠረተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በፈጣን እድገቱ በአፍሪካ ስመ ጥር ነው፡፡ አየር መንገዱ አፍሪካን ከዓለም፤ ዓለምን ከአፍሪካ በማስተሳሰርም ስሙን ገንብቷል። ዋና መናኸሪያውን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ላይ አድርጎ፤ በቶጎ ሎሜ፣ በማላዊ ሊሎንፍዌ፣ በዛምቢያ ሉሳካ ተጨማሪ መናኸሪያዎችን ከፍቷል።
የአፍሪካን መንገደኞች እና ጭነቶችን በማጓጓዝ ከአህጉሪቱ የአየር ትራንስፖርት ገበያ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው አየር መንገዱ፤ ዘመናዊ በሆኑ አውሮፕላኖች በአምስት አህጉራት ከ150 በላይ ወደ ሆኑ መዳረሻዎቹ ይበራል።
የቦይንግ፣ የኤርባስ እና የቦምባርድኤር ምርት የሆኑ የተለያዩ አውሮፕላኖች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በአጠቃላይ 148 አውሮፕላኖችን በአየር ላይ በማሰማራት በአፍሪካ ውስጥ ተፎካካሪ የሌለው ለመሆን ችሏል። በየዓመቱ በቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪን ለሀገሪቱ ያስገኛል።
መረጃ ያጋሩን ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ፤ መንግሥት ሌሎቹን ተቋማት እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ጎልተው እንዲወጡ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ሌሎችም ተቋማትም ከአየር መንገዱ የስኬቱን ምስጢር መማር ይጠበቅባቸዋል፡፡
አየር መንገዱ አሁን ያለበት ሁኔታ ጥሩ ሲሆን፤ ወደፊት በራሱ ብራንድ መገለጥ የሚችልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንምና ያንን ግብ ለማሳካት በጀመረው ሂደት ይቀጥላል፡፡ የራሱንም አውሮፕላን የሚያመርትበት ስትራቴጂ ቀይሶ ውጤታማ እንድንሆን ውድድሩን ከወዲሁ ከፍ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ ምሁራኑ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2017 ዓ.ም