በኢትዮጵያ ከ600ሺህ በላይ ሰዎች ከኤች አይቪ ቫይረስ ጋር እንደሚኖሩ ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል። በዓመት ከሰባት ሺህ በላይ ሰዎች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንደሚሆኑ የጠቆመው መረጃው፤ በየዓመቱ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡ ይገልጻል።
በጤና ሚኒስቴር የኤችአይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጸሚ አቶ ፍቃዱ ያደታ እንደሚሉት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለይም ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍ የኤች አይቪ ቫይረስን ለመከላከል አራት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጠው እየሠራ ነው።
የመጀመሪያው ማንኛዋም እድሜዋ ከ15-49 የሆነች ሴት ስለ ኤች አይቪ ግንዛቤ እንዲኖራት ማስቻል ፣ ሁለተኛው ከእርግዝና በፊት ራሳቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ፣ ሶስተኛ ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ከተገኘ ወደ ፅንሱ እንዳይተላለፍ ክትትል እንድታደርግ ማስቻል እና አራተኛው ከወለዱ በኋላ ለእናትና ለልጁ ምን አይነት ጥንቃቄ መደረግ አለበት የሚል መሆኑን ያስረዳሉ።
ከጋብቻ በፊት መመርመር ዋነኛና ትልቁ ተግባር መሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስፈጻሚው፤ አብዛኞቹ እናቶች ኤች አይቪ ፖዘቲቭ መሆናቸውን የሚያውቁት በመጀመሪያ እርግዝና ላይ መሆኑን ይገልጻሉ። የዚህ ዋና ምክንያትም ከጋብቻ በፊት ተመርምሮ አለመጋባት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ብለዋል።
ይህንንም ለመከላከል ወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ላይ በግንዛቤ ማስጨበጫና በባህሪ ለውጥ ዙሪያ መስራት እንደሚገባ አመልክተው፤ ኤች አይቪ እንደጠፋ የሚቆጥሩና ከጋብቻ በፊት መመርመር ግዴታ እንዳልሆነ የሚገልጹ መኖራቸውን ጠቁመዋል። በበሽታው ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ቲክቶክን ጨምሮ የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። ከዛ ባሻገር የሃይማኖት ተቋማት ድጋፍም እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት መጋቢ ሰንበቱ ባሼ በበኩላቸው፤ በእኛ ስር ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ተጋቢዎች ለመጋባት ፍቃድ ሲጠይቁ እስከ ስድስት ወር ድረስ እናቆያቸዋለን ይላሉ። በዛ ወቅትም ኤች አይቪ ተመርምረው ውጤታቸውን እንዲያመጡ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ አሁን ላይ ሌሎች አጀንዳዎች እየበዙ ከመምጣታቸው አኳያ እንደ ከዚህ በፊቱ በጉዳዩ ላይ ንቃት የመፍጠሩ ነገር ግን በእኛም በኩል ተቀዛቅዟል ሲሉ ያስረዳሉ።
አዲስ ተጋቢዎችን በተመለከተ ግን ጥንቃቄ እናደርጋለን የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በስድስት ወር ቆይታቸው ከሚሰጣቸው ትምህርቶች አንዱ ስለኤች አይቪ መሆኑን ይጠቁማሉ። የእምነቱ አስተምህሮቱም ግንኙነት የሚፈቀደው በጋብቻ ውስጥ ብቻ እንደሆነም አንስተዋል። ሌሎች ተቋማትም የእኛን ተሞክሮ ቢወስዱና ቢሰሩበት የስርጭት መጠኑን መቀነስና አስቀድሞ መከላከል ያስችላል ብለዋል።
ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ሙሉ በሙሉ ቀርቷል በሚያስብል ሁኔታ ወደ ቤተክርስቲያኗ ለመጋባት የሚመጡ ሰዎች የምርመራ ወረቀት ስለመጠየቃቸው ሰምተው እንደማያውቁ የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መምህር የሆኑት መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ ናቸው።
እንደእርሳቸው ገለጻ፤ እንደከዚህ ቀደሙ በቤተክርስቲያኗ አስገዳጅ ተብሎ የኤች አይቪ የምርመራ ወረቀት እየተጠየቀ አይደለም። ይህም እንደሀገር ለበሽታው ከተሰጠው ትኩረት ጋር ተያያዥ እንደሆነ ይገልጻሉ። እንደ ድሮ በሬድዮና በቴሌቪዥን እንዲሁም በተለያዩ ክበባት በኤች አይ ቪ ዙሪያ የሚካሄዱ ፕሮግራሞች እንደሌሉ የገለጹት መምህሩ፤ አሁን ላይ ያለው ሁኔታ ግን በሽታው ጨርሶ ጠፍቷል የተባለ ያህል መሆኑን ያስረዳሉ።
የማህበረሰብ ጤናን በተመለከተ የሚካሄዱ ዘመቻዎች የአንድ ሰሞን ብቻ የማድረጉ ነገር ተገቢ እንዳልሆነም በመግለጽ፤ መንግሥትም ሆነ ሃይማኖት ሕዝብ ሲኖር ነውና የሚኖሩት ኤች አይ ቪ ላይ ብቻ ሳይሆን አሁን እየተስፋፉ የመጡትን ተላላፊ ያልሆኑ እንደልብ፣ ካንሰር፣ ስኳርና ደምግፊት የመሳሰሉ በሽታዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ነፃነት አለሙ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም