በፌዴራል መንግስትና በክልሎች ርብርብ ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ተፈናቃዮች መካከል 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑትን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡ ይህም አሀዝ ከጠቅላላው ተፈናቃይ 94 በመቶ ገደማ ነው፡፡ ቀሪዎቹን 130 ሺ ገደማ የሚሆኑትን ደግሞ በቅርቡ ለመመለስና ለማቋቋም ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡
መንግስት በቀጣይም የዜጎችን መጎሳቆል እና ግጭትን የማስቆም፣ እምቅ ግጭትን የማምከንና ዘላቂ ሰላም በማስፈን ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ለተፈናቃዮች ሰብአዊ እርዳታ በሚፈለገው መጠንና ወቅት እያደረሰ ፣ የመልሶ ማቋቋሙን ስራ በብቃት ለመወጣትም የተቻለው ሁሉ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዜጎችን በማፈናቀል እና ጥቃት በማድረስ የተጠረጠሩ አመራሮችንና የጸጥታ አካላትን ለህግ እያቀረበ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
ይህ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስኬት ተፈናቃዮችን ከጉስቁልና ፣ ከጤና ጠንቅ፣ ከጸጥታ ስጋት እና ከስነልቦና ችግር የሚታደግ ተግባር ነው፡፡ ወደ ግብርና ሰራቸው እንዲመለሱና በእርዳታ ላይ ተመስርቶ ከቆየው ህይወታቸው እንዲላቀቁም ያስችላል፡፡
የመመለሱ ስራ ከመኸር ወቅት በፊት መከናወኑም አርሶ አደሮቹን ከእርሻ ስራቸው ጋር ማገናኘት አስችሏል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው ችግር ሳቢያ ጦም ያደረ መሬት እንዲለማ የሚያስችል እንደመሆኑም የግብርናው ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
በዜጎች መፈናቀል ሳቢያ መላ ኢትዮጵያን ክፉኛ አዝነው አንደነበር ይታወቃል፡ ፡ የተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው መመለስ በዚህ ህዝብ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ቁስል እንዲያጠግ እና እንዲሽር ያደርጋል፡፡ ህዝብ በሰላምና በመረጋጋት ሕይወቱን እንዲመራም ያስችላል፡፡ ልማቱን ብቻ እንዲያስብም ያደርጋል፡፡
ሀገሪቱ ከመፈናቀል ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተበላሽቶ የነበረው ገጽታዋ እንዲጸዳም ያስችላል፡፡ በፈረንጆቹ 2018 ሀገሪቱ በሀገር ውስጥ መፈናቀል ሶሪያን አፍጋንስታንና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን በማስከተል ከዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዳ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የተፈናቃዮቹ መመለስ ይህ ገጽታዋ ትርጉም ባለው መልኩ እንዲቀየር ያደርጋል፡፡
ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የሚመለሱት የአካባቢው ሰላምና መረጋጋቱ ሲመለስ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ችግር እያለ እንዲመለሱ አይደረግም፡፡ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውም በአንድ ወቅት ደፍርሶ የነበረው የአካባቢያቸው ሰላምና መረጋጋት ወደቀድሞ ሁኔታው ለመመለሱ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡
በመንግስት ርብርብና በህዝቡ ድጋፍ የተገኘው ይህ ስኬት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ሀገሪቱ ወደ ሰላም እና መረጋጋት መምጣቷን የሚያመለክትና መንግስት ይበልጥ እየተጠናከረ ስለመምጣቱም ጠንካራ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው፡፡ ሀገሪቱ ከችግሩ አቅዳ እና ፋጥና መውጣት መቻሏም እንደ ትልቅ ስኬት ሊወሰድ ይገባል፡፡
ቀሪው ስራ ተፈናቃዮችን ማቋቋም ይሆናል፡፡ ተፈናቃይ ወደ ቀዬው ሲመለስ ቄዬውን እንጂ ምንም እንደማያገኝ ይታወቃል፡፡ እድሜውን ሙሉ ያጠራቀመውን ጥሪት ፣ እንስሳቱን ፣ የጓሮ አትክልቱን ፣ ወዘተ ያጣ ነው፡፡ ከግብርና ስራቸው ከአንድ ዓመትና ከዚያ በላይ ለሚሆን ጊዜ የራቁም ናቸው፡፡
መመለሱ አንድ ስኬት ሆኖ ይህን ህዝብ ወደ ቀድሞ ጥሪቱ ፣ ስነልቦናው ፣ ወዘተ እንዲመለስ የማድረግ ትልቅ ስራ ወደፊት ይጠብቃል፡፡ ለዚህም የመንግስትና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ከፍተኛ ይሆናል፡፡
አርሶ አደሩ እርሻውን በሚገባ እንዲከውን የእርሻ መሳሪያዎች፣ ግብአት እና የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ ምርቱን መሰብሰብ እስከሚጀመርም በቂ የምግብ እህል አቅርቦት ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ እስከ አዝመራ ስብሰባ ወቅት ድረስ ይሄው መቀጠል ይኖርበታል፡፡
አሁን ወቅቱ የዘር እንደመሆኑ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ አርሶ አደሩ ማሳውን በሚገባ አለስልሶ እንዲዘራ የግብርና ባለሙያዎች፣ የእርሻ መሳሪያዎች ድጋፍ በበቂ መልኩ ሊደረግ ይገባል፡፡ ግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በዚህ በኩል ከአርሶ አደሮቹ አጠገብ መሆን አለባቸው፡፡
የአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እና ማህበራዊ ትስስራቸው እንዲጠበቅ በትኩረት መስራትም ያስፈልጋል፡፡ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል ይበልጥ እንዲጎለብት ማድረግም ያስፈልጋል፡፡
ዜጎች አፈናቅለው ለእዚህ ችግር ዳርገዋል በሚል የተጠረጠሩ አካላትንም በቁጥጥር ስር ከማዋል ባሻገር ጉዳያቸውን በአፋጣኝ በማየት በጥፋታቸው ልክ ቅጣታቸውን እንዲያገኙና ሌላውም እንዲማርበት ማድረግ ይገባል፡፡
በዚህም የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ መስራት የግድ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ስኬቱን እንደ ስኬት በመያዝ ለሌላ ስኬት ርብርቡ ተጠናክሮ ሊዲቀጥል ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2011