• ሐምሌ 22 ቀን 100 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል
ደብረ ብርሃን፡- በአማራ ክልል በዚህ ክረምት ወራት 2 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተናገሩ፡፡ ሐምሌ 22 ቀን 100 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከልም ዝግጅት ተደርጓል፡፡
በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ከዞን እስከ ቀበሌ ያለው አመራር፣ ሙያተኞች እና የቀበሌው አርሶ አደሮች በአሳግርት ወረዳ ጎላ ቀበሌ ውዱ ተፋሰስ ትናንት ችግኝ ተክለዋል፡፡ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ማርቆስ ወንዴ እንደተናገሩት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተያዘው 4 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ 2 ቢሊዮን በክልሉ ለመትከል ታቅዷል፡፡ እስከ ሐምሌ 15 ድረስ ተከላውን ለመጨረስ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡
እስከ ባለፈው ሳምንት በአዊና ደቡብ ወሎ ዞኖች 400 እስከ 500 ሚሊዮን የሚሆኑ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ የሌሎች አካባቢዎች ምን ያህል ችግኝ እንደተተከለ መረጃ የማሰባሰብ ሥራው እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የውሸት ሪፖርት እንዳይጨመር ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
አንድ ነጥብ 6 ቢሊዮን ገደማ ችግኞች በየችግኝ ጣቢያዎችና በግለሰብ አርሶ አደሮች ተዘጋጅተዋል ያሉት አቶ ማርቆስ፤ በክልሉ የችግኝ ተከላ የንቅናቄ መድረኮችም እየተካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ከተያዘው ውስጥም 100 ሚሊዮኑን በክልሉ ለመትከልም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እንደ አቶ ማርቆስ ማብራሪያ ለችግኝ ተከላው ምቹ የሆኑ አካባቢዎች ተመርጠዋል፤ የመስኖ አውታር ያሉባቸው አካባቢዎች ከተመረጡት አካባቢዎች መካከል ናቸው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታቸው ከፍ ያሉ ችግኞች በብዛት እንዲተከሉ እየተደረገ ነው፡፡ በዋናነት ድርቅን የሚቋቋሙ እንዲሆኑ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡
እያንዳንዱ ችግኝ ከተተከለ በኋላ እንዴት ይጸድቃል የሚለውን በጂፒኤስ ኮርድኔት ክትትል ይደረጋል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ እያንዳንዱ ችግኝ በምን ሁኔታ ይገኛል የሚለው ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ ማረጋገጫው የሚሰጠው በተተከለው ልክ ሳይሆን በጸደቀው ልክ ይሆናል፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አልማዝ አፈራ እንደሚሉት፤ ችግኝ ከመትከል ባሻገር ለየትኛው አካባቢ ምን ዓይነት ችግኝ ተስማሚ ነው የሚለው ላይ ትኩረት መደረግ አለበት፡፡ ይህንን ተግባር የምርምር ተቋማት ማከናወን አለባቸው ብለዋል፡፡
ችግኞች ከተተከሉ በኋላም ከአርሶ አደሮቹ ባሻገር የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች እየተከታተሉ ችግኞቹን ለችግኞቹ ተገቢው እንክብካቤ እንዲደረግ ድጋፍና ክትትል ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ሀገር በቀል ችግኞችን አፍልቶ በማቅረብ ለችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ስኬታማነት የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን አሳግርት ወረዳ ጎላ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ወይዘሮ በለገ አማረ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አሁን የሚተከለው ችግኝ ለነገ የሚኖረውን ፋይዳ ስለሚያውቁ ያለማንም ጫና በችግኝ ተከላ ለመሳተፍ ወጥተዋል፡፡
በመንግሥት ከሚዘጋጁ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ባሻገር ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ በግላቸውም ችግኞችን እየተከሉ መሆናቸውን የተናገሩት ወይዘሮ በለገ፣ እስካሁን ድረስ ከ4 ሺህ እስከ 5 ሺክ የሚሆኑ መጽደቃቸውን አንስተዋል፡፡ ከሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ችግኞቹን እንደሚንከባከቡም አንስተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2011
መላኩ ኤሮሴ