ባለፉት ወራት በፌዴራልና በክልል አካላት የጋራ ጥረት ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ተፈናቃዮች መካከል አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑትን መንግሥት ወደቀያቸው መመለሱን በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተናግረዋል፡፡
የተፈናቃዮቹ ወደ ቀዬቸው መመለስ ለሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ከተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ የዘመመውን የአገሪቱን ገፅታ ለማቃናት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ምሁራን አመልክተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም ተባባሪ አካዳሚክ ዳይሬክተር ዶክተር ዮናስ አዳዬ፣ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት ከሶሪያ በልጣ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህም መፈናቀል ከብሔርተኝነትና ከጎሰኝነት የተነሳ እንደመጣ እና አብሮ የመኖር ባህልን የሚሸረሽር ክስተት እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
የተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው መመለስ ለአገሪቱ የገፅታ ግንባታ ትልቅ ሚና እንዳለው የሚናሩት ዶክተር ዮናስ፣ «በኢትዮጵያውያኑ መካከል መሠረታዊ ቅራኔ ስለአመኖሩም ለሌሎች አገሮች መልዕክት ያስተላልፋል፡፡» ብለዋል፡፡ «ኢትዮጵያውያኑን ሲያጣላቸው የነበረው ሦስተኛ ወገን መሆኑን፣ ሕዝቡ አሁንም ቢሆን የጠነከረ አብሮ መኖር የሚያስችል እሴት እንዳለው የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ጭምር እንዲረዳ ያደርጋል፡፡» ሲሉም ያብራራሉ፡፡
በዋናነት የተፈናቃዮቹ መመለስ ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰው፣ የአገሪቱን ገፅታ መልካም በማድረጉ በኩልም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡
ዶክተር ዮናስ እንደሚሉት፤የስደተኞች ዓለምአቀፍ ድርጅትን /አይ.ኦ.ኤም/ን ጨምሮ ሌሎች ተቋማትና የመገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈናቀለውን ሕዝብ ቁጥር ከፍ አድርገው ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ ተቋማቱ የተፈናቃዮችን ቁጥር የቱንም ያህል ከፍ ቢያደርጉት በአሁኑ ወቅት ይህን ያህል ተፈናቃዮች ወደቀዬቸው መመለሳቸው ትልቅ እርምጃ ነው፡፡
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተፈናቅለው በደሴ አካባቢ የነበሩትን ዜጎች ለመደገፍ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ በማስተባበር ከወር ደመወዛቸው እንዲቆርጡ ሲደረግ እንደነበር አስታውሰው፣ተፈናቃዮች ያደጉበትን፣ የወለዱበትንና ኩለው የዳሩበትን ስፍራ እንደዋዛ በስተርጅና ለቀው ሲወጡ አስቸጋሪ እና የሚያም መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ዶክተር አባተ፣«በአሁኑ ወቅት ብሔረተኝነቱ ገኖ ከብሔርም አልፎ ጎጥ ድረስ ወርዷል፡፡» ሲሉ ተናግረው፤ የተፈናቃዮቹ ወደ ቀዬቸው መመለስ ይህን ዓይነቱን ጎጠኝነት ለመቀነስ እንደሚረዳ ይጠቁማሉ፡፡
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ገለታ ገመቹ፤ መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰው፣ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን አግባብ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ሰላምና መረጋጋትን በተመለከተ ዋና መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው የሚሏቸውን አብነት ጠቅሰው ሲዘረዝሩ እንደተናሩት፤ የመጀመሪያው የአንድ ሰው ሰብዓዊ መብት ሲባል አንዱ የመኖር መብት ነው፡፡ ያንን ጉዳይ ለማረጋገጥ ደግሞ መንግሥት ግዴታ አለበት፡፡ ስለዚህ የተፈናቀሉት ወደቀያቸው ሲመለሱ
ይህንን የመኖር መብታቸውን ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ ይህም በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው መተማመንን ይጨምራል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የማህበረሰቡን ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑ ነው፡፡ ይህም የማህበረሰቡን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ያግዛል፡፡ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ሲመለሱ በአካባቢው ያለው ሰላም አስተማማኝ ከሆነ ጠንካራ የሆነውን ማህበራዊ ግንኙነት እንደገና ማደስ ተቻለ ማለት ነው፡፡
ይህ ደግሞ በማህበረሰቡ መካከል ያለውን መተማመን የሚጨምር ይሆናል፡፡ የእርስ በርስ ግንኙነቱ መረጋገጥ በጥቅሉ አገሪቱ ውስጥ ያለውን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ በጣም ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡
እንደ አቶ ገለታ ገለፃ፤ ሦስተኛውና በጣም ወሳኝ የሆነው ደግሞ ስለሰላምና መረጋጋት ሲወራ ሥርዓቱ ምን ይመስላል የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡ የውጭ የመገናኛ አውታሮች በኢትዮጵያ ስላለው መፈናቀል ሲያወሩ መፈናቀሉን ወደ ሦስት ሚሊዮን ያደርሱታል፡፡
ስለዚህ መንግሥት ውዝፉንም ሆነ ከለውጡ ማግስት አንስቶ የተፈናቀሉ ዜጎቹን ወደቀያቸው እንዲመለሱ ማድረጉ ሥርዓቱን ከማሻሻል አኳያ ትልቅ ሚና እንዳለውም ነው የሚናገሩት፡፡«ሥርዓቱ ከተስተካከለ ሰላምና መረጋጋት መጣ ማለት እንደሆነም ጠቅሰው፣የአገሪቱን ስም ከማቃናት አኳያም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ያመለክታሉ፡፡
በአፍሪካ ቀንድ የሰብዐዊ መብቶች ሊግ ዳይሬክተር አቶ ጋሩማ በቀለ የተፈናቃዮች ወደቀያቸው መመለስ ጉዳይ ለአገሪቱ ፖለቲካ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፣የአገሪቱ መረጋጋት ማሳያም አድርገው ነው የሚገልጹት፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት ግንባር ቀደም ከሚባሉ አገሮች ተርታ የምትመደብ እንደነበረች ያስታውሳሉ፤ የተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው መመለስ ይህን የሀገሪቱን ገጽታ እንደሚቀይረው በመጥቀስ የአቶ ገለታን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡
እንደ ዶክተር አባተ ገለፃ፤ መፈናቀል የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የሥነ ልቦናም ጫናም ጭምር እንደሚያስከትል መረዳቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ለመፈናቀሉ መንስኤ የሆነው የጥላቻ ትርክት በመብዛቱ ነው፡፡ ስለዚህ ጥላቻን በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ መሰራት ይኖርበታል፡፡መፈናቀሉ ከቀጠለ ግን አለመረጋጋት ይጠናከራል፡፡ ጦርነትና መገዳደል ይፈጠራል፡፡ አለመረጋጋት ደግሞ አገርን ያጠፋል፡፡
ዶክተር ዮናስም እንደ ዶክተር አባተ ሁሉ መፈናቀል ካለ ሰላም እንደማይኖር ነው የሚናገሩት፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ መፈናቀሉ ከተባባሰ የአገርን ገፅታ በእጅጉ ያበላሸዋል፡፡ መፈናቀል አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ከበሬታና አመኔታ ዝቅ እንዲል ያደርጋል፡፡
መፈናቀልና ግጭት ሲኖር መረጋጋት እንደማይኖር፣ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያበረታታ ሁኔታ እንደማይፈጠር ዶክተር ዮናስ ጠቅሰው፣ ጥላቻውና መገፋፋቱ ጊዜያዊ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህንንም ሕዝብ እንደሚረዳና ቀጣይ አብሮነቱ እንደማይሸረሸር እምነታቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
እኤአ በ2018 መጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት ሶርያን፣አፍጋኒስታንና ዴሞክራቲክ ኮንጎን በማስከተል አንደኛ ላይ መቀመጧን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2011 በጀት ዓመት አፈጻጸምን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ባለፈው የበጀት ዓመት ውዝፍ የመፈናቀል ችግሮችና በለውጡ ማግስት በተከሰቱ የመፈናቀሎች ችግሮች ላይ መንግሥት 2011 በጀት ዓመት ሰርቷል፡፡
ከለውጡ በፊት በተከሰተው ግጭት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡ ከለውጡ ጀምሮ ደግሞ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የተፈናቃዮች ቁጥር ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ያህል ደርሶ ነበር፡፡
ከእነዚህ ተፈናቃዮች ውስጥ 400ሺ ገደማ የሚሆኑት በአየር ንብረት፣ ለውጥ ምክንያት የተፈናቀሉ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአጠቃላይ ተፈናቃዮቹ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑትን ወደቄያቸው መመለስ የተቻለ ሲሆን፣ ቀሪዎቹን 130 ሺ ተፈናቃዮች ለመመለስ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ዶክተር ዮናስ እንደሚሉት፤ መፈናቀል ዳግም እንዳይከሰት መሰራት ይኖርበታል፡፡ የግጭት መነሻ የሆኑ ጉዳዮችንም በማጣራት ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ግድ ይላል፡፡ ጎን ለጎንም እርቅ ማካሄድ እና ይቅርታ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ይመለሳሉ ተብለው የሚጠበቁ ተፈናቃዮችን የመመለሱ ሂደትም የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ሰላምን በማረጋገጥ ከግጭት ትርፍ ፈላጊ ኃይሎችን ዓላማ ማኮላሸትም ያስፈልጋል፡፡
ዶክተር አባተም ሆኑ አቶ ጋሩማ እንደሚሉት፤ ሁከት የሚፈጥሩ አካላት ሕግ ሊያከብሩ ይገባል፡፡ ሚዲያውም ወገንተኛ መሆኑን ማቆም ይኖርበታል፡፡ የቀሩት ተፈናቃዮች እንዲመለሱ በሚደረገው ሂደት ጉዳይ ፈፃሚው መንግሥት ብቻ መሆን የለበትም፤ሌላውም የኅብረተሰብ ክፍል እገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ተፈናቃዮች ከተመለሱ በኋላም አስፈላጊውን ከማሟላት አኳያ ሊሰራበት እንደሚገባ ምሁራኑ ጠቅሰው፤ ይህም የመንግሥት ሥራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት፡፡
ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ባይመለሱና መፈናቀሉም ቢቀጥል ከፍተኛ ቀውስ ሊከተል ይችል እንደነበር የሚጠቅሱት ምሁራኑ፣ መልሶ ማቋቋም ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ መልሶ በማቋቋሙ ሥራም የማህበራዊ ትስስራቸው እንዲጎለብት ማድረግ በተለይ ማህበራዊ እሴቶችን ማጎልበት ግድ እንደሚልም ያብራራሉ፡፡ መፈናቀሉ ቢባባስ ግን የሚፈጠረው ሌላ ትኩሳት እንደሆነና የአገሪቱም ስም እንደሚጎድፍ ያስረዳሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2011
አስቴር ኤልያስ