የትምህርት ቤቱ ቀደምት የመማሪያ ክፍሎች እርጅና ተጫጭኗቸዋል፡፡ የሚፈርሱ የሚፈርሱ የሚመስሉ ክፍሎችም ይታያሉ፡፡ ይህን እርጅናቸውን የተመለከተ እንኳንስ ለመማሪያ ክፍልነት ይቅርና ለእንስሳት ማደሪያ እንኳን አይመኛቸውም፡፡ ለዚያውም በአዲስ አበባ ከተማ፡፡ ፀሐይና ዝናብ የተፈራረቀበት ግድግዳቸው ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡ ወለላቸው ተቦርቡሯል፤ ኮርኒስ እና ጣራቸው ክፉኛ ተጎድቷል፡፡
ትምህርት ቤቱ የዳግማዊ ምኒልክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ዕድሜ ጠገብ ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው፡፡ ከተገነባ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በርካታ ምሁራንን አፍርቷል፡፡ የተጓዘበትን ረጅም የዕድሜ ጅረት ያህል ግን በሁለት ሕንፃዎች ውስጥ ከሚገኙ የመማሪያ ክፍሎች ውጪ እርጅና በተጫጫናቸው ነባር ክፍሎቹ ሲያስተምር ቆይቷል፡፡
የትምህርት ቤቱ የመምህራን ልማት ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ አለማየሁ ነጋሽ እንደሚሉት፤ ትምህርት ቤቱ በየክረምቱ ትምህርት ቤት ሲዘጋ በራሱ አቅም እድሳት ያደርጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት አቅም ትምህርት ቤቶችን ለማደስ መታቀዱ ለቀጣዩ ዓመት ለተማሪዎች ምቹ አድርጎ ለመጠበቅ ያስችላል፡፡
አብዛኛዎቹ የመማሪያ ክፍሎች በእርጅና ምክንያት ተገቢውን የመማር ማስተማር ሥራ ለማከናወን እንዳላስቻሉ የሚናገሩት ምክትል ርዕሰ መምህሩ፣ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቤቶችን ለማደስ በገባው ቃል መሠረት በተለይ በጣም ያረጁ ክፍሎችን መልሶ የማደስ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ይጠቅሳሉ፡፡ የመብራት ገጠማ፣ የተማሪዎች የመጠጥ ውሃና የመፀዳጃ ቤት ግንባታም ከዚሁ ጎን ለጎን እንደሚከናወኑ ይጠቅሳሉ፡፡
የተማሪዎችን አጠቃላይ መረጃ ለከተማአስተዳደሩ በማቅረብም የደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተማሪዎች እንዲያገኙ እንደሚደረግም ይገልጻሉ፡፡
«ትምህርት ቤቶችን የማደሱ ተግባር በከተማ አስተዳደሩ ተነሳሽነት መደረጉ የሚበረታታ ነው» የሚሉት ምክትል ርዕሰ መምህሩ፣ በተለይ ለተማሪዎች ምቹ የመማር ማስተማር አካባቢ ከመፍጠር አኳያ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ነው የሚገልጹት፡፡ ባለሀብቶችን በማስተባበር በትምህርት ቤት ማደስ ሥራው ተሳታፊ እንዲሆኑ የማድረጉ ሥራ ይበልጥ እንዲለመድ ማድረግ በትምህርት ቤቶች የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚያስችልም ይጠቁማሉ፡፡
ቤተ መንግሥት ግቢ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኘው የኢትዮጵያ አንድነት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትም ረጅም ዕድሜ ካስቆጠሩ የከተማዋ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ የዚህም ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎች ተመሳሳይ ችግር ይታይባቸዋል፡፡
ጣራቸው የተበሳሱ፣ ግድግዳዎቻቸው የተቦደሱ፣ ወለላቸው የተቦረቦሩ የመማሪያ ክፍሎች ይታያሉ፡፡ ክፍሎቹን የተመለከተ ተማሪዎች በነዚህ ክፍሎች ውስጥ ይማራሉ ብሎ ለማመን ይቸገራል፡፡
የአዳራሽ ስያሜን የያዘው ነገር ግን አዳራሽ ለመባል የማይበቃው ሰፋ ያለው የትምህርት ቤቱ መሰብሰቢያ ክፍል ጣራ በስብሷል፤ ኮርኒሱም ተሸነቋቁሯል፡፡ በተበሳው ጣራ በኩል የሚወርደው ፍሳሽ ለወለሉም ተርፎ ክፉኛ ቦርቡሮታል፡፡
ከመማሪያ ክፍሎቹ በስተጀርባ የሚገኘው አነስተኛ ቤተ መጻሕፍትም ውስጡ በቅርቡ የታደሰ ቢመስልም፣ ውጪው እርጅና ከተጫጫናቸው ሌሎች ክፍሎች ብዙም አይለይም፡፡
የትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህሯ ወይዘሮ መርሐዊት ማሞ «ከትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጆች ውስጥ አንዱ የትምህርት ቤት መሻሻል መርሃግብር ነው» ይላሉ፡፡ ከመርሃ ግብሩ ውስጥ ዋነኛው ደግሞ ምቹ የትምህርት ቤት አካባቢ መፍጠር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቤቶችን ለማደስ የታሰበው እቅድ በበጎ የሚታይ መሆኑን በመግለጽ የአቶ አለማየሁን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡
በክረምት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ለትምህርት ቤቶች በጀት ቶሎ እንደማይለቀቅ ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም ትምህርት ቤቶችን አድሶ ለትምህርት ለማዘጋጀት ችግሮች ሲያጋጥሙ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ የደረሰበት ውሳኔ ትምህርት ቤቱን በአፋጣኝ ለመማር ማስተማር ሥራ ምቹና ዝግጁ ለማድረግ እንደሚያስችል ይገልጻሉ፡፡
ምክትል ርዕሰ መምህሯ እንደሚሉት፤ በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ መሠረት በተለይ እርጅና የደቆሰው የትምህርት ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ፈርሶ በአዲስ መልክ ይገነባል፡፡ የመማሪያ ክፍሎች የወለል ጥገናና የግድግዳ ቀለም እድሳት ሥራዎች
ይከናወናሉ፡፡ ለዚህም አሸናፊው ተቋራጭ በትምህርት ቤቱ ተገኝቶ የሥራ እቅድ ርክክብ አድርጓል፡፡ የእድሳት ሥራውም በተያዘው ሳምንት ይጀምራል፡፡
እድሳቱ ለተማሪዎች ምቹ የመማር ማስተማር አካባቢን ይፈጥራል፡፡ በተማሪዎች የውጤት መሻሻል ላይም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የምገባ ፕሮግራምና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ በራሱ ለማድረግ መወሰኑም ተማሪዎች ለትምህርት የበለጠ እንዲነሳሱ ይገፋፋቸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በክረምት መርሃግብር በትምህርት ዘርፉ በተለይ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ የከተማውን አመራሮች ባሳተፈ መልኩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡
ከነዚህ ተግባራት ውስጥ አንዱ በከተማዋ የሚገኙ ሁሉንም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ማደስ ሲሆን፣ ትምህርት ቤቶቹ ወጥነት እንዲኖራቸውና ተማሪዎች ለትምህርት ዝግጁ እንዲሆኑ የአጥር፣ የምድረ ግቢ ማስዋብ፣ የኤሌክትሪክና የመማሪያ ክፍሎች ጥገናና የቀለም ቅብ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ ለዚህም ከከተማው ከኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር ስምምነት ተደርጓል፡፡
የእድሳት ሂደቱ በመንግሥት በጀት፣ በባለድርሻ አካላትና ለጋሽ ድርጅቶች እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል ያሉት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፣ የመንግሥትም ሆነ የሕዝብ ሀብት ለዚሁ ሥራ የሚውልበት አሠራርም መዘርጋቱን ይጠቁማሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ከእድሳቱ በተጓዳኝ ተማሪዎች በአዲስ መንፈስ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ ከቅድመ መደበኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ላሉ ለሁሉም ተማሪዎች የደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ምግብ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎችም ከተማ አስተዳደሩ ሙሉ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
«ትምህርት ቤቶችን የማደስና የመጠገን ሥራ ከዚህ በፊት ትምህርት ቢሮው በተደጋጋሚ የሚያቀርበው ጥያቄ ነበር» የሚሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ የከንቲባው ጽሕፈት ቤት በራሱ ተነሳሽነት ይህን ተግባር ለመፈፀም መወሰኑ ሊበረታታ የሚገባው ተግባር እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት አብዛኛው የከተማው በጀት ወደ ትምህርት እንዲዞር መደረጉም ትልቅ እምርታ እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡
ምክትል ቢሮ ኃላፊው እንደሚሉት፤ ትምህርት ቤቶቹን የማደስ ተግባሩን ትምህርት ቢሮውና የከተማው ኮንስትራክሽን ቢሮ በበላይነት ይመሩታል፡፡ ሁሉም የከተማዋ አመራሮችም ሥራውን በቅርበት ይከታተሉታል፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥም ማጭበርበር የሌለውና ጥራቱን የጠበቀ ሥራ በመስራት የ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከመጀመሩ በፊት የትምህርት ቤቶቹ ዕድሳት ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2011
አስናቀ ፀጋዬ