አዲስ አበባ፡- ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ በደረሰ ጥቃት የተሰዉ አመራሮችን ቦታ ክፍተት ለመሙላት የተደረገው ምርጫ የአማራን ሕዝብ ካጋጠሙት ችግሮችና ክስተቶች በማውጣት ወደተሻለ ደረጃ እንደሚያሻግር ተገለጸ፡፡ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድርነት በዕጩነት፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ደግሞ ለአዴፓ ምክትል ሊቀመንበርነት ተመርጠዋል፡፡
የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ
እንደገለጹት፣ የአመራር ማሟላት ሥራው በማዕከላዊ ኮሚቴው በተካሄደ ምስጢራዊ ምርጫ መሠረት ዕጩ ርዕሰ መስተዳድርና የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ተመርጠዋል፡፡
በጥቃቱ በተሰዉት እና የአዴፓ እና የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚዎች በነበሩት የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንን እና የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ ምትክ አቶ ተመስገን ጥሩነህን እና አቶ አገኘሁ ተሻገርን የመተካት ሥራ እንደተሰራም አቶ አብርሃም ገልጸዋል፡፡ የተተኩት አመራሮች በፌዴራልና በክልል ደረጃ በተለያየ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉና የዳበረ ልምድና እውቀት ያላቸው መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ወደኃላፊነት የመጡት አመራሮች አዴፓን በማጠናከር በኩልም ትልቅ ድርሻ እንደሚኖራቸው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድርነት በዕጩነት እንዲቀርቡ መወሰኑን የገለፁት አቶ አብርሃም፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ደግሞ የአዴፓ ምክትል ሊቀ-መንበር ሆነው መመረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡
ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድርነት በዕጩነት የቀረቡት አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ አሁን በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
አቶ ተመስገን ከዚህ በፊት በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ በሀገር መከላከያ ሠራዊት መረጃ ዋና መምሪያ፣ ኤሌክትሮኒክስ መምሪያ እና ቴክኒካል መረጃ መምሪያ ሰርተዋል፤ እስከ ሻለቅነት ማዕረግም ደርሰው ነበር፡፡
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መስራች አመራር ሆነው ሰርተዋል፡፡ በዚህም ከመምሪያ ኃላፊነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነት ተቋሙን መርተዋል፡፡
አቶ ተመስገን ጥሩነህ በአማራ ክልል የርዕሰ-መስተዳድሩ የፀጥታ እና ቴክኖሎጂ አማካሪ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ባለሥልጣን ም/ሥራ አስኪያጅ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሁም
የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነውም ሰርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2011
ድልነሳ ምንውየለት