. በክልሉ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲያብብ እንደሚሰራ ተጠቆመ
አዳማ፡- ጨፌ ኦሮሚያ ለክልሉ የ2012 በጀት ዓመት ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ፡፡ ጨፌው ከ 2 ቢሊዮን 183 ሚሊዮን በላይ ብር ተጨማሪ በጀትም አጽድቋል፡፡ የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅና ዴሞክራሲ እንዲያብብ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡
በአዳማ ከተማ ገልማ አባገዳ ከትናንት በስቲያ የተጀመረው አምስተኛው የጨፌ ኦሮሚያ አራተኛ የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ትናንት የክልሉን የ2012 በጀት ዓመት 70 ቢሊዮን 159 ሚሊዮን 637 ሺ 142 ብር በጀት አጽድቋል፡፡
ከጸደቀው ጠቅላላ በጀትም ለተዘዋዋሪ ፈንድ 14 ቢሊዮን 933 ሚሊዮን 874 ሺ 550 ብር ፣ ለክልል ካፒታል በጀት ደግሞ 17 ቢሊዮን 292 ሚሊዮን 417 ሺ 149 ብር እንዲሁም ለወረዳና ለከተማ አስተዳደር ድጋፍ 37 ቢሊዮን 433 ሚሊዮን 345 ሺ 443 ብር በተጨማሪም ለመጠባበቂያ በጀት 500 ሚሊዮን ብር የሚውል ነው፡፡
በተያያዘ ዜና ጉባኤው በትናንትና ውሎው ጨፌ ኦሮሚያ የኦዲትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2011 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2012 በጀት ዓመት እቅድን ጨምሮ በሌሎችም ሪፖርቶች ላይ ተወያይቷል፡፡
የኦሮሚያ ዋና ኦዲተር አቶ ኤሌማ ቃምፖ ለጨፌው ባቀረቡት ሪፖርት እንዳስታወቁት፤ በበጀት ዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ተገቢ ያልሆነ ክፍያ መፈፀሙንና መሰብሰብ የነበረበት ወደ 224 ሚሊዮን ብር አልተሰበሰበም፡፡
ከክልሉ ስፋት አንፃር ኦዲት ማድረግ የተቻለው ከ828 መስሪያ ቤቶች 474ቱን ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው፣የኦዲቱ ሽፋኑን ከ70 በመቶ በላይ ማድረስ እንዳልተቻለም ተናግረዋል፡፡ በ2012 በጀት ዓመት የውስጥ አቅምን በማሳደግና የውጭ ኦዲተሮችንም በማሳተፍ ወደ 540 መስሪያ ቤቶችን ኦዲት ለማድረግ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
የጨፌው ጉባኤ ከትናንት በስቲያ በተጀመረበት ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተጠናቀቀውን 2011 በጀት ዓመት አፈጻጸም አስመልክተው ባቀረቡት ሪፖርት እንደተናገሩት፤የክልሉን ሰላም፣ ብሎም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት እንዲጠበቅ፣ዴሞክራሲ እንዲያብብና የሕግ የበላይነትም እንዲረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ይሰራል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሀገር ደረጃ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲደረግ መቆየቱን የጠቀሱት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፣በዚህም ለውጥ ማምጣት መቻሉን አመልክተዋል፡፡ ‹‹የመጣውን ለውጥ ጠብቆ ሰላም የማረጋገጡ ሥራ ይጎለብታል፡፡›› ብለዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነና የሕዝብን ሰላም የሚያውክ ቦታ እንደሌለው ጠቁመው፣ በፀጥታ መደፍረስ ከቀያቸው ከተፈናቀሉት አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጎች መካከልም ወደ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑት ወደየአካባቢያቸው መመለሳቸውንም አመልክተዋል፡፡ ወደ ቀያቸው የተመለሱትን መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጨፌው በዛሬው ዕለት ሹመቶችን እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2011
ለምለም መንግሥቱ