አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን አመራርና ሠራተኞች ችግኝ ከመትከል በተጨማሪ በባለቤትነት ስሜት ለመንከባከብ መዘጋጀታቸውን ገለጹ።
የባለሥልጣኑ አመራርና ሠራተኞች በትናንትናው ዕለት በኮተቤ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ኮሶ ሜዳ የክረምት ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በተከናወነበት ዕለት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንደገለጹት፤ በመርሃ ግብሩ ከ160 በላይ ሠራተኞችና አመራሮች በበጎ ፍቃድ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ሁሉም ሠራተኛ በአማካኝ 10 ችግኞችን ተክሏል።
መንግሥት በዘንድሮው ክረምት ብቻ አራት ቢሊዮን የዛፍ ችግኞች ለመትከል ያቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሊከናወን እንደተቻለ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ ሠራተኛውም ሆነ አመራሩ ችግኝ ከመትከል በተጨማሪ በባለቤትነት ስሜት ለመንከባከብ ከመግባባት ላይ መደረሱንም አመልክተዋል።
የባለሥልጣኑ ሠራተኛ ወይዘሮ ዱሬቲ ታደሰ በበኩላቸው፤ መንግሥት በተያዘው ክረምት የዛፍ ችግኞች እንዲተክል ለኅብረተሰቡ ሀገራዊ ጥሪ ማድረጉን አስታውሰዋል። ባለሥልጣኑም የተደረገውን የሀገር ጥሪ በመቀበሉ ወደተግባር መገባቱን ጠቅሰዋል፡፡ የትናንቱ ችግኝ ተከላም ቢያንስ 10 ችግኞችን በመትከል በረሃማነትን ለመከላከል አሻራን ለማሳረፍ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ዱሬቲ ችግኞችን መትከሉ ብቻ ውጤት የሚያመጣ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ችግኞቹ መፅደቅ አለመፅደቃቸው ሊያሳስባቸው የሚገባና በባለቤትነት ስሜት መንከባከብ እንዳለባቸውም መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡
«የተተከሉ ችግኞችን ተመልሶ በመምጣት መንከባከብ ይገባናል» የሚሉት ደግሞ ሌላኛዋ የተቋሙ ሠራተኛ ወይዘሮ ገነት ማሞ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ተቋሙ ፍቃደኛ ከሆነ እርሳቸውም ሆኑ ባልደረቦቻቸው ይሄንኑ ተግባር የሚያከናውኑ መሆኑን ተናግረዋል። ሀገራዊ የችግኝ ተከላ ዘመቻው የአንድ ወቅት ሥራ ብቻ መሆን እንደሌለበት ጠቅሰው፤ ዘላቂነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
አቶ ታደሰ አበራ በበኩላቸው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ እውቅና እያገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህም እውቅና በውጤት የታገዘ እንዲሆንም የችግኝ ተከላው አንድ ሰው 40 ችግኝ እስኪተክል ድረስ ተጠናከሮ ሊቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ በዘንድሮው ክረምት ብቻ አራት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2011
ዳንኤል ዘነበ