አዲስ አበባ፡- ሶስተኛው ሀገር አቀፍ የፅዳት ዘመቻ ትናንት የተካሄደ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም የመርሐ ግብሩ ተሳታፊ በመሆን የጽዳትና የችግኝ ተከላ ተግባር አከናውነዋል።
በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የጽዳትና ችግኝ ተከላ በተከናወነበት በትናንቱ መርሐ ግብር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በአዲስ አበባ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መስተዳድር ፅህፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር በመሆን ጽዳት አጽድተዋል፤ ችግኝም ተክለዋል። በመርሐ ግብሩ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የህብረተሰብ ክፍሎችም ተሳትፈውበታል።
በተያያዘም የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች የጽዳት ዘመቻ አካሂደዋል። ዘመቻው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በነቂስ ወጥቶ አካባቢውን እንዲያፀዳና በዚህ ሂደት መልካም ያልሆኑ እሳቤዎችን በመተው ለሀገር አንድነት በጋራ መቆም እንደሚያስፈልግ ባስተላለፉት ጥሪ መሰረት ከወራት በፊት የተጀመረ ሲሆን በቋሚነት በየወሩ የሚከናወንም ነው።
በዚህም መሰረት የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች ትናንት በዋናው መስሪያ ቤት ተገኝተው የጽዳት ዘመቻውን አከናውነዋል።
ከዚህ በፊት በተከናወኑ ሁለት ዙር የፅዳት ዘመቻዎችም የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮችን ጨምሮ መላው ሠራተኛ ከግብር ከፋዩ ጋር የፅዳት ዘመቻ ማከናወኑን ሚኒስቴሩ አስታውሷል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር