በኢትዮጵያ እያሻቀበ ከመጣው የሥራ አጥ ቁጥር አኳያ መንግሥት በ2012 በጀት ዓመት የያዘው የሶስት ሚሊዮን ሥራ ፈጠራ እቅድ ተገቢ ነው። ሆኖም ይሄን ለማሳካት መንግሥት ሥራ ፈጠራ ላይ ሳይሆን ሥራ የሚፈጠርባቸውን አውዶች ማመቻቸት ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባው ምሑራን ይመክራሉ።
የኢኮኖሚ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ተኪኤ ዓለሙ፤ እንደ አገር የሥራ እድል ለመፍጠር መሰራቱ መልካም ነው። ይሁን እንጂ መንግሥት በራሱ አቅም ሥራ መፍጠር የሚችለው በቢሮክራሲውና በፐብሊክ ኢንቨስትመንት ነው። የመንግሥት ቢሮክራሲ ደግሞ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር ስለማይችል ዋናውና ትልቁ የሥራ እድል መፍጠሪያ የግል ዘርፉ ነው። በመሆኑም መንግሥት ለሶስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል እፈጥራለሁ ሲል ማሰብ ያለበት ሥራ እንዲፈጠር በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራትን ነው።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ሥራ መፍጠር የሚቻለው በብዙ መንገዶች ሲሆን፤ ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎችና አገልግሎቶች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሪያ የሚሆኑ ናቸው። ወጣቶችም በእነዚህ ዘርፎች ራሳቸውን አደራጅተውና አቅም ፈጥረው እንዲሰሩ መንግሥት መደገፍ አለበት። በዋናነት የሥራ እድል መፍጠር የሚቻለው ግን የግሉ ዘርፍ ሲንቀሳቀስ ነው።
አንድ ልማታዊ መንግሥት የሥራ እድል መፍጠር የሚችለው፤ አንደኛ፣ መንግሥት ራሱ ሥራ አጥነትን ለመፍታት መዋለ ንዋይ በማፍሰስ በራሱ የልማት ሥራዎች ውስጥ በማሳተፍ ነው። ሁለተኛው የግል ዘርፉ ሲሆን፤ ሦስተኛው ደግሞ እነዚህን ሂደቶች በጥናት በታገዙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመደገፍ በሚፈጠረው አገራዊ አቅም ውስጥ ወጣቱን ተጠቃሚ በማድረግ ነው።
ዶክተር ተኪኤ እንደሚሉት፤ ኢንቨስትመንቱ እንዲስፋፋ ባለሃብቱን በመደገፍ ሂደት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ባለሃብቶችን በተገቢው መልኩ ተቀብሎ ከማስተናገድ እስከ ድጋፍና ክትትል ያለውን ሥራ በአግባቡ በማስኬድ ይዘው የመጡትን ሃብት ለአገር ኢኮኖሚ በሚደግፍና የሥራ እድል በሚፈጥር አግባብ እንዲያውሉት ማስቻል ያስፈልጋል።
ለመንግሥትም ቢሆን የሥራ እድል ከመፍጠር ይልቅ የሥራ እድል የሚፈጠርባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸቱ የተሻለ በመሆኑ፤ ኢንዱስትሪው የሚስፋፋበትንና የሚያድግበትን እድል መፍጠር፤ ከመሰረተ ልማትና መሰል ግንባታዎች ጋር ተያይዞ ሰፋፊ የሥራ እድል መፍጠሪያ ዘርፎችን ማጠናከር፤ ወጣቱም እየተደራጀ የተሻለ የሥራ እድል መፍጠርና ተጠቃሚ መሆን የሚችልባቸውን ተግባራት ለይቶ ማከናወን፤ እንዲሁም ለዚህ የሚሆኑ የቢሮክራሲና ሌሎች ገፊ ጉዳዮችን መፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል።
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ ደግሞ፤ የግል ሴክተሩን በመደገፍም ሆነ የሥራ እድል በመፍጠር እንቅስቃሴ ውስጥ የፋይናንስ ሴክተሩ ዋና ሞተር ነው። የፋይናንስ ዘርፉ ዝግ ሆኖ የግሉ ዘርፍ ማደግ አይችልም። ለዚህም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የግሉ ዘርፍ በሚገባው ልክ ማምረት ባለመቻሉ ሰራተኛን የመቀነስ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱን ማስተዋል ይገባል። የግል ዘርፉ አቅሙን አሳድጎ ሰፊ የሰው ኃይል መቅጠር እንዲችል ደግሞ ከውጭ የሚገቡ ማሽነሪዎች፣ መለዋወጫዎች ብሎም ጥሬ እቃዎች ጭምር ማስገባት፤ ምርታማነቱን ማሳደግና ሰራተኛም መቅጠር አለበት።
ለምሳሌ፣ የውጭ ባንኮች አገር ውስጥ ቢገቡ 110 ሚሊዮን ህዝብ ባለባት አገር ካፒታላቸውን ይዘው ለመውጣት ሳይሆን ሥራቸውን ለማስፋት ነው የሚሰሩት። ለዚህ ደግሞ የፋይናንስ ዘርፉ በሚኖረው የስርዓት ለውጥ ታግዞ በአገር ውስጥ ከሚያገኙት ድጋፍ ባለፈ ከውጭ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችላቸው የዋስትና እድል ሊመቻች ያስፈልጋል። ለወጣቶች ትልቅ የሥራ እድል መፍጠሪያ ከሆኑት መካከል ደግሞ ግብርናና ማዕድን ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ደግሞ ከፋይናንስ ጀምሮ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርን ብቻ ሳይሆን ሰላምና መረጋጋትን ይሻሉ።
ዶክተር ተኪኤ እንደሚሉት ደግሞ፤ ኢንዱስትሪዎችን ከማስፋፋትና ወጣቱ በዛ ውስጥ ገብቶ የሥራ እድል እንዲፈጠርለት ከማድረግ ባለፈ ወጣቱ በተለያየ መልኩ ተደራጅቶና ድጋፍ ተደርጎለት በዘላቂነት ራሱን ማገዝ የሚችልበት አካሄድ ላይ ማተኮር ይገባል። በዚህ ረገድ እስካሁን ባለው አሰራር አንድም ይሄን ማድረግ የሚያስችል ሀብት መኖሩን አለመረዳት ተስተውሏል።
ሁለተኛም ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሰሩ የሚደረገው በውስንና ብዙም ርቀት በማያስጉዙ የተወሰኑ ዘርፎች ላይ ነው። የክትትልና ድጋፍ ሂደቱም ያን ያክል ጠንካራና ችግሮችን በተገቢው መልኩ ያገናዘበ ስላልነበረ የሥራ እድል የመፍጠር ሂደቱ ላይ ጫና በማሳደር የሥራ አጥ እንዲበራከት አድርጓል።
ይሄን ሀሳብ የሚጋሩት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎች ይመረቃሉ፤ በርካቶቹም ሥራ ሳይኖራቸው በቤተሰቦቻቸው ላይ ጡረተኛ ሆነው ተቀምጠዋል። ከዚህ አኳያ ወጣቶችን እያደራጁ ወደሥራ የማስገባት ተግባር ለዓመታት የተከናወነ ቢሆንም፤ በሚፈለገው ልክ ውጤት አምጥቷል ማለት አይቻልም።
ለዚህ ውጤት መጥፋት ደግሞ የመንግሥት መዋቅሩ በተለይም የታችኛው መዋቅር ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። አሁንም እቅዱን ለማሳካት መዋቅሩ ያለበትን ድክመት መፈተሽና የታዩ መልካም ልምዶችን መለየት ያስፈልጋል። ለሥራ እድል ፈጠራ የሚመደብ ፋይናንስን (ለምሳሌ፣ የ10 ቢሊዮን ብሩ) አጠቃቀም፣ አስተዳደርና ውጤታማነትን መገምገም፤ የታዩ ክፍተቶችን ማረም፤ ካለፈው ተምሮም የተሻለ አቅጣጫ ይዞ መስራት ያስፈልጋል።
ምክንያቱም ሥራ የሌለው ወጣት በተለያየ መልኩ ለችግሮች ሲጋለጥ፤ ለተለያዩ ኃይሎች ዓላማ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ሆኖ ሲያገለግል ታይቷል። ለጽንፈኛና ሽብር አስተሳሰቦችም ሲጋለጥ ተስተውሏል። ወደነዚህ ድርጊቶች ዓይኑን አፍጥጦ የሚሄደው ደግሞ ሥራ ሲያጣ ነው። በሃይማኖት፣ በብሔርና በሌላም ተጎዳን የሚል ሀሳብን አንግቦ በየቦታው የሚገኘውም ሥራ ስላልተፈጠረለት እንጂ የኢትዮጵያ ክልሎች አንዱ ከሌላኛው የተሻለ ሆኖ አይደለም።
ዶክተር ተኪኤ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አሁንም በዚህ መልኩ የሚፈጠሩ ሥራዎች በእውቀት ካልታገዙ፤ ያለውን ሀብት ለይቶ አማራጭ የሥራ መስኮችም ካልታዩ፤ የብድር አሰጣጥና አመላለስ ስርዓቱ ተፈትሾ ካልታረመ፤ ብሎም የሚፈጠሩ የሥራ እድሎች በተገቢው የመረጃ ስርዓት ተደራጅተው ካልተያዙ ሥራው እንደቀድሞው ሁሉ መፈተኑ አይቀርም። ይህ ደግሞ የሥራ አጥ ክምችትን በማሳደግም በአገር ልማትና ሁለንተናዊ እድገት ጉዞ ላይ ፈተና መሆኑ አይቀርም።
እንደ ምሑራኑ ሀሳብ፤ አሁንም ቢሆን የሥራ ፈጠራ /የኢንተርፕሩነርሺፕ/ አስተሳሰብና ለዚህ የሚያግዝ ክህሎት የያዙ ምሩቃንን መፍጠር፤ ቀደም ሲል በሥራ እድል ፈጠራው ላይ ሲሰራ የነበረውና የሚፈለገውን ውጤት ያላመጣውን መዋቅር መፈተሸ፤ የግል ባለሃብቱን ትኩረት ሰጥቶ ማበረታታትና የፋይናንስ ስርዓቱንም ማሻሻል፤ ሥራውንም በእቅድና በተደራጀ የፋይናንስ አስተዳደር መምራት ካልተቻለና ሥራውም መንግሥት ተኮር ሆኖ ከቀጠለ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም። ይህ ውጤት ካልመጣ ደግሞ በየዓመቱ እየተከማቸ ያለው የሥራ ፈላጊ ቁጥር ከማሻቀቡ ባለፈ፤ ሰርቶ መብላትና ገንዘብም ማግኘት ስላለበት እንደ ቀደመው ሁሉ ለተለያዩ አጀንዳዎች ተገዢ መሆኑ ስለማይቀር በአገሪቱ ያለው ችግር ይፈታል ማለት አይቻልም። በመሆኑም ይሄን ሊቀይር የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2011
ወንድወሰን ሽመልስ