በሕክምና ተቋማት ሰፋ ያሉ የሙያ ሥነ- ምግባር ግድፈቶች እንደሚታዩ ይገለጻል። እነዚህ ግድፈቶች እየተበራከቱ ከሄዱ ደግሞ ዘርፉ እምነት እንዲያጣ ስለሚያደርጉት ለሕክምና ሙያ ሥነ- ምግባር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ምሑራን ይመክራሉ።
የሕጻናት ሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ፕሮፌሰር ጥላሁን ተካ እንደሚሉት፤ በሕክምና ቦታ ላይ የሚገለጽ መልካምም ሆነ መልካም ያልሆነ የሙያ ሥነ-ምግባር ጉዳይ ከግለሰቦች ባለፈ የባለሙያዎች ድምር ውጤት ነው።
ከዚህ ባለፈም አገልግሎቱን ፈልገው የሚመጡ ታካሚዎችና አሳካሚዎች አገልግሎቱን ለማግኘት የሚፈጽሙት ተግባርና የሚያሳዩት ባህሪ፤ ብሎም የጤና ተቋማት ኃላፊዎች ለባለሙያዎች የሚያደርጉት ድጋፍና ከለላም ተደማሪ ምክንያት ነው።
እንደ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተካ ገለጻ፤ የሕክምና ባለሙያዎች መርሆዎች ከሚባሉት ዋና ዋናዎቹ፣ በሰው ላይ ጉዳት አለማድረስ፤ ለሰው ክብር መስጠትና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኝነቱን ማረጋገጥ፤ መልካም ወይም ጥሩ ማድረግ፤ እና ሁሉንም የሰው ልጅ በፍትሃዊነት ማገልገል ተጠቃሽ ናቸው። ይህ ደግሞ ከታካሚ ጋር ከሚደረጉ የቃላት ልውውጥ ጀምሮ በሚኖር ተግባቦት የሚሰጥን ክብር፣ እንክብካቤና ሙያዊ
ድጋፍን ጨምሮ የሚገለጽ ነው። ይሁን እንጂ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ የሕክምና ሙያ ስነምግባር በበጎ መልኩ የሚገለጸው ከ30 በመቶ የዘለለ ባለመሆኑ፤ 70 በመቶው የሙያ ስነምግባር ግድፈቶች የሚስተዋሉበት ነው።
የሕግ ባለሙያው ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ማንኛውም ሰው በሚፈ ልገው መስክ ተሰማርቶ መስራት የሚችልበት ሕገመንግሥታዊ መብት ያለው እንደመሆኑ የሕክምናው ዘርፍም እንደማንኛውም ሙያ ሥራ የመስራት መብት ነው። ዋናው ነገር ግን የተሰማሩበትን መስክ የሥራ ሥነምግባር ጠብቆ መስራቱ ላይ ነው።
ምክንያቱም ሙያው በሰው ሕይወት ላይ የሚሰራ እንደመሆኑ የሰዎችን መብት ከማክበር ጀምሮ በሙያው ስነምግባር መሰረት ተግባርን በጥንቃቄ ማከናወን ይጠይቃል። ከሕክምና ባለሙያዎችም የሚጠበቀው ይሄው ሲሆን፤ በዚህ መልኩ ከሰሩም የማንኛውም አካል ጣልቃ ገብነት ሊፈትናቸው አይችልም፤ አይገባምም።
እንደ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ ገለጻ፤ የሕክምና ሥነምግባር ጥሰትን በተመለከተ መሰረታዊ የሕክምና ባለሙያዎች የሙያ ስነምግባር መለኪያዎች አሉ። እነዚህም ጠቅላላ መለኪያዎቸ፣ ሙያዊ መለኪያዎች፣ የሕግ መለኪያዎችና የስምምነት መለኪያዎች ናቸው።
ለምሳሌ፣ አገልግሎት ለሚፈልግ ታካሚ አገልግሎት አለመስጠት፤ ከጽንስ ማቋረጥ ጋር ያለ የሕግ አሰራር (ተከልክሎ ሳለ የማይከለከልባቸው ሁኔታዎች ተዘርዝሮ መቅረብ)፤ ከመደበኛ የሕክምና አገልግሎት ባለፈ ለብርድ፣ ለሞት፣ ለወንጀል፣ ለአካል ጉዳት፣ ለዓዕምሮ ሕመም፣ ለሥራና መሰል ጉዳዮች ከሚሰጡ የሕክምና ማስረጃዎች ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ የሙያ ሥነምግባር ጥሰቶች አሉ።
እንደ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተካ ገለጻ ደግሞ፤ የሕክምና ሥነምግባር ትምህርት በኢትዮጵያ የሕክምና ትምህርት ቤቶች እምብዛም የተለመደ አይደለም። እንደውም ከ200 ዓ.ም በፊት የነበሩት ትምህርቱን አልወሰዱም፤ ከዚህ በኋላ ግን በተበጣጠሰ መልኩም ቢሆን እንዲጀመር ተደርጎ የአሰልጣኞች ስልጠና ጭምር በመስጠት የሥነምግባር ትምህርት ለመስጠት እየተሞከረ ነው።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም ለመተግበር ባወጣው እቅድ ውስጥም የሐኪሞች የሕክምና ሥነምግባር ጉልህ ድርሻ ተሰጥቶታል። ይሄን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት ተፈጥሮለትም እየተሰራ ይገኛል። ይሁን እንጂ በተግባር ከሚታየው የሥነምግባር ክፍተት አኳያ ያሉት ጅምር እርምጃዎች ችግሩን መፍታት አስችለዋል ለማለት የማያስደፍር፤ ይልቁንም ሥራው ብዙ መጓዝ እንዳለበት የሚያመላክት ነው።
ምክንያቱም አሁንም ድረስ፣ የግል የህክምና ተቋማት መስፋፋት ይታያል፤ እነዚህ ደግሞ 30 በመቶ የሚሆነውን የመንግሥት አገልግሎት የሚሸፍኑ ናቸው። ሆኖም እነዚህ ሐኪሞች ምን ያክል ሥነምግባር አላቸው የሚለው መታየት ያለበት ነው። ለምሳሌ፣ እነዚህ ተቋማት ማሰልጠኛ ጭምር ከፍተዋል፤ ሆኖም ልምምድ የሚያደርጉት በመንግሥት ተቋማት ነው። በዚህ ሂደት ደግሞ የሥነምግባር ችግር ቢኖር፤ ምን አይነት ባህሪ በሕሙማን ላይ እንደሚያሳዩ መገመት አያቅትም።
ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ እንደሚገልጹት፤ የሚፈጠሩ የሙያ ሥነምግባር ጥሰቶችን መነሻ በማድረግ በሕክምናው ዘርፍ በመሰረታዊነት የሚገለጹ ሶስት የተጠያቂነት ጉዳዮች/ግዴታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ አስተዳደራዊ ግዴታዎችን የሚመለከት ሲሆን፤ የሕክምና ዘርፍ በሰው ሕይወት ላይ የሚሰራ እንደመሆኑ ወደ ሙያው የሚገቡ ሐኪሞች በከፍተኛ ጥንቃቄ መግባት ያለባቸው ከመሆኑ የሚጀምር ነው።
ምክንያቱም ኃላፊነቱ ማህበራዊ፣ ሥነ ልቡናዊና ሌሎች ተያያዥ ጫናዎችን ተቋቁሞ ለሙያው ሥነምግባር መገዛትን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ከስልጠና እስከ ሙያ ፈቃድ መስጠት፤ ከክትትልና ቁጥጥር እስከ እርምትና እርምጃ መውሰድ ያሉ ሂደቶችን የሚመለከት ነው።
በመሆኑም ይሄን ማድረግና ዘርፉ በሙያው ሥነምግባር እንዲመራና ሥራዎችም በዛው አግባብ እንዲከናወኑ ያስፈልጋል። ሁለተኛው ጉዳይ የፍትሐብሄር ኃላፊነት/ግዴታዎችን የሚመለከት ሲሆን፤ የሚፈጠሩ ሙያዊ ግድፈቶች በሶስተኛ ወገኖች ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት ይመለከታል።
ይህ ለደረሰው ጉዳት የሚፈጸምን ካሳ የሚመለከት ሲሆን፤ ካሳው የደረሰውን ጉዳት መሰረት ያደርጋል። ሶስተኛው ደግሞ የወንጀል ተጠያቂነት ግዴታዎችን የሚይዝ ሲሆን፤ ይህ በሚፈጠር የሙያ ግድፈት ምክንያት የገንዘብ ወይም የእስር ቅጣት የሚፈጸምበት ነው።
ፕሮፌሰር ጥላሁን ተካ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ሥነ ምግባር የተሞላበት የህክምና አገልግሎት የታካሚዎችን እርካታ ያሳድጋል፤ ቅሬታን ይቀንሳል፤ ታካሚዎችንም ካልተገባ ወጪ ይታደጋል። በመሆኑም ሐኪሞች ከታካሚዎች ጋር ያላቸው የተግባቦት ሂደት ለታካሚዎች እርካታ ትልቅ ድርሻ አለው።
ይሄም በታካሚዎች “እገሌ በቃል ብቻ ያድናል” በሚል ብሂል ጭምር በጉልህ ይነሳል። ምክንያቱም በመልካም የተግባቦት ሂደት ሕሙማንን በስነልቡና ብቻ ፈውስ እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል።
ሕክምና ደግሞ የሂደት ውጤት እንደመሆኑ የታመመን ማዳን፤ ጤናው የተጠበቀ አምራች ዜጋ ማፍራት ነው። ሆኖም የስነምግባር ክፍተቱ ተገቢው ማሻሻያ ተደርጎ የማይታረምና በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ሙያው እየተሸረሸረ እንዲሄድና እምነት እንዲታጣበት ሊያደርግ ይችላል።
በመሆኑም የሕክምና ትምህርት ቤቶች ሥነምግባር ላይ አተኩረው መስራትና ይሄንኑ የተላበሱ ባለሙያዎችን ማፍራት ይኖርባቸዋል። የጤና ሚኒስቴርም ከእስካሁኑ በተሻለ መልኩ መስራትና ለባለሙያዎች ሥነምግባር መጎልበት የሚከናወኑ ተግባራትን ማገዝ ይጠበቅበታል።
ከዚህ በተጓዳኝ የግል የሕክምና መስጫና ማስተማሪያ ተቋማት ሕክምናውን መሰረት ያደረገ ሥራ ወይስ ገንዘብን ለማግኘት ሲሉ ነው ስልጠና የሚሰጡት የሚለው ትኩረት ተሰጥቶት ሊታይ ይገባዋል።
ምሑራኑ እንደሚሉት፤ የሕክምና ተማሪዎችን የሕክምና ሙያ ሥነምግባርን በተመለከተ ወደ ኋላ ሊባል የማይገባው፤ አንተና አንቱ ከሚል የተግባቦት ሂደት የሚፈጠርን ግድፈት ለማረም ተማሪዎች በእንጭጩ ሊታነጹበት እንደሚገባ ነው።
ከዚህ በተጓዳኝ ሕጎች የሚወጡት ችግሩን በሚያውቁትና በውስጡ ባሉ ሰዎች አለመሆን እና ሰሞንኛ ጉዳዮችን አማክለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የራሳቸው ክፍተት አለባቸው። በዚህ መልኩ በየጊዜው የሚወጡ በርካታ ሕጎችም በየወቅቱ ከሁኔታዎች ጋር እየተገናዘቡ መሄድ ላይ ክፍተት አለ።
እነዚህም የስነ ምግባር ጉድለቶችን ተከትሎ በሚሰጡ የተጠያቂነት ሂደት ውሳኔዎች ላይ እንቅፋት ስለሚሆኑ ባግባቡ ሊታዩ ያስፈልጋል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ምንም እንኳን የግብዓት ችግር፣ የሥራ ጫናና የጥቅማጥቅም ጉዳዮች ለሙያ ሥነምግባር መከበር ፈታኞች ቢሆኑም፤ ባለሙያዎች ለዚህ እጅ ሳይሰጡ ለሰው ሕይወት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2011
ወንድወሰን ሽመልስ