የሰርከስን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ በመገንዘብ እውቅና የሰጠውም ሆነ በባለቤትነት የሚከታተለው የመንግሥት አካል ባለመኖሩ የዘርፉ እድገት እጅጉን መጎዳቱ ይነገራል። ይሄን መነሻ በማድረግም ዘርፉ የመንግሥትን እውቅናና የፖሊሲ ድጋፍ አግኝቶ የሚጠናከርበትን አቅጣጫ ለመተለም የሚያስችል የባለድርሻዎች የውይይት መድረክ ሰሞኑን ተዘጋጅቷል። በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የባህል እና ቴአትር አዳራሽ የተካሄደውን ይሄን መድረክ ያዘጋጀው ሰላም ኢትዮጵያ ከስዊድን ኤምባሲ ጋር በመተባበር ሲሆን፤ የሰርከስ ዘርፉ የሚያስተባብረው፣ የሚያቀናጀውና ከተበታተነ አሰራር የሚያወጣው አካል ባለመኖሩ መድረስ ያለበት ከፍታ ላይ ሊደርስ እንዳልቻለ ነው የተገለጸው።
በመድረኩ “የኢትዮጵያ ሰርከስ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶች እና እድሎች” በሚል ርእስ አቶ ፅና ከበደ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ እንደተመለከተው፤ በኢትዮጵያ የሰርከስ ዘርፍ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። በተለይም ባለፉት 25 ዓመታት በዘርፉ በርካታ ቡድኖች የተፈጠሩ፣ ከጥራትና ብቃት አንፃር ከፍተኛ እድገት የተመዘገበበት፣ ለበርካታ ባለ-ተሰጥኦ ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የመታወቅ እድልን ያስገኘ ከመሆኑም በላይ፤ የአገርን መልካም ገፅታ ከመገንባትና ሰፊ የሥራ እድልን ከመፍጠር ባሻገር፤ ከማንም የስፖርት አይነቶች በላይ ለአገራችን ኢኮኖሚ ከፍተኛ ገቢና የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ያለ ዘርፍ ነው። በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀና ተፅእኖ ፈጣሪ መሆንም ችሎ ነበር። ሆኖም በሂደት እየተዳከመና ወደ ተናጠል እንቅስቃሴ እያሽቆለቆለ መጥቷል።
የ“ሠላም-ኢትዮጵያ” መስራችና ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ወንድሙ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የመንግሥት አካላትን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለ ሰርከስ ሙያ ምንነትም ሆነ ስለሚያበረክተው ጉልህ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አስተዋፅኦ በቂ ግንዛቤ የላቸውም። የሰርከስ ክለቦችም የጋራ ጥቅማቸውን የሚያስከብሩበትና የድርድር አቅማቸውን ለማጎልበት የሚያስችላቸው አደረጃጀት አልፈጠሩም። ዘርፉን የሚመራ ምንም አይነት ሀገራዊ ፖሊሲም ሆነ ስትራቴጂክ እቅድ፣ የግብአት አቅርቦት፣ የክሂል ስልጠናዎችና የዳበረ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ብቃትም የለም። በእነዚህና መሰል ምክንያቶችም ሰርከስ በሚፈለገው መጠን አላደገም።
አቶ ተሾመ እንደሚሉት፤ “ሠላም-ኢትዮጵያ” ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነና ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት “ባህል መንገድን ይጠርጋል” የሚል ፕሮጀክት ቀርፆ፤ ኢትዮጵያ ባለው ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ አማካኝነት በሙዚቃ፣ ፊልም፣ ሚዲያ እና በሰርከስ ዘርፎች እየተሳተፉ ያሉ አካላትን፣ ባለ- ተሰጥኦ ወጣቶችንና ክበባትን ለማበረታታት በአራት የክልል ከተሞች በመንቀሳቀስ አቅም የመገንባት ሥራውን ጀምሯል። ሆኖም በሚፈለገው ፍጥነትና ሁኔታ ተግባሩን ለማከናወን አመቺ ሁኔታዎች የሉም። ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያውን ኃላፊነት መውሰድ ያለበት እራሱ ባለሙያውና ማህበራቱ ናቸው። የእነሱ በባለቤትነት መንፈስ መንቀሳቀስና ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት፤ በተለይም ለመንግሥት ማድረስ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ደግሞ አቅም ቢኖራትም ስላልተሰራበት ከሌላው ዓለም ጋር በንፅፅር ስትታይ በዚህ ዘርፍ በጣም ኋላ ቀርና በዘርፉ ያልተጠቀመች ሆናለች። ሌሎች ግን ምንም ሳይኖራቸው ርቀው ሄደዋል። ይህን ችግር ለመፍታት ደግሞ ሀገር አቀፍ የሰርከስ ማህበር መመስረት በጣም ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ ድርጅታቸው የሰርከስ ዘርፉን ለማጎልበት በአቅም ግንባታ፣ ገንዘብ፣ ቁሳቁስና በመሳሰሉት ለማገዝ በሙሉ አቅሙ ይሰራል።
የሰርከስ ሙያና ማህበራቱ የታዳጊዎችን አካል ብቃትና ማህበራዊነት ከማሳደግ፤ የግል ህይወትን ከማሻሻል እና የአገርን ገፅታ ከመገንባት ባለፈ ያገር ኢኮኖሚን በማሳደግ ብሎም የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘት አኳያ የሰርከስ ትርኢት ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን የሚናገረው ደግሞ በ13 ዓመቱ “ሰርከስ ደብረ ብርሃን”ን የተቀላቀለውና የ26 ዓመቱ ለግላጋ ወጣት ሰርከሰኛ ፋኑኤል ሀብተ ማርያም ነው።
ሰርከሰኛ ፋኑኤል፣ ለአዲስ ዘመን እንደተናገረው፤ በሰርከስ ሙያ ከፍተኛ ችሎታን አዳብሯል። በችሎታውም ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ ክፍሎች ባለፈ በአፍሪካና አውሮፓ ዞሯል። በዚህም ትልልቅ ቦታዎች ላይ ውሏል፤ ኢትዮጵያንም ስሟን በትልልቅ ዓለማአቀፍ ሚዲያዎች ጭምር አስጠርቷል፤ ለራሱም በብዙ ተጠቅሟል። ብዙዎችም በልጅነት እድሜያቸው የሃብት ባለቤት እንዲሆኑም አቅም የፈጠረ የገቢ ምንጭ ዘርፍ መሆኑንም ተመልክቷል። ሰርከስ መልካም ቁመናን እንደሚፈጥር፤ ከሱስ ተገዢነት ነጻ እንደሚያደርግ፤ በህዝብ ዘንድ የተወደደ ባህሪንም እንደሚያጎናጽፍ ታዝቧል። በመሆኑም ወጣቶችና ታዳጊዎች ወደ ሰርከስ ቢገቡ የዚህ ባለቤት መሆን ይችላሉ። እርሱም በቀጣይ በዚሁ ዘርፍ የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል።
በተመሳሳይ የ“ሰርከስ ደብረ ብርሃን” መስራችና ዳይሬክተር አቶ ተክሉ አሻግር ይሄንኑ ያጠናክራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የሰርከስ ጥበብ ሁለንተናዊ ፋይዳ ያለው ሲሆን፤ ዘርፉ ትልቅ ደረጃ እንዲደርስና ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃም እንዲያድግ በመንግሥት ፖሊሲ መደገፍ አለበት።
“የአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ አንድ ሺህ ካሬ ቦታ ተሰጥቶኝ ማሰልጠኛ ማእከል ገንብቼ በመስራት ብቃት ያላቸውን ወጣቶች በማፍራት ላይ ነኝ።” የሚሉት ወይዘሮ ውዴ ፅጌ፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሰርከስ ማሰልጠኛ ተቋማትን በመክፈት ወጣቶችን እያበቁ የሚገኙ ባለሙያዎች መካከል አንዷ ናቸው። ባለሙያዋ ለበርካታ ዓመታት ከፍተኛ ውጣ ውረድ ቢያጋጥማቸውም ተስፋ ባለመቁረጥ ባደረጉት እንቅስቃሴ ዛሬ ውጤታማ መሆን እንደቻሉ ይገልጻሉ። ሁሉም ክልሎች እንደ አማራ ክልል ለዘርፉ ትብብር ቢያደርጉ ሰርከስን ለማስፋፋትና ለማሳደግ፤ ከዘርፉም ተጠቃሚ ለመሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራሉ።
ነዋሪነቱን ጀርመን ያደረገው፣ ሰርከሰኛ ግርማ ፀሐይ በበኩሉ፤ በዘርፉ ትልቅ ደረጃ የደረሱ አገራት ሁሉ ነገር የተመቻቸላቸው መሆናቸውን ይናገራል። በኢትዮጵያም የመንግሥት እውቅናና አሰሪ ፖሊሲ ቢኖር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ትልልቅ ማእከላትን ገንብተው በመስራት ሰርከስን በሌሎች አገራት ካለበት ደረጃ ማስበለጥ እንደሚቻል ይገልጻል። ይህ የሙያና የአገር ፍቅር ደግሞ በፖሊሲ ማእቀፍ ሊታገዝ እንደሚገባውም ይመክራል።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሬክተር አቶ ይስማ ፅጌ፤ ለሰርከስ ዘርፍ እድገት ከመድረኩ ብዙ ቁም ነገሮች የተገኘበት መሆኑን በመግለጽ፤ በቀጣይ ከሰርከስ ባለሙያዎችና ክበባት ጋር በመሆን ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመመስረት የሚፈገውን የ“ሰርከስ ኢትዮጵያ” ማህበር ከማቋቋም አኳያም መስሪያ ቤታቸው ከጎናቸው እንደሚቆም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 8/2011
ግርማ መንግሥቴ
ፎቶ፡- ከድህረ ገፅ