የሴቶች መብት ጉዳይ የአንድ ወቅት ሥራ አይደለም!

በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚፈፀም አስገድዶ መድፈር፣ ድብደባ፣ ግድያና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች መጨመራቸውን በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ የተለያዩ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበራት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከጊዜ ወደ ጊዜ በጾታዊ ጥቃት ሕይወታቸውን የሚያጡ፣ አካላቸው የሚጎድል ሴቶች ቁጥር አስደንጋጭ በሆነ መንገድ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመሆኑን በየጊዜው በተለያዩ ሚዲያዎች የምናየውና የምንሰማው ጉዳይ ነው። የሚደርሰው ጥቃት አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ሰለባ ከማስከተሉም ባሻገር፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወት እስከማሳጣት የሚያደርስ ድርጊት ነው:: መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ችግሩን ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርጉም፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩ እየተባባሰ ለመሄዱ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል::

የጥቃቶች መደጋገምና አሳሳቢነት ለአብነት የሴቶችን ገጽታ በአሲድ ማበላሸትና የነበራቸውን ሙሉ ጤንነት ማሳጣት፤ እንዲሁም አዳዲስ የጥቃት ዓይነቶች መምጣትም ሁላችንም እየታዘብነው ያለ ዕውነታ ሆኗል:: በተለይም በሚያሰቅቅ ሁኔታ በአብዛኛው ግድያው የሚፈጸመው በቅርብ ወዳጅ፣ በትዳር አጋር መሆኑ ልብ የሚሰብር ድርጊት ነው።

ይህ ለቀጣዩ ትውልድም ስለ ትዳር ሕይወት ያለውን አዎንታዊ አመለካከት የሚያዛባ ከመሆኑም ባሻገር የማህበረሰብ ዋና ምሰሶ የሆነውን ቤተሰብ የሚያናጋና ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚንድ መሆኑ ይበልጥ አሳሳቢ እየሆነ ነው።

በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቁጥሩ እንደጨመረ ለመረዳት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ጋር የሕግ ድጋፍ ፈልገው የሚሄዱ ተጠቂዎችን ብዛት መመልከት በቂ ማሳያ ነው። ማህበሩ በፈረንጆች 2022 ብቻ በቢሮዎቹ ከተደረጉለት የእርዱኝ ጥያቄዎች 47ቱ ግድያ እና ግድያ ሙከራዎች፣ 32 አስገድዶ መድፈር እንዲሁም 158 በሴቶች ላይ የደረሱ አሰቃቂ ድብደባዎች መሆናቸውን የገለጸበትን መረጃ መመልከት ይቻላል።

ማህበሩ ያሉት ቅርንጫፍ ቢሮዎች በተወሰኑ ከተሞች ወይም አካባቢዎች እንጂ በሁሉም ቦታ አይደለም። ስለዚህ ሀገር አቀፍ የሆነ ጥናት ቢደረግ ቁጥሩ ከፍተኛ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። ልብ ማለት የሚኖርብን ወደ ማህበሩ የሚመጡት የድረሱልኝ ጥሪዎች በሀገር ደረጃ እዚህ ግባ የሚባሉ አለመሆናቸውን ነው። ይህ ሴቶች ላይ የሚደርሰው የጥቃት መደጋገም ነገሩ ‘የተለመደ’ እንዲሆን ያደረገው ይመስላል።

ጾታዊ ጥቃትን እንደ ተለምዷዊ ድርጊት በቸልታ መታየቱ የማህበረሰብ ባህልንና እሴትን ጭምር እንደመናድ ነው። ይህ ሁሉንም ሰው ካላስደነገጠና ካላስቆጣ እንዲሁም ለመፍትሄ እንድንረባረብ ካላደረገ የከፋ መዘዝ አለው። ቀደም ሲል የምናያቸውና የምንሰማቸው ውግዘቶች፤ በሀገር ደረጃ የሚሰሙ ጩኸቶች ጥቃቶች እንዳይደገሙ የሚያስብሉ ብሔራዊ ሃዘኖች፣ ይመለከተኛል የሚሉ መቆርቆሮች እየጠፉና እየከሰሙ ነው። ጥቂቶች ብቻ ያውም አንድ ጥቃት ሲፈፀም ጠብቀው ድምፅ ማሰማታቸው እየተለመደ መጥቷል። ይባስ ብሎ በእህቶቻችን ሞት መቆጨቱ ቀርቶ አሁን አሁን በማህበራዊ ሚዲያ አጥቂውን፣ ‹‹ደግ አደረገ›› የሚሉ ድምጾች ሁሉ መስተጋባት ጀምረዋል።

ከአሰቃቂ የሴቶች ጥቃት ማግስት “እና ምን ይጠበስ?” ዓይነት ስሜቶች መስተጋባት ከጀመሩ ለአንድ ማህበረሰብ የሞራል ዝቅጠት ምልክቶች እና አደገኛ አዝማሚያዎች ናቸው። በቅርቡ በሴቶች ላይ የሚፈጸምን እኩይ ድርጊትና ጥቃትን በተመለከተ “የእሱን ማን አየለት”፣ “ይሄኔ አቃጥላው ነው የሚሆነው” የሚሉ አስተያየቶች ለተጠቂ ሁለት ጊዜ ሞት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ከአጥቂ ጎን የሚቆሙ አስተያየቶች እየበዙ መጥተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰማናቸው ጥቃቶች ምን ያመሳስላቸዋል ካልን የቅርብ ሰው ነው በሚባል ሰው መፈጸማቸው ነው። ባል፣ የእንጀራ አባት፣ ፍቅረኛ፣ እጮኛ፣ በመሆኑ ለችግሩ እልባት ለመስጠት አንዱ ፈተና ነው።

አደጋ የሚጥሉት የእኔ ሰው ነው በሚባል በመሆኑ ወዴት ይኬዳል? ሴቶች ላይ የሚፈጸም አሰቃቂ ጥቃትን ቀድሞ መረጃ እንዲኖር ፈታኝ የሚሆነውም ከለላ ሰጪዎች ራሳቸው አጥቂዎቹ ስለሚሆኑ ነው። ባእድ ከሆነ ጠላት ይሸሻል፤ ቤት ውስጥ ካለ ወገኔ ከምንለው ሰው ግን ወዴት ይሸሻል? በራስ ሰው መጠቃት አጥቂውን ቶሎ ለፖሊስ አካል ሪፖርት ለማድረግ ማመንታት ውስጥ ሊከት ይችላል። ነገር ግን አንዳንዶቹ ጥቃቶች ለፖሊስ ሪፖርት ተደርገው ቶሎ እርምጃ ስለማይወሰድ ትልቁን መዘዝ ይዘው ይመጣሉ። ከሕግ አስፈጻሚው በኩል ክፍተት የለም ለማለት አይቻልም። ፖሊስ መረጃ የሚሰበስብበት መንገድ፤ ለማህበረሰብ ጠንቅ የሆነን ሰው የሚከታተልበት መልክ ይበልጥ መዘመን አለበት።

ወንዱ እጁን ያነሳባት ሴት ጋር እንዳይቀርብ የሚያደርጉ ሕጎችን አልተለማመድንም። ከዚህ አንጻር የሕግ አስፈጻሚ አካላት ቸልተኝነት ጋር ተዳምሮ የማህበረሰቡ ግንዛቤ ማነስ ሊኖር ይችላል። የችግሩ ስር መሠረት አንድ አስፈጻሚ አካል ላይ የሚደፈደፍ ግን አይደለም። የችግሩ ክፍተት ከአስፈጻሚው ነው ብሎ መደምደም አይቻልም::ችግሩ ውስብስብ ነው።

ሕጉን ከማስፈጸም በኩል፣ አስተማሪ ቅጣት ካለመወሰን በመነጨ መንገድ ጥቃቶች ተበራክተው ይሆናል። ስር መሠረቱ ግን በዋናነት ሴትን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት ማህበረሰብ ነው። ጥቃት አድራሹም ያደገበት ማህበረሰብ ውጤት መሆኑን መዘንጋት የለብንም። የሴቶች ጥቃት መጨመር ዋናው መንስዔ በኅብረተሰቡ ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘው አድሏዊ አመለካከት መሆኑን ማስተባበል አያስፈልግም።

ይህም ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግ አመለካከት፣ በኢኮኖሚ ራስን አለመቻል፣ ሱስ፣ መጠጥና አደንዛዥ ዕፆች ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው:: ለዚህም ከሕግ ክፍተቶች በተጨማሪ በእጅጉ የሚስተዋለው የአፈጻጸምና ያሉትን ሕጎች የመተግበር ችግር እንዲሁም በጥቃት አድራሾች ላይ አስተማሪ የሆኑ ቅጣቶች አለመወሰናቸው እንዲባባስ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው።

የሕግ ባለሙያዎች ለጥቃቱ መበራከት የሕጉ ክፍተት ብቻ መንስኤ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ሲነገሩ ይደመጣል። ሁሉም የራሱን ኃላፊነት ሲወጣ፣ እንደ ማህበረሰብ ራሳችንን ስንፈትሽ፣ ለሴቶች ያለን አመለካከት ሲቀየር፣ በባህላችን ውስጥ ልክ ነው ያልነው ልክ እንዳልሆነ ሲገባን ጥቃቶች ቀስ በቀስ ሊቀንሱ ይችሉ ይሆናል።

ችግሩ የሚያሳው በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት እየተደረገ ያለው ጥረት በቂ እንዳልሆነ፣ ሌሎች ጥቃቱን ለመከላከልም ሆነ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች መቀየስ እንዳለባቸው የሚጠቁም ነው:: እዚህ ላይ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሴቶች መብት ተቆርቋሪዎችና ሚዲያዎች በሆነ ወቅት ላይ ጥቃቶች ሲፈፀሙ ብቻ አይደለም ድምፃቸውን ማሰማት ያለባቸው:: ሁሌም ቢሆን የሴቶች ጥቃት አጀንዳቸው ሊሆን ይገባል::

ብሌን ከ6ኪሎ

አዲስ ዘመን ህዳር 12/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You