የሰላሌና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን አስመረቁ
ሰላሌ፡- የሰላሌ እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ያስተማሯቸውን ተማሪዎች ትናንት አስመረቁ።ተመራቂዎች በተ ማሩበት የትምህርት ዘርፍ ለአገራቸው ህዳሴ ጠንክረው እንዲሰሩ ተጠየቀ።
የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በሁለት ፕሮግራሞችና በሰባት የትምህርት ዓይነቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 198 ተማሪዎች ባስመረቀበት ወቅት በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ በዚህ ዓመት አገሪቱ ከአንድ መቶ አምሳ ሺ በላይ ተማሪዎችን ታስመርቃለች። ምሩቃኑ አገራቸው ወደ ህዳሴ የምታደርገውን ግስጋሴ የሚያቀላጥፉ፣ ለሰላም ፣ለፍትህ ፣ለህዝቦች ወንድማማችነትና አብሮ ማደግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መላው ህዝብ ትምህርት እንዲስፋፋ የሚጠ ይቀው መስኖና መንገድ፣ መብራት እና ውሃ፣ የጤናና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች ስለማይፈልግ ሳይሆን ልጆቹ በመማራቸው የሚ መጣውን ትልቁን የነገን ተስፋ አሻገሮ በማየቱ ነው፡፡ስለሆነም ተመራቂዎች የሀገራችሁና የራሳችሁ ህይወት ብሩህ እንዲሆን በሀገርና ወገን ፍቅር፣ በማስተዋልና በሥራ ወዳድነት እንዲሁም በማንበብና በመማር ራሳችሁን በማነፅ እንድትኖሩ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በ2009 ዓ.ም በአንድ ሺ አርባ ሰባት መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በግብርናና ተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ የትምህርት ፕሮግራሞች ተማሪዎችን እያሰለጠነ ይገኛል፡፡
በተያያዘ ዜናም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለሃያኛ ጊዜ ባከናወነው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ዘጠኝ ሺ 860 ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 28 ነጥብ ሶስት በመቶ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኢንጅነር ፍስሃ ጌታቸው በምረቃው ወቅት እንደተናገሩት፣ ዩኒቨርሲቲው በስምንት ኮሌጆችና በሁለት ኢንስቲትዩቶች በ93 የትምህርት አይነቶች የመጀመሪያ ዲግሪ፤ በ101 የትምህርት አይነቶች ማስተርስና በ20 የትምህርት አይነቶች የሶስተኛ ዲግሪ እያስተማረ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲው በ2011 ዓ.ም 31 ሺ 124 ወንድ 12ሺ 326 ሴት ተማሪዎች በመደበኛና ተከታታይ ትምህርት መርሐ ግብር እያስተማረ ይገኛል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ በተጓዳኝ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም 560 የምርምር ሥራዎችን በተለያዩ ጆርናሎች ማውጣቱን ጠቁመዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራትና በምርምር ረገድ የሚሰራቸው ሥራዎች ለሌሎች አርአያ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል። ዘንድሮ በመላው ሀገሪቱ 175 ሺ ተማሪዎች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይመረቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ምንም እንኳ በርካታ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ የትምህርት ሽፋኑ 13 ከመቶ በመሆኑ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጸዋል። በመሆኑም በተለይም በሀገሪቱ የጤናና የግብርና ዘርፍ መሻሻሎች ላይ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ የሚያመለክት መሆኑን አስቀምጠዋል።
ተመራቂዎች ሀገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ለማፋጠን እውቀታቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህም በተለይ ከብሄር ተኮር ግጭቶች ራሳቸውን በማቀብ በሀገር ልማት ሥራ ላይ መረባረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 7/2011
በአብርሃም ተወልደ እና በክፍለዮሐንስ አንበርብር