ፀሐይዋ እያዘቀዘቀች ነው፤ የወጣችበትን የምሥራቁን አቅጣጫ ተሰናብታ መጥለቂያዋን ምዕራቡን ይዛለች። በደብዛዛ ፈገግታዋ ልግባ ልቆይ የምትለዋ ፀሐይ መልሳ ትርባለች። በአረንጓዴ ተክሎቹ መሀል በነፋሻማ አየር ታጅቦ ሽው የሚለው አየር ምግብ ነው። አረንጓዴ ከለበሰው መሬት ጋር ተዳምሮ ቦታው ለተመልካች ልዩና ውብ ነው። ማድነቅ ብቻ ሳይሆን በውስጡ አረፍ ማለትንም ይጋብዛል።
ይሄ ስፍራ በመዲናችን አዲስ አበባ ሰሚት አካባቢ ይገኛል። በልዩ መጠሪያው የወጂ ህብረት አምባ አረንጓዴ ቦታ አልሚዎች ማህበር ይባላል። በዚህ ስፍራ ላይ የአካባቢውን ነዋሪዎች ማጣት ፍጹም አይታሰብም፤ የኑሯቸው አንዱ ክፍል አድርገው ጠዋት ማታ በኃላፊነት ይንከባከቡታል። በበጋ የበጋ፣ በክረምት ደግሞ የክረምት ሥራዎችን በመስራት ለአካባቢያቸው ውበት እና ጽዳት ምሳሌ ሆነዋል።
በተለይ በዕድሜ ጎልማሳ የሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎች በአረንጓዴ ልማት ቦታ (ግሪን ኤሪያ) ላይ ተሰባስበው የሚመክሩት የአረንጓዴ ቦታቸውን በምን እና እንዴት እንደሚያስውቡት ነው። ጉልበት፣ ጊዜና እውቀታቸውን ሁሉ አካባቢያቸውን ለማሳመር ያውላሉ። ደከመን ሰለቸን ሲሉ አይደመጡም። ሥራውን የሚሰሩት ደግሞ በራሳቸው ተነሳሽነት በኃላፊነት ጭምር በመሆኑ ውጤታማ አድርጓቸዋል። ሌላው ነዋሪም በገንዘብ ፣በሞራል ጭምር ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው የነገሩኝ በማስተባበር ሥራ ላይ የተጠመዱት መምህር ገብረመድህን በሀምላ ናቸው።
«የአረንጓዴ ልማት ጥቅሙ ለራስ ነው፤ ሰዎች የድካም ስሜት ሲሰማቸው የአእምሮ መጨናነቅ ሲያጋጥማቸው ሰውነትን ዘና ለማድረግና ንጹህ አየር ለመተንፈስ አረንጓዴና ንጹህ ቦታ ያስፈልጋል። ሕፃናት በንጹህ ቦታ ይጫወታሉ። በየሰፈሩ አረንጓዴ ቦታ ሲኖርና ልጆችም ሆኑ ሌሎች ተገናኝተው መጨዋወት ሲኖር መቀራረብ ይኖራል፤ ይሄም ያፋቅራል። የሰውነት ማጎልመሻ ስፖርት በመስራትም ጤናን መጠበቅ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ አረንጓዴ ቦታዎችን ማስዋብና መንከባከብ ያስፈልጋል ።» ይላሉ።
አቶ ንጉሴ ክብሩ አስተባባሪ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት አካባቢውን ለነዋሪው ምቹ በአረንጓዴ ተክሎች ያማረ ከማድረግም በተጨማሪ ሕፃናት እና ወጣቶች የሚያነቡበት ምቹ የማንበቢያ ቦታ ጭምር እንደሚሰራ ይናገራሉ። ይሄ ደግሞ ልጆች አልባሌ ቦታ ላይ እንዳይውሉ ፊታቸውንም ወደ ንባብ እንዲያዞሩ ያደርጋል። ስለዚህ በአካባቢ ሕዝብ እንዲለማና የአካባቢው ሕዝብ እንዲጠቀምበት ነው ያደረግነው። ለተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችም ይውላል።
በአሁኑ ሰዓት እየለማ ያለው አረንጓዴ ስፍራ ሦስት ሺ850 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው። ካለፉት ዓመታት ጀምሮ እንደ ግራር፣ ወይራ፣ዝግባ … የመሳሰሉትን ሀገር በቀል ዛፎችን ጨምሮ በርካታ ችግኞችን ተክለናል። ቦታውን በብሎኬት በማሳመርና በሳር በመሸፈን ንጹህና ማራኪ አረንጓዴ ስፍራ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ለዚህ ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ከ500 እስከ 5000 አዋጥተዋል የቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 9 ችግኝ እና ሳር በመስጠት ከፍተኛ ትብብር አድርጎልናል። የቦሌ ክፍለ ከተማ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ቦታውን በአካል በመመልከት እንድናለማ ፈቃድ ሰጥቶናል፤ ውል ወስደናል ሲሉ ነው የተናገሩት።
የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ እንዳሉት በአዲስ አበባ የሚገኙ የአረንጓዴ ቦታዎችን በደን ከመሸፈን አንፃር በርካታ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ።
ከተማዋን አረንጓዴ የማልበስ ዕቅድ መንግሥት ብቻውን ውጤት የሚያመጣበት ባለመሆኑ ኅብረተሰቡ በተለያዩ አደረጃጀቶች በማህበራት መሳተፍ አለባቸው። በዚሁ መሠረት ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመኖሪያቤት ማህበራት የመሳሰሉት አረንጓዴ ስፍራዎችን ማልማት ላይ ሲሳተፉ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ይበልጥ ተበረታትተው ወደ ሥራው እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።
በክረምቱ ወቅት በችግኝ ተከላ ወደ ሥራ ለሚገቡ ማህበራትም ሆነ ተቋማት አስፈላጊውን ችግኞች እና በጉድጓድ ቁፋሮ እገዛ ይደረጋል። አሁን ከ500ሺ በላይ ችግኞች መኖራቸውን ይገልጻሉ።
«የደን ተከላ በአንድ ጊዜ ብቻ የሚሰራ ሥራ አይደለም፤ ዓመቱን በሙሉ የሚሰራ ነው። በመሆኑም ችግኝ ማፍላት፣ ጉድጓድ መቆፈር፣ ከዚያም ችግኝ መትከል ይከተላል። በዚሁ መሠረት ባለፉት አስራ አንድ ወራት ችግኝ የማፍላት ሥራ ተሰርቷል። በተለያዩ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች 780 ሺ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል። ይሄ በራሳችን የተሰሩ ናቸው። እስካሁንም 250ሺ ችግኝ የተተከለ ሲሆን በዚህም ሥራ 19 ሺ ዜጎች ተሳታፊ ሆነዋል» ይላሉ አቶ ዋለልኝ። በቀጣይ እንደ ሀገር አቀፍ ለሚሰራው ሥራም የጉድጓድ ማስቆፈር ሥራ እየተሰራ ነው።
አቶ ዋለልኝ እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ በዓመቱ መጀመሪያ የተያዘው ዕቅድ አንድ ሚሊዮን ችግኝ እንተክላለን የሚል ነበር። ሆኖም ግን አሁን ለአረንጓዴ ልማት በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የተነሳ ዕቅዱን ወደ ሦስት ሚሊዮን ከፍ በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ተገብቷል። ሐምሌ 22 ደግሞ በመላ ሀገሪቱ በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታስቧል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 7/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር