ሚሊኒየም አዳራሽ 9ሺ637 ምሩቃንን ለማስ ተናገድ አሸብርቃለች። ምሩቃኑ ወደ ውስጥ ለመግባት በመብራት በደመቁት ድንኳኖች ውስጥ ተሰልፈዋል። ራቅ ብለው ደግሞ ወላጆች ቤተሰቦች በምሩቃኑ ደስታ ላይ ለመታደም በሚያምሩ አልባሳቶች ተውበው ተገኝተዋል።ወደ አዳራሹ ለመግባት በቆሙት ሰልፈኞች መካከል ሽር ጉድ የሚሉ አስተባባሪዎች ለበዓሉ ድምቀት ሆነዋል። ለምረቃ የበቁ አካል ጉዳተኞች፣ አዛውንትና ወጣቶች ከቤተሰብ ጋር የመልካም ምኞት መግለጫ አበባ በመሰጣጣት ይለዋወጣሉ።
ወደ ውስጥ ሲዘለቅም ስፍራ ስፍራቸውን ይዘው የተቀመጠው እድምተኞች አጀብ ያሰኛሉ። በተለይም በባለስልጣናት የደመቀው መድረክ አይን ይሰርቃል።ምክንያቱም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተርነት ለመስጠት የሞሸራቸው እንግ ዶችም ተገኝተዋል።በመድረኩ ብዙዎቹ በቀይ ድርብ በደመቀው ጥቁሩ ገዋን አምረዋል። ይህን ሁሉ ነገር እየተመለከትን መደመምን ሳንጨርስ መርሐግብሩ ተጀመረ። ሁሉም በየተራ ስለተመራቂዎቹ፤ ስለአገር ጉዳይና ስለ ቤተሰብ አሳሰቡ ፣ አስገነዘቡ።
«የሰው ልጅ ከበላይና ከበታቹ እንዲሁም ከተፈጥሮ እንደተማረ የትምህርትን መጨረሻ ሳያይ ይዘልቃል። እናንተ ግን እስከዛሬ የሚሰጣችሁን ኮርስ በላቀ ውጤት እንዳለፋችሁ ሁሉ ከፊታችሁ ሌላ ዩኒቨርሲቲ አለና የማንበብ ልማዳችሁ ተቀይሮ በጭንቅላት ብቻ ሳይሆን በመንፈስም፣ በውስጥ ማንነትም መባረክ ይኖርባችኋል።» አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ ቀጠሉናም የመማር ዋናው ገፊ ነገር ትርጉም ያለው ኑሮ መኖር ነው። ይህ ደግሞ ካልተዋደዳችሁ በስተቀር ፍላጎታችሁን የሚያሳካ አይሆንም። እናም በዚህ ዩኒቨርሲቲ የተመረቃችሁ ቀላሉን ሳይሆን ትክክለኛውን መምረጥ መቻል ይኖርባችኋል።
ተማሪዎች ሊተገብሯቸው የሚገቡ ስምንት ዋነኛ እሴቶች እንዳሉ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይም እንዲህ ብለዋል። «የሁሉንም አበርክቶ፣ የሁሉንም እውቀት ማክበርና እንደሚበልጠን በጸጋ መቀበል ያስፈልጋል፤ በሚሰሩ ሥራዎች ሁሉ የተሻለ ነገር ማምጣት ይገባል። እንግዳ መቀበል ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በየሄዱበት ቦታ በራስ ስሜት እንዲያገለግሉ ማድረግም ያስፈልጋል “። ብለዋል።
ፐብሊክ ርሌሽን ኤንድ ስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ አቶ ወንድም ተክሉ እንዳሉት ፤ የተሰጠው አደራ እጅግ ሰፊና ጥልቅ ሥራን የሚጠይቅ ነው። በተለይ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ አገርን ወደ ፊት ከማራመድ አንጻር የአላማ ጽናት ምን ያህል እንደሚያስፈልግ ያስረዳል። በዚህም የሰው ዘር መገኛ፤ ትልቅ ነበርንና ትልቅ እንሆናለን የምንል እኛ ኢትዮጵያዉያን የእርስ በእርስ መበላላትና የዘር መከፋፈል ያሳንሰናል። ስለሆነም መገኛነታችንን ልናጸና ያስፈልጋል እንጂ ለማንም መጠቀሚያ ልንሆን አይገባም ብለዋል።
ሌላዋ ተመራቂ ዶክተር እመቤት በቀለ እንደምትለው፤ ማህበረሰባችን የተማረን ሰው ያከብራል። ትልቅ ቦታና ተሰሚነትንም ይሰጣል። በመሆኑም እኛም መገኘት ያለብን ማህበረሰቡ እንደሰጠን ክብር ነው። የተነገረ ነገር ሁሉ እውነት ነው ከማለት በፊት ነገሮችን መርምሮ ማየትና ለአገር በሚጠቅም መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል። ነገር ግን ከዚህ የተለየ ተግባር የምንፈጽም ከሆነ ካልተማረው አንሻልምና እንደተማረ ሰው ልናስብ ይገባል ብላለች። መከፋፈል ጉልበት ያሳጣል የምትለው ዶክተር እመቤት፤ በተለይ አሁን ተመርቆ ወደተለያየ ቦታ የሚሄደው ተመራቂ በአንድነት ላይ ሊሰራ ይገባል።
የፖለቲካል ሳይንስና ኢንተርናሽናል ሪሌሽን የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂው ዳዊት አብርሃም በበኩሉ፤ በሁሉም ዘርፍ ሥራ ላይ የሚሰማራው አካል የተማረ በመሆኑ ለአገሩ የሚሰራና አሳቢ መሆን እንዳለበት ይናገራል። ሁሉም ሰው በዘር ከመከፋፈል ወጥቶ በሃሳብ ልዕልና የሚያምን መሆን አለበት።
ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ካውንስል እና የዑለማ ኃላፊ ለተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር እድሪስ እና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለአቶ ተወልደ ገብረማርያም የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 7/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው