አዲስ አበባ፡- የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን የሌላቸው እና እድሳት ያላደረጉ በአንድ ወር ውስጥ የመድን ሽፋን እንዲኖራቸውና እንዲያድሱ ጥሪ ቀረበ።
የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፣ የተሽከርካሪ ባለቤቶች ከሐምሌ 10 እስከ ነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ድረሰ ባለው አንድ ወር ውስጥ የመድን ሽፋን ምዝገባ ማካሄድ አለባቸው።በተሰጠው ቀን ውስጥ ምዝገባ በማያደርጉ የተሽከርካሪ ባለቤቶች ላይ ከነሐሴ ወር መጨረሻ ጀምሮ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል።
የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ እንደገለጹት፣ በተሰጠው አንድ ወር ውስጥ የተሽከርካሪ ባለቤቶች የመድን ሽፋን ምዝገባ እንዲያደርጉ ከፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ይሰራል።በተሰጠው አንድ ወር ውስጥ የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ለሚያደርጉ የተሽከርካሪ ባለቤቶች ከዚህ በፊት የነበረው የምዝገባ መስፈርት እንደሚቀርላቸውም ተናግረዋል። መስፈርቱ የሚቀረው ለተሰጠው አንድ ወር ብቻ ሲሆን፤ ይህም መስፈርቱን በመፍራት ምዝገባውን የሚሸሹ ባለቤቶችን ለማበረታታት ነው ተብሏል።
የምዝገባ መስፈርቱ ከባድ እንዳልነበር የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ከዚህ በፊት፤ ምን እንደሰሩ፣ ምን ያህል ጊዜ እንደሰሩ የሚጠየቋቸውን መስፈርቶች እና ወረፋ መጠበቅን እንደ መሰናክል በማየት ምዝገባውን ይሸሹት እንደነበር ተናግረዋል።
በተሰጠው ቀን ውስጥ ምዝገባ በማያደርጉ የተሽከርካሪ ባለቤቶች ላይ ከሦስት ሺህ እስከ አምስት ሺህ የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ወይም የሁለት ዓመት እስራት እንደሚቀጡ የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ የመድን ሽፋን የሌላቸው ተሽከርካሪዎች በፍተሻ እንደሚለዩ ተናግረዋል።የመድን ሽፋን የራሱ ምሥጢራዊ ምልክት ያለው ስቲከር ሲሆን ፎርጅድ ያሰራ የተሽከርካሪ ባለቤት ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበታል።የተሰጠው ቀን ከመጠናቀቁ በፊትም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይሰራሉ።
የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የተሽከርካሪ አደጋ ለደረሰባቸው ወገኖች እስከ ሁለት ሺህ ብር የሀኪም ወጪ የሚሸፍን ሲሆን አዋጁን በማሻሻል መጠኑ እንዲጨምር ይደረጋል ብለዋል፡ አዋጁ ሲሻሻል እስከ 40 ሺህ ብር ይከፈል የነበረው የተጎጂ ካሳ መጠኑ ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች ያሉ ሲሆን የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ያላቸው 569 ሺ ብቻ ናቸው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
ዋለልኝ አየለ