አዲስ አበባ፡- በ2011 ዓ.ም በሀገርና ክልል ደረጃ የተቀመጠውን የችግኝ ተከላ ግብ ለማሳካት በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሃምሌ 22 ቀን 50 ሚሊዮን ችግኝ እንደሚተከል ተገለጸ። 667 ሚሊዮን 181 ሺ 450 ችግኞችን ለመትከል ተዘጋጅቷል።
የግብርና ሚኒስቴር የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ መና ጠቅሶ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፣ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለተያዘው የአራት ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ግብ ለማሳካት በግለሰብ ዓርባ ችግኝ የሚተከል ሲሆን ለችግኞቹ ተገቢውን እንክብካቤ ለማድረግ ግለሰቦቹ የራሳቸውን ድርሻ በአግባቡ እንዲወጡ ይደረጋል።
በክልሉ በመንግሥትና በተለያዩ ተቋማት በተቋቋሙ ሰባት ሺ ችግኝ ጣቢያዎች ለበልግና መኸር ተከላ የሚሆን 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለማዘጋጀት ታቅዶ 667 ሚሊዮን 181ሺ 450 ችግኝ መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።
እንደ ሃገር ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ለሚካሄደው የ200 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ፕሮግራም 50 ሚሊዮን ችግኝ በከተማና በገጠር ለመትከል የታቀደ ሲሆን፣በ17 ዞኖችና በአራት ወረዳዎች እንደሚተገበር መግለጫው አመልክቷል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ችግኞቹ የሚተከሉት የተራቆቱ ቦታዎችን በመለየት ነው። ለቦታው ተስማሚ የሆኑ ችግኞች ተለይተው እንደየአካባቢው የአየር ሁኔታ የሚስማማው የዛፍ አይነት እንዲተከል ይደረጋል።
በክልሉ ውስጥ ከንባታ፣ ሲዳማ፣ ጉራጌ፣ ጋሞ፣ ወላይታ እና ስልጤ ጥሩ አፈጻጸም ያሳዩ ተብለው ተለይተዋል። በስልጤ ዞን ሁልባረግ ወረዳ በዚህ ዓመት ብቻ 125ሺ ችግኞች በ25 ሄክታር ቦታ የተተከሉ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት በእንስሳት ግጦሽና በተለያየ ምክንያት ተራቁተው በነበሩ አካባቢዎች 50ሺ ችግኞች መተከላቸው መግለጫው አስታውሷል። በሲዳማ ዞን ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ በአራት ሄክታር ላይ 20 ሺ ችግኞች ተተክለዋል ብሏል።
እንደ ክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ መረጃ የተተከሉ ችግኞች ከሰውና እንስሳት ንኪኪ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይሰራል። ያልጸደቁ ችግኞችን የመተካትና የኩትኳቶ ሥራም በተከታታይነት ይሰራል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር
ፎቶ፡- ፋይል