አዲስ አበባ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎችና ለልማት ተነሺዎች ለማስተላለፍ ያወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2008 አንቀጽ 44/ሐ/ እና /ሠ/ የህገመንግሥቱን አንቀጽ 40 ድንጋጌዎች የሚቃረን መሆኑ ተገለጸ፡፡
የህገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ጉባዔው በዚህ ሳምንት ባደረገው ስብሰባ የመመሪያ አንቀጽ 44/ሐ/ እና /ሠ/ ህገ መንግሥቱን የሚቃረን መሆኑን በማጣራት የውሳኔ ሃሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲላክ ወስኗል፡፡
በመመሪያው አንቀጽ 44 የቤት እድለኛ በሞተ ግዜ እድሜያቸው 18 ዓመት የሞላቸው የሟች ልጆች በሟች ስም የወጣውን እጣ አይወርሱም በሚል የደነገገ ሲሆን፣ይህ ደግሞ በሟች ወራሾች መካከል ልዩነት በመፍጠር ቤት የሌላቸው ግለሰቦች በውርስ መልክ የሚያገኙትን የቤት ባለቤትነት መብት የሚሸራርፍ በመሆኑ ጉባዔው በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 ስር የተደነገገውን የዜጎች የንብረት መብት የሚያጣብብና ከሌሎችም የህገ መንግሥቱ መርሆች ጋር የሚጋጭ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ስለሆነም የህገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት ለመጨረሻ ውሳኔ ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መላኩን መግለጫው አስታውቋል፡፡
ጉዳዩ ወደ አጣሪ ጉባዔው ሊቀርብ የቻለው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 160818 ሰኔ 28ቀን 2010 ዓ.ም በአንድ አመልካችና በተጠሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኤጀንሲ መካከል ሲካሄድ ከነበረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ጋር በተያያዘ ክርክር የመመሪያውን አንቀጽ 44 ህገ መንግሥታዊነት እንዲመረመር በመላኩ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር
ፎቶ፡- ፋይል