አዲስ አበባ፡- አዲስ የተቋቋመው የአዲስ አበባ የመብራት አገልግሎት አስተዳደር በመዲናዋ የሚገኙ የመንገድ ዳር መብራቶች እንደሚያስተዳድር ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለሥልጣን እና በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን መካከል ይፋዊ የሥራ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት በትናንትናው እለት ተካሂዷል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ እንደገለፁት፤ የመንገድ ዳር መብራቶች የአንድ ከተማ ዘመናዊነትና የሥልጣኔ ምልክት ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ አዲስ የተቋቋመው የአዲስ አበባ የመብራት አገልግሎት አስተዳደር የመንገድ ዳር መብራቶችን የሚያዘመንና ተደራሽ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
አዲሱ ተቋም ቀደም ሲል ጨለማ የነበሩ አካባቢዎችን በመቀየር ደኅንነቱ የተረጋገጠ እና ምቹ እንቅሰቃሴ ያለባት ከተማ በማድረግ ከተማዋን የብልፅግና ምልክት ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሙዲን ረሻድ (ኢ/ር) በበኩላቸው፤ የከተማው መንገዶች ባለሥልጣን በርካታ የመንገድ ግንባታና ልማት ብሎም የመንገድ ዳር መብራቶችን በማካተት የማስተዳደር ሥራ ሲሠራ የነበረ ተቋም ነው።
የከተማውን እድገት እና የኮሪደር ልማት መከናወንን ተከትሎ የመንገድ ዳር መብራቶችን እራሱን ችሎ እንዲሠራ ለማስቻልም የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ለማቋቋም ተችሏል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም ከተማዋን ለነዋሪዎች የምትስማማ፣ ዘመናዊና ሀያ አራት ሰዓት እንቅስቃሴ ያለባት ከተማ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰብስቤ ሁሴን፤ ተቋሙ የመንገድ ዳር መብራቶችን ተደራሽና ዘመናዊ በማድረግ የከተማዋን ነዋሪዎች ከመንገድ ዳር መብራት ጋር የተገናኙ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያስችላል ብለዋል።
ተቋሙ 26 ዋና ዋና ተግባራትን በማካተት የሚሠራ ሲሆን በዋነኝነትም የከተማዋን የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታ፣ ጥገናና ጥበቃ ሥራ እንደሚሠራ ጠቅሰው፤ በከተማዋን የመንገድ ዳር መብራቶች በማዘመንና ተደራሽ በማድረግ የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኅብረተሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ዘመናዊ የመንገድ መብራቶችን በሁሉም አካባቢ ተደራሽ በማድረግ ከተማዋን የማስዋብ፣ ከነዋሪዎች ከቀን እንቅስቃሴ በተጨማሪ በማታ ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ማሕሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም