አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር በሚገኘው ዩኔስኮ የዓለም የቅርስ ኮሚቴ አፍሪካን በመወከል እንድትሳተፍ በአፍሪካ ህብረት አባል አገራት በእጩነት መመረጧንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ይህም የአገሪቱን ቅርሶች ከስጋት ለመታደግ የሚያስችሉ ድጋፎችን እንድታገኝ የሚረዳት መሆኑን አመለከተ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ትናንት በኒጀር ኒያሚ የተካሄደው 35ኛውን የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ጠቃሚ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጤቶችን ያገኘችበት መሆኑን አስታውቀዋል። በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ ትምህርትና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) የዓለም የቅርስ ኮሚቴ አፍሪካን በመወከል ኢትዮጵያ መመረጧ ስጋት የተጋረጠባቸው ቅርሷቿን ለመታደግና ድጋፍ ለማግኘት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርላት መሆኑን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት የአፍሪካን መቀመጫ ለማግኘት የሚያስችላትን ውሳኔ በኅብረቱ ፀድቆ ወደ ፓሪስ መላኩን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በኮሚቴው መቀመጫዋን ማግኘቷ ከተረጋገጠ በተለይም በቱርካና ሃይቅ ጋር ተያይዞ የሚነሳባትን አሉታዊ እሳቤዎች በፊት ለፊት በመከራከርና በመደራደር ጥቅሟን ለማስጠበቅ ጥረት የምታደርግ መሆኑን አስ ገንዝብዋል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ምንም እንኳ የኅብረቱ ዋና ፅህፈት ቤት መቀመጫ አገር ብትሆንም እስካሁን በፅህፈት ቤቱ ቋሚ መቀመጫ የሌላት በመሆኑ የፅህፈት ቤቱን የአገልግሎት ጥያቄዎችና የትብብር ሁኔታዎችን በተሟላ ሁኔታ ለመመለስ ሳትችል መቅረቷን አመልክተዋል። ይሁንና በዚሁ የመሪዎቹ ጉባኤ ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ ውሳኔ በመተላለፉ የፅህፈት ቤቱን ጥያቄዎች በተሟላ ሁኔታ ከመመለስ ባሻገር የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች በላቀ ሁኔታ ለማስጠበቅ ሰፊ እድል የሚሰጣት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩልም በኒጀር በመሪዎች ደረጃ በተደረገው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ላይ በስኬት እንዲካሄድ ኢትዮጵያ የመሪነቱን ሚና መጫወቷን አምባሳደር ሂሩት አስታውሰዋል። ይህም አባል አገራቱ ወደ ስምምነት መድረሳቸው የቀደሙት የአህጉሪቱ መሪዎች ለነፃነታቸው ያደረጉትን ብርቱ ተጋድሎ በተጨባጭ ወደፊት ለማስኬድ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
የንግድ ቀጣናው እውን መሆኑ ከኢኮኖሚ ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ወደተሻለ ደረጃ ያሸጋግረዋል ብለዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ስምምነቱን መፈረሟ ለግሉ ዘርፍ ህልውና ስጋት አይሆንም ወይ ተብለው ተጠይቀው ከስጋት ይልቅ የገበያ እድላቸውን የሚያሰፋላቸው መሆኑንና ይህም የበለጠ እንዲያመርቱ እድል የሚፈጥርላቸው መሆኑን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
ማህሌት አብዱል