አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የተረከበው ኃላፊነት ከፍተኛ በመሆኑ ህዝብንና አገርን በሚመጥን መልኩ መምራት እንደሚጠበቅበት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ገለፁ።
የግንባሩ እህት ድርጅቶች አሁን ባላቸው አቋም ከቀጠሉ የኢትዮጵያ አብዛኛው ህዝብ ለአገሪቱ ህልውና ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆኑ በአገሪቱ ላይ የመፍረስ አደጋ እንደሚያጋጥም ሊታወቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የፓርቲዎቹ አመራሮች በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ህዝቡና የፖለቲካ ኃይሎች የአገሪቱን የለውጥ ጉዞ ማስቀጠል ላይ ቢሰራ አዋጭ ነው።አገሩንም ለውጡንም እመራለሁ ከሚል አካል በጥልቀቱም ሆነ በፍጥነቱ ተመሳሳይ እይታና አቅጣጫ ሊያዝ ይገባል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እንደተናገሩት፤ አገሪቱን እየመራ ያለ ድርጅት ኢህአዴግ ሲሆን፣መግለጫ የሰጡ ሁለቱ (ህወሓትና አዴፓ) ደግሞ የዚህ ግንባር አባል ድርጅቶች ናቸው።ከእነሱ የሚጠበቀው ህዝባዊና አገራዊ ኃላፊነታቸውም መወጣት ነው።የዚህን አይነት ኃላፊነት ይዘው ባልተገባ መንገድ ለመሄድ መሞከር አስፈላጊ አይደለም።ሲመረጡ ህዝብን ለማገልገል መሃላ ፈጽመው ነው።
የተጣለባቸውን ህዝባዊና አገራዊ ኃላፊነት አስቀድመው በራሳቸው በገዥው ፓርቲ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ተቀምጠው ቢነጋገሩና ቢደራደሩ መልካም መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር በየነ፤ የውስጥ ገመናቸውን በማውጣት ህዝብን በሚያሳስብ ደረጃ መግለፁ ተገቢ አለመሆኑን ገልፀዋል።
ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹አገሪቱን ለማረጋጋት ባለባቸው ኃላፊነት ከማንኛውም ግዜ በላይ በትከሻቸው ላይ በወደቀበት በዚህ ጊዜ ከእነርሱ የሚጠበቀው ትክክለኛ አካሄድን መከተል ነው።›› ሲሉ ጠቅሰው፣ የራሳቸውን የውስጥ ጉዳይ ለአሁኑ ወደጎን በመተው አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት ወደፊት መሄድ እንዳለባቸው አስረድተዋል።
እንደ ፕሮፌሰር በየነ ገለፃ፤አሁን ላይ እየተሰማ ያለው እሰጥ አገባ ነው።ይህን የውስጥ ችግራቸውን ማንም መስማት አይፈልግም።የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ እየታዘባቸው ነው።አገራዊ የሆነ ኃላፊነታቸውን እስከሚያወርዱ ድረስ የአገር ሁኔታ ለማረጋጋት ትልቅ ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋልና ትክክለኛውን አመራር መስጠት አለባቸው።
‹‹በአደባባይ ያወጡትንና ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያሰሙትን ጉዳይ በሰከነ አዕምሮና በጎለበተ አመለካከት ቁጭ ብለው ሊነጋገሩበትና ሊስማሙበት ይገባል።›› በማለት ያሳሰቡት ፕሮፌሰር በየነ፣ አገርና ህዝብ ችግር ላይ የሚጥል አካሄዳቸውን መተው እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል።‹‹አሁን እየሆነ ያለው አካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየነገሩን እና እያሳዩን ካለው እንዲሁም ከሚሉት ራዕይ ወጣ ያለ ነገር ነው ሲሉም ተናግረዋል። እርሳቸው እንዳብራሩት፤የኃላፊነታቸውን ደረጃ ጠንቅቀው ማየትና ተቀምጠውም መነጋገር ወደሚችሉበት አቅጣጫ መሸጋገር አለባቸው።የከሸፈም አሰራር ካለም እንደገና መመርመር ይጠበቅባቸዋል።
ፕሮፌሰሩ፣ ‹‹አሁን ባላቸው አቋም የሚቀጥሉ ከሆነ አገሪቱ ምንም የተለየ ነገር አይገጥማትም።ምክንያቱም አገሪቱ በችግሮች ውስጥ ማለፍ የለመደች ናት።ህዝቧም አብሮ በመኖር ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ያው ቃል። አገር ይፈርሳል አይቀጥልም የሚባለው ነገር ልክ አይደለም፤ እንዲያውም ያኮረፈው ወገን ይጎዳል እንጂ አገር ትቀጥላለች። ምክንያቱም የኢትዮጵያ አብዛኛው ህዝብ ለአገሪቱ ህልውና ግንባር ቀደም ተዋናይ ነውና።ሁሉም ቢሆን መጣፈጥ ያለበት ለራሱ ሲል ነው።ስለዚህም ሁሉም የሕዝብን አክብሮት ሊያስገኝለት ወደሚችል አካሄድ መግባት አለበት።››ብለዋል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና በበኩላቸው፤ዶክተር ዐብይ መቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያን ህዝብ ለለውጥ መምራት ሳይሆን የኢህአዴግ አባላትን መምራት የበለጠ ፈተና እንደሚሆንበት አስቀድመው መናገራቸውን አስታውሰው፣ አሁንም በግልፅ እየታየ ያለው ነገር ይኸው እንደሆነ ገልፀዋል።
ፕሮፌሰር መራራ እንደገለፁት፤ችግሩ ባለው ለውጥ ላይ እኩል የሆነ ፍጥነትና ጥልቀት ባለው መንገድ ተመሳሳይ እይታና አቅጣጫ መያዝ አለመቻሉ ነው።አዲሱ ነገር ቀደም ሲል ሲብላላ የነበረው ነገር በአሁኑ ሰዓት አደባባይ ላይ መውጣቱ ነው። ‹‹ተመሳሳይ እይታ አለመያዛቸው እንደ አገር የሚፈጥረው ችግር አለ።የዚህ ለውጥ አንዱና ትልቁ ፈተና ለውጡን ይመራል የሚባለው አካል በፍጥነቱም ሆነ በጥልቀቱ ላይ ተመሳሳይ እይታ መፍጠር አለመቻሉ ነው።››ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ወደ ብሄራዊ መግባባት መሄድ የሚያስችለውን መንገድ መከተል ያስፈልጋል።አገሩንም ለውጡንም እመራለሁ ከሚል አካል ተመሳሳይ እይታና አቅጣጫ ሊኖር ይገባል።ህዝብ የሚፈልገው ሰላምና አንድነትን እንዲሁም ለውጥን ነው።
ፕሮፌሰር መራራ፣‹‹አንዱ በሌላው ላይ ያውም በመንግሥት በጀት ሚሊሻና ልዩ ኃይል ሲያሰለጥን ነበር።››ሲሉ ተናግረው፤ዛሬ የእርሱ ድምር ውጤት ነው አደባባይ ላይ ማውጣት የቻለው››ብለዋል።ይህም አካሄድ ወደ ሌላ ቀውስ እንዳይመራ መጠንቀቅ እንደሚበጅ አሳስበዋል።
እንደ ፕሮፌሰር መራራ ገለፃ፤በሰከነ አዕምሮ እርምጃዎች የማይወሰዱ ከሆነ ውሎ አድሮ የሚያስከፍለው ዋጋ ወድ ይሆናል።መፍትሄው ዴሞክራሲያዊ ለውጥን ማምጣት ነው።ይህ ደግሞ የሚመጣው በመግባባትና በመነጋገር ሲሆን፣ ሌሎች አገሮችም እንዲህ አይነት ነገር ሲፈጠርባቸው ማለፍ የቻሉት መሰረታዊ በሆኑ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ የጋራ እይታና የጋራ አጀንዳ መፍጠር በመቻላቸው ነው።
‹‹ፖሊሲዎቻቸው የግድ አንድ መሆን አለባቸው ማለት ሳይሆን አገራችን ላይ ለውጡን እንዴት እንመራለን የሚለው ላይ ፍትሃዊ ጨዋታ ውስጥ ካልገባን ሁሉም የየራሱን የበላይነት አገኛለሁ የሚለው ገመድ ጉተታ ውስጥ ገብቶ መሄዱ አዋጭ አይደለም››ብለዋል። ህወሓትና አዴፓ እርስ በርስ የተካሰሱበትን መግለጫ ሰሞኑን ማውጣታቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
አስቴር ኤልያስ