የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ-በተደራሽነትና  በባለሙያ እጥረት ፈተና

በዓለም የመጀመሪያው የዓይን ባንክ አገልግሎት ከተቋቋመ 80 ዓመት እንደሞላው ይነገራል፡፡ የብሌን ንቅለ ተከላ በዓይን ሕክምና ተቋማት ከተጀመረ ግን ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ እንዳያስቆጠረ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የብሌን ንቅለ ተከላ መጀመረን ተከትሎ የተጀመረው የዓይን ባንክ አገልግሎት ከአሜሪካ ተነስቶ አውሮፓን አካሎ እስያ ደርሷል፡፡ ይሁንና በአህጉረ አፍሪካ ገና ጅምር ላይ ያለ አገልግሎት ነው፡፡ በአፍሪካ እንደ ኢትዮጵያውና ደቡብ አፍሪካው የዓይን ባንክ ከሃያ አንድ ዓመታት በላይ ቋሚ አገልግሎት በመስጠት የቀጠለ የዓይን ባንክ አገልግሎትም የለም፡፡

በኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ሲጀመር በባለሞያዎችም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ ስጋት ነበር፡፡ የብሌን ልገሳ ማግኘት ከባድ ይሆናል የሚል ግምትም ነበር፡፡ ይሁንና በሂደት ለውጦች እየታዩ በመምጣታቸው በርካታ ወገኖች በንቅለ ተከላ የዓይን ብርሃን ማግኘት ችለዋል። ከነዚህ ወገኖች ውስጥ አንዱ ወግአየሁ ፈጠነ ነው። ወግአየሁ ትውልዱና እድገቱ ሀረር ሲሆን የዓይን ብርሃኑን ያጣው ገና በሕፃንነቱ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የኩፍኝ በሽታ የዓይን ብሌን ጠባሳ አስከትሎበት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ወግአየሁ ልክ እንደ እድሜ አቻዎቹ እንደልቡ መንቀሳቀስ፣ መቧረቅ፣ መጫወትና ትምህርቱን በአግባቡ መከታተል አልቻለም፡፡

ይሁንና ልክ የዓይን ባንክ በ2000 ዓ.ም ሥራውን ሲጀምር አንደኛውን ዓይኑን የብሌን ንቅለ ተከላ በማድረግ የዓይን ብርሃኑ ተመለሰ፡፡ ትምህርቱንም መማር ጀመረ፡፡ ከስድስት ዓመት በኋላ ደግሞ ሁለተኛውን ዓይኑን የብሌን ንቅለ ተከላ በማድረግ ሁለቱም ዓይኖቹ ብርሃን አገኙ፡፡ በትምህርቱም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ቻለ፡፡ አሁን ላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ በማርኬቲንግና ማኔጅመንት የዲግሪ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል፡፡

ወግአየሁ የዓይን ብርሃኑ ሊመለስ የቻለው በጎ ፍቃደኞች ከህልፈት በኋላ በለገሱት የዓይን ብሌን ነው። እርሱም ይህ በጎ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ግንዛቤውን በማስፋት ሰዎች ከህልፈት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን እንዲለግሱና ለሌሎች ብርሃን እንዲሰጡ ለማስቻል የኢትዮጵያ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ የተሠራላቸውና በበጎ ፍቃደኞች የተሰኘ ማህበር በማቋቋምና ማህበሩን በመምራት ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ሰዎች ይህን ማህበር እንዲያግዙም ጥሪውን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ሲቋቋም ዋነኛ አላማው በዓይን ጠባሳ ምክንያት ማየት የተሳናቸው ዜጎች መልሰው ብርሃን እንዲያገኙ ለማስቻል ከህልፈት በኋላ ከለጋሽ ወገኖች ብሌን በማሰባሰብ ጥራቱንና ደህንነቱን ጠብቆ ለንቅለ ተከላ ሕክምና ማስራጨት ነው፡፡ ተቋሙ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም ድረስ ከ3ሺ በላይ ወገኖች በተለያዩ የሕክምና ማዕከላት የብሌን ንቅለ ተከላ ተደርጎላቸው የዓይን ብርሃን አግኝተዋል። ከ5 ሺ በላይ ወገኖች ደግሞ ከህልፈት በኋላ ብሌን ለመለገስ የቃል ኪዳን ሰነድ ፈርመዋል፡፡

የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ አገልግሎት እየሰጠ የቀጠለና እድገት እያሳየ የመጣ ቢሆንም አሁንም ያልተሻገራቸው ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ በጤና ሚኒስቴር በኩል በተደረገ ጥናት መሠረትም ከ300 ሺ በላይ የሚሆኑ የዓይን ብሌን ጠባሳ ዓይነ ስውራን ዜጎች አሉ፡፡ እነዚህ ዜጎች ብርሃን እንዲያገኙ ለማስቻል ብዙ መሥራት ይጠበቃል፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ ህብረተሰቡና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይህን የሕዝብ ዓይን ባንክ በተለያየ መልኩ መደገፍ ይኖርባቸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚናገሩት፣ ኅዳር ወርን በሀገር አቀፍ ደረጃ የዓይን ብሌን ልገሳ ወር በማድረግ ሰፊ የንቅናቄ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በዚህ የዓይን ብሌን ልገሳ ወር የተለያዩ ሥራዎች ይኖራሉ። ዋነኛው ሥራ ግን ህብረተሰቡ ስለ ዓይን ብሌን ልገሳ፣ የዓይን ብሌን ጠባሳና የሚያስከትላቸውን ማህበራዊ ችግሮች እንዲሁም ሕክምናውን ብሎም የዓይን ብሌን ልገሳ ሂደትን በማስረዳት ሰዎች የዓይን ብሌን ከህልፈተ ሕይወታቸው በፊት ቃል ገብተው እንዲለግሱ ለማበረታታት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዚሁ ኅዳር ወር የመክፈቻ ፕሮግራም በማዘጋጀት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በሚከናወን የአድቮኬሲና ንቅናቄ ሥራ ስለ ዓይን ባንክ ሰፊ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይከናወናል፡፡ በእለቱም የሞባይል ጽሑፍ መልእክት ለአጠቃላይ ማህበረሰቡ ይላካል፡፡ የማህበራዊ ሚዲያና የሚዲያ ዘመቻ በማካሄድ ስለ ዓይን ብሌን ልገሳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ይሰጣል። ከኃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎችና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አደረጃጀቶች ጋር የአድቮኬሲ ሁነት ይዘጋጃል፡፡

በተለያዩ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲ ብሎም ብዙ ሰዎች ባሉባቸው የትምህርት ተቋማት ቅስቀሳዎችን በማካሄድ የግንዛቤ ሥራና ቃል የማስገባት መርሃ ግብርም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይካሄዳል፡፡ በጎዳና ስፖርት መርሀ ግብር በማርሽ ባንድ የእግር ጉዞ በሚደረግ የቅስቀሳ ሥራ ግንዛቤ የማሳደግ ሥራም ይከናወናል፡፡ ከዓይን ሐኪሞችና ከማህበራት ጋር እንዲሁም ከተለያዩ የእድርና የሕዝብ አደረጃጀቶች ጋር የአድቮኬሲ ወርክሾፕ ይካሄዳል፡፡ የፓናል ውይይትም ይደረጋል፡፡

በወሩ መጨረሻ የመዝጊያ መርሀ ግብር የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ አገልግሎቱን ከማስፋት አንፃር ተጨማሪ የዓይን ባንክ በክልል ከተማ ለማስጀመር ሰፊ የንቅናቄ ሥራ ይሰራል፡፡ ዓይን ባንክን ለመክፈት ተግባራዊ እንቅስቃሴም ይጀመራል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት አጠቃላይ ዓይነ ሥውራን ዜጎች ውስጥ 20 ከመቶ የሚሆኑት የዓይን ብሌን ጠባሳ እንዳለባቸው ጥናት ያሳያል፡፡ በቁጥር ደግሞ ወደ 400 ሺ እንደሚጠጋ በቅርብ የተደረገ ጥናት ያመለክታል። በዚህ የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ የሃያ አንድ ዓመት ጉዞ ከ3 ሺ 500 በላይ የሚሆኑ ዜጎች የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ 15ሺ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ከህልፈት በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገብተዋል፡፡

የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ አገልግሎቱን ያገኙ ሰዎች በአብዛኛው በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ ከመቀሌ፣ ጎንደር፣ ሐዋሳና ጅማ ውጭ አገልግሎቱ በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ ያለ እንደመሆኑ መጠን የሕክምና አገልግሎቱን ያገኙ ዜጎች ቁጥር በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡ የተሰበሰበው የዓይን ብሌን መጠንም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ብዙ ሥራ መሥራት ይጠይቃል፡፡ በቀጣይ በክልሎች ውስጥ በዚህ ዓመት ቢያንስ አንድ ተጨማሪ የዓይን ብሌን ባንክ ለመክፈት እቅድ ተይዟል፡፡

አሁን ላይ የዓይን ብሌን የሚለግሰው የህብረተሰብ ቁጥር ዝቅተኛ ነው፡፡ ለዚህም አንዱና ዋነኛው ምክንያት የህብረተሰቡ ግንዛቤ አናሳ መሆኑ ነው፡፡ የዓይን ብሌን መለገስ ሊያመጡ የሚችሉትን ጉዳቶች ካለማወቅ አንፃር በህብረተሰቡ በኩል የተዛቡ አመለካከቶች አሉ፡፡ የዓይን ብሌን በአስክሬን ላይ ምንም ዓይነት መበላሸት፣ ቅርፅ ማሳጣትም ሆነ በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መስተጓጎል ሳይፈጥር በሃያ ደቂቃ ብቻ ትንሿን የዓይን ክፍል ብሌን መውሰድ መሆኑን በትክክል ካለመገንዘብም ጭምር ነው ህብረተሰቡ የዓይን ብሌኑን ከህልፈት በኋላ የማይለግሰው፡፡

በሌላ በኩል የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ የሚያደርጉ የሕክምና ባለሞያዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆንም ለአገልግሎቱ ውስንነት ሌላኛው ተግዳሮት ነው፡፡ አሁን ባለው መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ በዚህ የዓይን ንቅለ ተከላ ዘርፍ የሰለጠኑ ባለሞያዎች ቁጥር 12 ብቻ ነው። በነዚህ ባለሞያዎች ብቻ ይህን አገልግሎት ለበርካታ ሰዎች ተደራሽ ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለዚህ የሕክምና ባለሞያዎችን ቁጥር ከማሳደግ አንፃር ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠይቃል፡፡ በዚህ የሕክምና ዘርፍ የሰብ ስፔሻሊቲ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የትምህርት ዘርፉን ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ ወደ ክልል እንዲደርሱም የአገልግሎቱን ተደራሽነት ማስፋት ይገባል።

በዚህ ረገድ አገልግሎቱን ከማስፋት አኳያ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ብዙዎችን ከጨለማ ወደ ብርሃን ማምጣት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ሕክምና የሚፈልጉ ሰዎችን ተራ የማስያዝ፣ እንዲመዘገቡ የማድረግ ሥራ አልጀመረም። ይህን ሥራ ሲጀምር የሕክምና አገልግሎቱ ትክክለኛ አሠራር ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እስካሁን ግን ሆስፒታሎች በራሳቸው በሚያወጡት ተራ መሠረት የሕክምና አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በቀጣይ ግን ተቋሙ ይህን ሕክምና አገልግሎት የሚጠቀሙ ሰዎችን ዝርዝር ተራ በማስያዝ የዓይን ብሌን ሥርጭት አድርጎ አገልግሎቱን የሚያገኙበትን አሠራር የሚዘረጋ ይሆናል፡፡

ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓይን ብሌን ልገሳ ወር ‹‹ብርሃን አይቅበሩ፤ በብሌን ጠባሳ የተነሳ ዓይነ ስውር የሆኑ ወገኖችዎ ብርሃን እንዲያገኙ ምክንያት ይሁኑ!›› በሚል መሪ ቃል ከኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ ቅስቀሳና የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ሥራዎች ይከበራል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ የዓይን ሕክምና ባለሞያዎች ማህበር ጥቅምት 29 እና 30 2017 ዓ.ም 24ኛውን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን፣ በዚህ ጉባኤ ከ250 በላይ የሚሆኑ የዓይን ሐኪሞች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የጤና ማህበራት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ በዓይን ሕክምና ዙሪያም አዳዲስ ጥናትና ምርምሮች ቀርበዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት አጠቃላይ ዓይነ ሥውራን ዜጎች ውስጥ 20 ከመቶ የሚሆኑት የዓይን ብሌን ጠባሳ እንዳለባቸው ጥናት ያሳያል። በቁጥር ደግሞ ወደ 400 ሺ እንደሚጠጋ በቅርብ የተደረገ ጥናት ያመለክታል

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You