– ቡናውን በአገር ውስጥ ገበያ ለመሸጥ የመንግሥት ምላሽ እየተጠበቀ ነው
አዲስ አበባ፡- በቡና ገበያ ላይ በተፈጠሩ ተያያዥ ችግሮች እንዲሁም የዩኒዬኑ አመራሮችና አባላት በጌዲዮ ዞን ተከስቶ በነበረው ግጭት ተጠርጥረው በመታሰራቸው ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የ37 ሺ አርሶ አደሮች ሁለት ሺ ሜትሪክ ቶን ቡና በመጋዘን መቀመጡን የይርጋጨፌ ቡና ገበሬዎች የኅብረት ሥራ ዩኒዬን አስታወቀ።
የይርጋጨፌ ቡና ገበሬዎች የኅብረት ሥራ ዩኒዬን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዱአለም ሽፈራው በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በህገወጥ ነጋዴዎች እና በ2009 ዓ.ም በዩኒዬኑ አመራሮች ላይ በደረሰ እስር ምክንያት ከ37ሺ አርሶ አደሮች የተሰበሰበ ከ2ሺ ሜትሪክ ቶን ቡና ባለመሸጡ በመጋዘን ተከማችቷል። ቡናውን በአገር ውስጥ ገበያ ለመሸጥ ለመንግሥት ጥያቄ ቢቀርብም እስከአሁን ምላሽ አልተሰጠም።
እንደ አቶ አንዱአለም ገለጻ፤ በ2009 ዓ.ም በጌዴኦ አካባቢ የነበረውን አለመረጋጋት ተከትሎ እርሳቸውን ጨምሮ ዋና ሥራ አስኪያጁን እና በርካታ የዩኒዬኑን ሠራተኞች ተጠርጥረው ታስረው ነበር። ከዘጠኝ ወራት ተኩል በኋላም ያለምንም ክስ ቢለቀቁም በዩኒየኑ ኤክስፖርት ሥራ ላይ አሉታዊ ችግር ፈጥሯል። በእስሩ ወቅት ውል የተገባባቸው ቡናዎች ባለመላካቸው አሜሪካ እና የተለያዩ አገራት የሚገኙ ተረካቢዎች በዩኒዬኑ ላይ እምነት ስላጡ እስከአሁን ድረስ ተጨማሪ ቡና ለመግዛት ፈቃደኛ አልሆኑም። አሜሪካ፣ ጃፓን እና ጀርመን ድረስ በመሄድ ውይይት ቢደረግም አሁንም በአገሪቷ አለመረጋጋት እና የቡና አቅርቦት ላይ መተማመን ባለመቻላቸው ፊታቸውን ወደ ሌሎች አገራት አዙረዋል። በዚህ ምክንያት የአርሶአደሩ ቡና በመጋዘን ሊከማች ችሏል።
በሌላ በኩል ህገወጥ ነጋዴዎች እና ደላሎች የይርጋጨፌ ቡና ነው በሚል ለውጭ አገራት አንዱን ፓውንድ ቡና በሁለት ዶላር እና ከዚያም በታች የሚያቀርቡ መሆኑን አመልክተዋል። ዩኒዬኑ ደግሞ ጥራት ያለውን ትክክለኛውን አንድ ፓውንድ ቡና በአራት ዶላር የሚያቀርቡ መሆኑን ጠቅሰዋል። በመሆኑም ገዥዎች የደላሎቹን በመቀበል የዩኒዬኑ ምርቶች በመጋዘን እንዲቆዩ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።«ደላሎቹም ሆኑ ነጋዴዎቹ ዋነኛ ፍላጎታቸው ዶላሩን ለማግኘትና በቀጣይ ዓመት ወደ አስመጪነት መሸጋገር ስለሆነ የይርጋጨፌን ቡና ከዝቅተኛ ደረጃ ጋር በመቀላቀል ይሸጣሉ። ይህን ሁኔታ መንግሥት መቆጣጠር ካልቻለ በቀጣይ ዓመታት የዩኒዬኑ ምርቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የአገሪቷ ቡናዎች ገበያ ሊያጡበት የሚችልበት እድል አለ» ብለዋል።
በእነዚህ ምክንያቶች ገበያ በመቀነሱ ዩኒዬኑ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ አለመቻሉን ያስረዱት አቶ አንዱአለም ከዚህ ቀደም ግን መጋዘን ውስጥ ከፍተኛ የውጭ አገራት ግዥ ፍላጎት በመኖሩ ምርት የሚያልቅበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁንና ከእስሩ በኋላ እና ከህገወጥ ደላሎች ጋር በተያያዘ ግን ምርት ቢትረፈረፍም ገዥ አለመገኘቱን አስረድተዋል።
የዩኒዬኑ የእቅድና ፕሮጀክት ክፍል ኃላፊ አቶ አለኸኝ ጥባ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በ2007 ዓ.ም 2 ሚሊዮን 183 ሺ ኪሎ ግራም ቡና ተሸጦ 18 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል።ይሁንና ከዚያ በኋላ ባሉ ዓመታት ከፍተኛ አቅርቦት እያለ ገበያው ተቀዛቅዟል። በዘንድሮ ዓመት እስከ ሰኔ መጨረሻ የተሸጠው ደግሞ አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቡና ብቻ ነው።
በተከሰቱ ችግሮች ቡናው ባለመሸጡ ዩኒዬኑ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የባንክ ብድር ወለድ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ቡና አምራቹ ዜጋ ጥቅሞቹ እንዳይከበሩለት ያደረገ አጋጣሚ መፈጠሩን ተናግረዋል። በመሆኑም መንግሥት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ዩኒየኑን ገበያ እንዲያገኝ ከመደገፍ ባለፈ ህገወጥ ደላሎችን እንዲሁም ለአንድ ዓመት እና ሁለት ዓመት ብቻ ቡና በርካሽ ሸጠው ዶላር ለመሰብሰብ የሚፈልጉ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዩኒዬኑ በእራሱ ችግሩን ለመቀነስ ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ አለኸኝ፤ ቡናው ላይ እሴት ጨምሮ ለመሸጥ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ ቡና ቆልተው የሚፈጩ እና የሚያዘጋጁ ማሽኖች ተከላ መካሄዱን ጠቁመዋል። ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ትክክለኛውን የይርጋጨፌ ቡና ጣዕም የያዙ የተፈጩ ቡናዎች ለዓለም ገበያ ለማቅረብ አቅደዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
ጌትነት ተስፋማርያም