– በ2011 ዓ.ም 198 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል
– በ2012 ደግሞ 248 ነጥብ 3 ቢሊዮን ለመሰብሰብ አቅዷል
አዲስ አበባ፤- በ2011 ዓ.ም ከአገር ውስጥ ገቢ እና ከታክስ 198 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን እና በ2012 በጀት ዓመት 248 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ።
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ትናንትና በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ በተከናወኑ በርካታ የፈጣን አገልግሎት አሰራሮች ማሻሻያ እና በታክስ ንቅናቄ ስራዎች በ2011 በጀት ዓመት 198 ነጥብ አ1ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል። ይህም ከ2010 በጀት ጋር ሲነጻጻር የ22 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው። ይሁንና ገቢው የተወካዮች ምክር ቤት ካስቀመጠው ዕቅድ በ14ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከሚኒስቴሩ ዕቅድ በ42 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ያነሰ ነው።
እንደ ወይዘሮ አዳነች ገለጻ፤ በአገሪቷ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት እና የኮንትሮባንድ ዝውውር ዋነኛ የግብር አሰባሰብ ተግዳሮቶች ነበሩ። የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለበርካታ አስመጪዎች የሥራ እንቅስቃሴ መዳከም በመፍጠሩ በታክስ ገቢ መቀነስ ላይ አስተዋጽኦ ነበረው። ይሁንና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባከናወናቸው የታክስ ንቅናቄ፣ የአሠራር ግልጽነት መፍጠር እና የህግ ክፍተቶችን የማስተካከል ሥራ የግብር አሰባሰቡ ካለፈው ዓመት ገቢ በ22 ቢሊዮን ብር እንዲበልጥ አድርጓል።
«የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን» ያሉት ወይዘሮ አዳነች፣የተጀመሩ ለውጦችን መሰረት በማድረግ በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካስቀመጠው 224 ቢሊዮን ብር ዕቅድ በማስበለጥ 248 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማቀዱን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ከሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ 40 በመቶዎቹ በኢ-መደበኛ ንግድ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ጠቅሰው፣ ከነጋዴዎቹ ጋር ውይይት በመደረጉ አብዛኛዎቹ ወደ መደበኛ የንግድ አሠራር እንደሚመለሱ ተስፋ መጣሉን ገልጸዋል። ወደ መደበኛ ሲመጡም የ2011 ግብር አሰባሰብ ከፍተኛ እንዲሆን እንደሚረዳ አስረድተዋል። በዋናነት ደግሞ የተቋሙን አጠቃላይ ሠራተኛ በማነቃቃት፣ ህገወጥነትን በመከላከል እና አሠራርን ቀልጣፋ በማድረግ እንዲሁም የህግ ማሻሻያዎችን በማድረግ የግብር አሰባሰቡ ከፍተኛ እንዲሆን ጥረት እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል።
በሌላ በኩል ወይዘሮ አዳነች እንደገለጹት፤ በቀጣይ ሳምንታት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያጸድቀው የሚጠበቀው አዲስ የንግድ ህግ ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ ምርቶች ላይ ማዕከላዊ አሰራር እንዲኖር ያደርጋል። በአሁኑ ወቅት 35 ተቋማት ከቀረጥ ነፃ የመፍቀድ መብት ያላቸው በመሆኑ ቁጥጥር ሳይደረግ ትልቅ
ዝርፊያ ሲፈጸምበት ቆይቷል። በመሆኑም ህጉ ሲጸድቅ ለእያንዳንዱ ግንባታ እና የነጻ ቀረጥ ጥያቄ የጊዜ እና የመጠን ገደብ ያለው ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረጋል። እንደ ገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ በግብር አከፋፈል ላይ ታማኝነት ላሳዩ እና ከፍተኛ ግብር ከፋይ ለሆኑ ተቋማት እና ግለሰቦች ሰሞኑን ግብዣ ለማድረግ ዝግጅት እያካሄደ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
ጌትነት ተስፋማርያም