አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ ካሉ አንድ ሚሊዮን ኢንተርፕራይዞች ውስጥ በፌዴሬሽኑ አባል ሆነው የተመዘገቡት አራት ሺ ኢንተርፕራይዞች ብቻ በመሆናቸው እንደሚያሳስበው የኢትዮጵያ ጥቃቅንና አነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አሰሪዎች ፌዴሬሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ጥቃቅንና አነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ኃይሌ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንዳብራሩት፤ እንደ አገር በ2008 ዓ.ም በአገሪቱ 780ሺ ኢንተርፕራይዞች የነበሩ ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢንተርፕራይዞች ይገኛሉ።ሆኖም በፌዴሬሽኑ አባል ሆነው የተመዘገቡት 4000 ኢንተርፕራይዞች ብቻ መሆናቸው ያሳስበናል፤ በቂ አይደሉም ብለዋል።
አቶ ጌታቸው እንዳሉት፤ ቀደም ሲል በአገሪቱ የጥቃቅና አነስተኛውን የሚወክል ምንም ዓይነት ማህበር አልነበረም።በአብዛኛው ተደራጅተው የነበረው በንግድ ምክር ቤት፣ በዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሥር ነበር።ሃሳባቸውን የሚያንሸራሽሩት፣ ፍላጎትና መብታቸውን ሲጠይቁ የነበረው በዚሁ አደረጃጀት ነበር።ይሁንና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የሚይዘው አምራቾችን ነው።ፌዴሬሽኑ ሲመሰረት ግን አምራቾችንና አገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማሩትን በማካተት ነው።በዚህም መሰረት ጥያቄ በተደራጀ መንገድ ለመጠየቅ፣ ማምረቻ ቦታዎችን ለማግኘት፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና መሰል ችግሮችን በጋራ ለመጠየቅ ብሎም በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ የሚኖራቸውን አዎንታዊ ሚና ለማሳደግ ታስቦ የተቋቋመ መሆኑንም አብራርተዋል።
በ2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ በማህበር ደረጃ ተመዝግቦ የነበረው ይህ አደረጃጀት ክልሎችንና ኢንተርፕራይዞችን በማካተት በ2009 ዓ.ም ወደ ፌዴሬሽን አድጓል።በ2009 ዓ.ም 1000 ኢንተርፕራይዞች፣ በ2010 ዓ.ም 2000 ኢንተርፕራይዞች በ2011 ዓ.ም ደግሞ 4000 ኢንተርፕራይዞች የፌዴሬሽኑ አባል ሆነው ተመዝግበዋል።ይሁንና በአገሪቱ ካሉ ኢንተርፕራይዞች አኳያ የፌዴሬሽኑ አባላትን በማብዛት ረገድም ሰፊ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ፤ የኢትዮጵያ ጥቃቅንና አነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አሰሪዎች ፌዴሬሽን በአሁኑ ወቅት 4000 አባላት ያሉት ሲሆን፤ በቀጣይ ቁጥሩን ለማሳደግ የተለያዩ ስልቶችን መቀየሱን ተናግረዋል።ለአብነትም ቀደም ሲል ለመመዝገቢያ ሲባል ይከፈል የነበረው ሦስት ሺህ ብር ክፍያ እንዲቀር ተደርጓል።በአሁኑ ወቅት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ ለዓመታዊ መዋጮ 2000ሺ ብር ብቻ ነው።የፌዴሬሽኑ አባል ለመሆን ኢንተርፕራይዞች በቀጥታ መመዝገብ አሊያም ደግሞ በክልል ደረጃ በሚገኙ ማህበራት ተመዝግቦ በፌዴሬሽን ሊካተት እንደሚችልም ገልፀዋል።ከዚህም ሌላ በቀጣይ የፌዴሬሽን አሠራር ለማዘመን ብሎም አዳዲስ አሰራሮችን እንደሚከተል ጠቁመዋል።
ፌዴሬሽን ዕድገት ዘርፍ የሚባሉ እንደ ልብስ ስፌት፣ ብረታ ብረት ምርት፣ ኮንስትራክሽንና የባልትና ውጤቶችን ያካተተ መሆኑን አብራርተው፣በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ዕድገትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፣ መንግስትም ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።
ፌዴሬሽኑ በርካታ ጥረቶቸን እያደረገ ቢሆንም ችግሮች እንዳሉበት ጠቁመዋል።በተለይም ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ያደጉ ኢንተርፕራይዞች ሼድ እንዲያስረክቡ እየተደረገ በመሆኑ የመስሪያ ቦታ አጥተዋል።የመሰረተ ልማት አለመሟላትም ሌላኛው ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል።የውጭ ምንዛሪ እጥረትም ለኢንተርፕራይዞች ራስ ምታት መሆኑን አቶ ጌታቸው አብራርተዋል።ሆኖም ችግሩን ለማቃለል በአዲስ አበባ መስተዳድር የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማሉ ጀንበሩ በበኩላቸው፤ የመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ጉዳይ እንደማይመለከታቸው ጠቁመው።ይሁንና 10 እና 15 ዓመታት ሼዶችን ይዘው የቆዩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለዓመታት ሀብት ስላፈሩ ለተተኪው ወጣች እንዲለቁ መወሰኑን ጠቁመዋል።ችግሮች ካሉም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በውይይት እንደሚቃለል አረጋግጠዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር