አዲስ አበባ፡- ለወሎ ጋቢ የአካባቢ የወል ንግድ ምልክትና እውቅና መስጠቱን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።በወላይታ አካባቢ የሚገኙ የተለያዩ ምርቶች እውቅና ለመስጠት ጥናት እየተደረገ ሲሆን፤ የደሴ ሳፋ ደግሞ ለእውቅና ተቃርቧል።
በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የአዕምሯዊ ንብረት ዕሴት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ወርቁ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ጽሕፈት ቤቱ በሚቀርቡ ጥያቄዎች እና አሳማኝ የጥናት ውጤቶች ላይ በመመስረት እውቅና እየሰጠ ነው።በአሁኑ ወቅትም በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።በዚህ መሠረት የወሎ ጋቢ እውቅና የተሰጠው ሲሆን፤ የደሴ ሳፋ እውቅና እንዲሰጠው ጥረት መጀመሩን አብራርተዋል።በተመሳሳይ መልኩ በወላይታ አካባቢ ሰፊ አቅምና ዘርፈ ብዙ ምርቶችና እሴቶች በመኖራቸው እውቅና ለመስጠት የውይይት መድረክ ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።ምርቶቹ እውቅና ለመስጠት የሚያስችሉ በርካታ ጥናቶች መኖራቸውንና የወሎ ጋቢ እውቅና ለማግኘትም ጥልቅ ጥናት መካሄዱን አብራርተዋል።.
እንደ አቶ ታደሰ ገለፃ፤ ቀደም ሲል የጅሩ በሬ፣ የአረርቲ ሽንብራ፣ የመንዝ በግ፣ የደብረሲና ቆሎ፣ የአንጎለላ ጠራ (ጫጫ) ወተት እና የምንጃር ጤፍ በአካባቢ የህብረት ሥራ ዩኒየኖች ጥያቄ ጥናት ላይ ተመስርቶ የወል የንግድ እውቅና እንደተሰጣቸው አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።የሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ማህበራትና ዩኒየኖች በስፋት በመንቀሳቀሳቸውና የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አቀፍ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶና ጥናትና ምርምር በማካሄዱ እውቅና ለማግኘት ችለዋል።የምርቶቹ እውቅና ማግኘትም በአገር ውስጥ ሆነ ዓለም አቀፍ ገበያ ሰብሮ ለመግባትም መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ አንዳንድ ምርቶች የወል የንግድ ምልክት ቢያገኙም በተፈለገው መጠን ገበያ ላይ መገኘት እና ስማቸውን ይዞ ለመቆየት ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል።ለአብነትም የጅሩ በሬ እውቅና ቢሰጠውም የአካባቢው ነዋሪዎች በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ አድልበው ስለሚሸጡ በተፈለገው ሰዓት ገበያ ላይ አይገኙም።መሰል ችግሮች ደግሞ ምርቶቹ እንዳይታወቁ ከማድረግ ባሻገር በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የተሰጣቸው እውቅና ላይፀና የሚችልበት ዕድል መኖሩን አብራርተዋል።
አቶ ታደሰ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ለመሰል ምርቶች እውቅና ከመስጠት በተጨማሪ በርካታ ተግባራት እንዳለ ጠቁመው፣ ለዚህም የምርምር ተቋማትና እሴቱ ይመዝገብልኝ የሚሉት አካላት በጥልቅ ጥናት፣ መረጃ እና ማስረጃ ላይ መመስረት እንዳለባቸው አስረድተዋል።እነዚህ ሂደቶች ከተሟሉ እውቅናውን ከመሰጠቱ በፊት በጋዜጣ የሚታወጅ ሲሆን፤ የሚቃወም አካል እስከሌለ ድረስ ከሦስት እስከ አራት ወራት እውቅና ይሰጠዋል ብለዋል።ለመሰል ምርቶች እውቅና ከመስጠት በተጨማሪ የመልክዓ ምድር አቀማመጥና ሌሎች እሴቶች እውቅና እንደሚሰጥ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2003 የተመሠረተ ሲሆን፤ ለአዕምራዊ ንብረት እውቅና መስጠት፣ ለአዕምሯዊ ንብረት በአገር ውስጥ በቂ የሕግ ጥበቃ የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸትና በፓተንት ሰነዶች የታቀፉ የቴክኖሎጂ መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ ማደራጀት፣ ማሰራጨትና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማበረታታት የሚሉ ዋነኛ ዓላማዎችን አንግቦ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር