የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት፤ የ2025 የአፍሪካ የግብርና ልማት ፕሮግራም ረሃብን ለማጥፋት ብርቱ የሆነ ዓላማን ያነገበ ቢሆንም አፍሪካ ግን ከእቅዱ አኳያ ብዙ የሚቀራት ጉዳይ እንዳለ ያመላክታሉ። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያንም ሆነ ለተቀሩት የዓለም ሀገራት ምሳሌ ሊሆን የሚችል የግብርና ልማት ማሳየቷን ይገልጻሉ።
አፍሪካ 60 በመቶ የሚሆን የዓለም ምርታማ መሬት ይዛ መራብ እንደሌለባት የሚገልጹት ሊቀመንበሩ፤ ሆኖም በአሁኑ ወቅት 230 ሚሊዮን አፍሪካውያን የምግብ ዋስትናቸውን አለማረጋገጣቸውን ይጠቁማሉ። በአፍሪካ ኅብረት የተዘጋጀው የተቀናጀ የግብርና ልማት ፕሮግራም በሚፈለገው ልክ ለውጥ አለማምጣቱን አንስተው፤ ይህ ለአሕጉሪቱ አስጨናቂ ጉዳይ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
በዚህ ረገድ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የልማት አጋሮችን እና ሌሎች ቁልፍ ባለ ድርሻ አካላትን ማሳተፍ እንደሚገባ፤ የቴክኒክና የገንዘብ ሀብት እንደሚያስፈልግ ተናግረው፤ ለዚህ ደግሞ ስትራቴጂያዊ እና የድርጊት መርሐ ግብር በመተግበር የምግብ ሥርዓት ለውጥ ማምጣት ለነገ የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ።
የአፍሪካን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ጥራት ያለው የግብርና ሥራ በመተግበር ምርታማነትን ማስፋፋት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ በተለይም ኢትዮጵያ እየተገበረች ላለው ሞዴል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ሥራዎችም ለሁሉም ተሞክሮ እንደሚሆን አስታውቀዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከረሃብ ነፃ ዓለምን ለመፍጠር የበኩሏን ሚና እየተወጣች ትገኛለች። ለአብነትም ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ችላለች። ባለፉት 50 ዓመታት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ታስገባ የነበረውን የስንዴ ምርት ከማስቀረት አልፋ፤ ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች።
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ብቻ ከ230 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ማምረት ችላለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ባለፉት ዓመታት 40 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ለግብርናው ዓለም አቀፍ ፈተና የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመከላከል በግብርናው ላይ ምርታማነትን ማሳደግ ችላለች ሲሉ ገልጸዋል።
ረሃብን ለመከላከል በርካታ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች መኖራቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በዋናነት የምርጥ ዘር አቅርቦት አለመኖር፣ የግብርና ግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ ግጭት የመሬት መንሸራተት፣ ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋ፣ የአንበጣ ወረርሽኝ፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦት አለመኖር ዋና ዋናዎች መሆናቸውን አንስተዋል።
ይህም ከረሀብ ነፃ ዓለምን ለመፍጠር የሚደረገውን ትግል አክብዶት እንደነበር ጠቅሰው፤ ይሁንና ኢትዮጵያ ችግሮችን ተከላክሎ ረሃብን ማስወገድ የሚያስችል አቅም መፍጠር መቻሏን አብራርተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በግብርና ምርታማነት ላይ ስትራቴጂካዊ ለውጥ በማምጣት ሰፋፊ ድሎችን ያስመዘገበች ሲሆን፤ በተለይም የሚታረስ መሬትን በእጥፍ በመጨመር ምርታማነትን ማሻሻል ከተገኙ ውጤቶች እንዱ ነው ብለዋል። ይህም በስንዴ፣ በጤፍ፣ በቆሎ እና ገብስ ምርቶች ላይ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ሲሉ አስረድተዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 40 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸው የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለመጨመር ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከት እንደቻለ ተናግረዋል።
የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ዳይሬክተር ጄኔራል ገርድ ሙለር እንደሚሉት፤ ረሃብ የዓለም የጋራ ችግር ነው። ይሁንና የጋራ እውቀትን፣ ልምድንና፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በመጠቀም ከረሃብ ነፃ ዓለምን መፍጠር ይቻላል።
አፍሪካ የዓለማችን ባለፀጋ አሕጉር ናት፤ ይሁንና በአሕጉሩ የሚስተዋሉ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ከረሃብ ነፃ ዓለምን ለመፍጠር ትልቅ ፈተና ደቅነዋል ሲሉ ያብራራሉ። ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በምግብ ምርታማነት ላይ ያስመዘገበችው ስኬት ከረሃብ ነፃ አሕጉር መፍጠር እንደሚቻል ከአፍሪካ አልፎ ለዓለም ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ ነውም ብለዋል።
አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብት ብዙኃነት ያለባት አሕጉር ብትሆንም አሁንም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አልቻለችም ያሉት ሙሳ ፋኪ በበኩላቸው፤ ረሃብን ከአፍሪካ የማጥፋት ጉዳይም በሁሉም ዘንድ ትኩረት የሚሠጠው መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ኢትዮጵያ የወሰደቸውን ርምጃ በማድነቅ፤ ሀገሪቷ እየሳየች ያለው ዓለም አቀፍ ተልዕኮን የመወጣት ብቃት አስመልክቶ የገርድ ሙለርን ተመሳሳይ ሀሳብ ተጋርተዋል።
በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚቀመጡ የውሳኔ ሀሳቦችን በቁርጠኝነት የመተግበር ክፍተት መሆኑን በመግለጽ፤ አፍሪካን ከረሃብ ነፃ ለማድረግ የሚቀመጡ ውሳኔዎችን ሀገራት በቁርጠኝነት ሊተገብሩት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
ረሃብን ከአፍሪካ ምድር ማጥፋት የአሕጉሪቱ የምንግዜም ስትራቴጂክ ዕቅድ እንደሆነ በማንሳት፣ ይህንን ዓላማ ማሳካትና በአዲስ መንፈስ መሥራት ከሁሉም የሚጠበቅ ሚና መሆኑን ይናገራሉ።
በቀጣይ አካታች በሆነ መንገድ ሥራ ፈጠራን ማበረታታት፤ የንግድ እሴት ሠንሠለትን መፍጠር፤ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ፤ ቀጣይነት ያለው ምርታማነትን መጨመር፣ ግብርናን በፋይናንስ መደገፍ፣ የምግብ ሥርዓት አስተዳደርን ማጠናከርና ሌሎችም መሰል ዒላማዎች ከረሃብ ነፃ ዓለምን ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ ያላቸው መሆቸውን ሊቀመንበሩ አንስተዋል።
አፍሪካ በተፈጥሮ ሃብቶች የበለፀገች በመሆኗ ያላትን እምቅ ሃብት በአግባቡ በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ትችላለች ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከረሃብ ነፃ ዓለም ለመፍጠር በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ዘዴዎችን መከተል እንደሚገባ ይመክራሉ። በተለይ ዘመናዊ የግብርና ግብዓቶችን መጠቀም፣ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል፣ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ፣ ድርቅን የሚከላከሉ ሰብሎችን መዝራት፣ ግጭትን ማስቆምና መሠረት ልማትን ማስፋፋት ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ምግብ ወደ ሀገር ከማስገባት ወደ ውጭ ወደ መላክ ተሸጋግራለች። ይህ በሁሉም አፍሪካ ሀገር እውን መሆን ይችላል። “ለዚህ ኢትዮጵያ ማሳያዋ ናት” በማለትም ኢትዮጵያ በምግብ ምርታማነት ላይ ላስመዘገበችው ለውጥ አድናቆታቸውን ይገልጻሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ አፍሪካ ካላት የተፈጥሮ ሀብት አንጻር ረሃብን ማስቆም ትችላለች። አፍሪካ ለግብርና የሚውል ሰፊ የሚታረሰ መሬት አላት። በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከድህነት ወደ እድገት ጎዳና እየመጡ ነው፣ የኢትዮጵያም አንዷ ማሳያ ናት።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ከረሃብ ነፃ ዓለምን ለመፍጠር በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ብቻ 50 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ ያስፈልጋል።
በአዲሱ ገረመው እና ሞገስ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅት 27/207 ዓ.ም