ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ኢትዮጵያ የምድረ ቀደምት መገኛ” የሚል ስያሜ የተሰጠውን ግዙፉ የመንገደኞች አውሮፕላን ኤ350-1000 ትናንትና በአዲስ አበባ ተረክቧል። አውሮፕላኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በተደረገ መርሐ-ግብር ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ እንደተናገሩት፤ የአየር መንገዱን የመሪነት ሚና የሚያስቀጥል እና ሀገሪቱን የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ማዕከል የሚያደርጉ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡

ግዙፉ ኤ350-1000 አውሮፕላን ወደኢትዮጵያ መግባቱ የአየር መንገዱን ስም ይበልጥ ከፍ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ  እድገት ከሚያበረክተው አስተዋፅዖ ባለፈ፤ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ሀብት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ እንዲሁም ከሀገራት ጋር ያለውን የኢኮኖሚ  እና የንግድ ትስስር ለማጠናከር በርካታ ሥራዎች ታቅደው እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓመት ከ100 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው አዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ ልማትን ጨምሮ በርካታ መሠረተ ልማቶች ላይ ኢንቨስት እየተደረገ መሆኑን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ የተረከበው አውሮፕላን ከኤርባስ ኩባንያ የተገዛ ነው። አየር መንገዱ ካዘዛቸው አራት አውሮፕላኖች መካከል አንዱ መግባቱን ገልጸው፤ ቀሪዎቹ በየወሩ እንደሚመጡ አስታውቀዋል።

ኤ350-1000 አውሮፕላን ነዳጅ ቆጣቢ መሆኑ፣ የኤሌክትሪክ ሥርዓቱ፣ ባሉት የመቀመጫ ወንበር ብዛት፣ በመንገደኞች መገልገያ ቁሳቁሶች፣ በመንገደኞች የመዝናኛ አማራጮች እጅግ ዘመናዊና ያደርገዋል ብለዋል።

የአውሮፕላኑ ወደ ገበያ መግባት የአየር መንገዱን የመሪነት ሚና ለማስቀጠል እንዲሁም ስምና ዝናውን ይበልጥ ለማጉላት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመዳረሻ እና በአውሮፕላን ብዛት፣ አዳዲስ አውሮፕላኖችን በማስመጣት ከአፍሪካ አየር መንገዶች መንገደኞች ቀዳሚ መሆኑን ተናግረዋል።

አየር መንገዱ የመሪነት ሚናውን ለማስቀጠልና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ከ120 በላይ አውሮፕላኖችን ለማስመጣት መታዘዙን እና በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደሀገር ውስጥ እንደሚገቡ አመላክተዋል።

በተጨማሪም አዳዲስ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ለማስፋፋት እየተሠራ ሲሆን፤ ይህም የመንገደኞችን ቁጥር እና ገቢው እንዲያድግ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን  ጥቅት 27/207 ዓ.ም

Recommended For You