ብዙ የተባለለት እና የተነገረለት፤ ብዙዎችን ለከፋ ስቃይ የሚዳርገው ሕገወጥ ፍልሰት ዛሬም ድረስ ብዙዎችን ለመከራ እያጋለጠ ይገኛል። ዛሬም ኢትዮጵያ ስሟ ከሕገወጥ ስደት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ይገኛል። ለመሆኑ በመንግሥት በኩል ይህን ዜጎችን ለመከራ የሚዳርግና የሀገርን ገጽታ የሚያጠለሽ ተግባር ለማስቆም ምን እየተሠራ ይገኛል? ስንል በፍትህ ሚኒስቴር ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ አብርሃም አያሌው ጋር ቆይታ አድርገን የሚከተለውን አዘጋጅተናል።
አዲስ ዘመን፡– እንደ ሀገር ሕገወጥ ስደትን በተመለከተ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ እንዴት ይታያል?
አቶ አብርሃም፡– ስደት ሰፊ ነገር እና አጠቃለይ የሰዎች እንቅስቃሴን የሚይዝ ሲሆን፤ የሕዝብ ብዛትን ከሚወስኑ ውልደትና ሞት በመቀጠል በሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው። ይህም ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገራችን ከቃላት አጠቃቀም ጀምሮ የሰዎች እንቅስቃሴን በተመለከተ ትክክል ያልሆኑ መረዳቶች አሉ። ምንአልባትም ይህ ሊከሰት የቻለው በመገናኛ ብዙኃንና በሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሰራቱ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በመድረክ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እየተባለ የሚነገረው በሕግ አግባብ በዓለም አቀፍ ደረጃም ባሉትም ሆነ በኢትዮጵያ ሕግ የሚገለጸው በሰው የመነገድ ወይም ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎች በመባል ነው።
በሰው መነገድ የሚባለው በእንግሊዝኛው አጠራር «ሂውማን ትራፊኪንግ» የሚባለው ሲሆን፤ ሰውን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ደግሞ «ማይግራንት ስማግሊንግ» የሚባለው ነው። ይሄ በአጠቃለይ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ይባላል። ሕገወጥ ፍልሰት የሚባለው በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ቃሉ ተቀይሮ «ኢ ሬጉላር ማይግሬሽን» ተብሏል። ይህ የተባለበት ዋነኛው ምክንያት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን የሚከተሉ አብዛኛዎቹ ሰዎች ተጎጂዎች በመሆናቸው ነው። ነገር ግን ይሄ ሕገ ወጥ ፍልሰት ከተባለ በየደረሱበት ሀገር ወይም በመተላለፊያ ሀገራት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው በወንጀል ተጠያቂ መሆንን እንዲሁም መገለልን ያመጣል በሚል ነው።
መደበኛ ያልሆነ ማለት ከመነሻ ሀገራት ጀምሮ በመተላለፊያና በመዳረሻ ሀገራት ያሉትን ሕጋዊ መንገዶች በመጠቀም ያልሄዱ ማለት ነው። በአንጻሩ መደበኛ ፍልሰት የሚባለው በመነሻ ሀገር የተቀመጡ ሕጎችን ደንቦችና መስፈርቶችን አሟልተው የሚንቀሳቀሱና በመተላለፊያ ሀገራትና በመዳረሻ ሀገራትም የሚጠበቅባቸውን አሟልተው የሚንቀሳቀሱ የሚዘዋወሩ ማለት ነው።
በሌላው ደግሞ አስገዳጅ ፍልሰት «ፎርስድ ማይግሬንሽ» የሚባለው ነው። ይህ ሰዎች ከሚኖሩበት ቀዬ በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም እንደ ጎርፍ መሬት መንሸራተት፣ ድርቅ ባሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ወይም ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭትን ተከትሎ በሚፈጠር የሰላም እጦት ካሉበት አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ማለት ነው። ይህም ስደት «ሪፊውጂ» የሚባለው ነው።
ፍልሰት አጠቃላይ ሰፊውን ማሕቀፍ የሚይዝ ሲሆን፤ የግዳጅ ስደት በዚህ ውስጥ አንድ ክፍል ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገራቸው የመከሰስ፣ የመገደል እጣ ፈንታ የሚጠብቃቸው ወይም የሰላም እጦቱ ባልተቀረፈበት ሁኔታ መመለስ ሳይችሉ ሲቀሩ ባሉበት ሀገር ጥገኝነት ጠያቂዎች ይባላሉ።
በተመሳሳይ በሀገር ውስጥ በተፈጥሯዊም በሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች ተፈናቃዮችም በዚሁ ማሕቀፍ ውስጥ የሚካተቱ ይሆናል። በዚህም መሰረት መደበኛ ያልሆነ ፍልስት፤ መደበኛ ፍልሰት እና የግዳጅ ፍልሰት የሚታይባቸው የሕግ ማሕቀፎች የተለያዩና ራሳቸውን የቻሉ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– በኢትዮጵያ ያለው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት እንዴት ይታያል ?
አቶ አብርሃም፡– ምንም እንኳን ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት ፣ መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ውስጥ የሚካተት ቢሆንም፤ ወንጀሎች ተብለው የተጠቀሱት ግን በሰው የመነገድ ወይንም ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር እና ለሥራ ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጪ መላክን ያካትታል። ለሥራ ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጪ መላክ በግለሰብም ደረጃ ሆነ ድርጅት አቋቁሞ ወዳልተፈቀደለት ሀገር መላክ፤ ፈቃድ ሳይኖር መላክንም ያካትታል። ይህንን መነሻ አድርገን ወደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ስንመለስ ኢትዮጵያ የስደተኞች መነሻ፤ መተላለፊያና መዳረሻ ሀገር ናት። መዳረሻ በሚለው ከተለያዩ እንደ ሱዳን፤ ሱማሊያ፤ ኤርትራ ካሉ ከሃያ ስድስት በላይ ሀገራት የመጡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች በመሆኑ ነው።
የመዳረሻነት ታሪክ ሲነሳ ኢትዮጵያ ከሰባተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረ የእንግዳ ተቀባይነት ታሪክ አላት። ለዚህ ነብዩ መሀመድ አዝዘዋቸው ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ባሏቸው መሰረት እዚህ መጥተው የነበሩት እንግዶች የነበራቸው ቆይታ በታሪክ የሚታወስ ነው። እንደ መተላለፊያ ደግሞ ሀገሪቱ የምትገኝበት ቦታ የፍልሰት መተላለፊያ ለመሆን ያስገደዳት ሲሆን፤ በዚህም ረገድ በተለይ ኤርትራውያን እና ሶማሊያውያን ይጠቀሳሉ።
በአሁኑ ወቅት ግን ዋናው ጉዳይ ሀገሪቷ በሁለት መልኩ የስደተኛ መነሻ የመሆኗ ነው። የመጀመሪያው መደበኛ ፍልሰት ሲሆን፤ ይህም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ዜጎቿ ወደ ውጪ ሀገራት በሚሄዱበት ጊዜ ካሉበት ቦታ ከመነሻቸው ጀምሮ ስልጠና ወስደው፤ በሕጋዊ ድርጅቶች ተመልምለው ሥራና ክህሎት ሚኒስትርም አውቆት የሚካሄደው ነው። እነዚህ ስደተኞች በዚህ ሁኔታ ሀገራቸውን ለቀው ወደ መዳረሻ ሀገራት ቢሄዱበትም ጊዜ ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የሥራ ስምምነት ወደፈረመችባቸው ሀገራት ነው።
በዚህ አይነት በ2015 ዓ.ም ከአንድ መቶ ስድስት ሺህ በላይ ዜጎች፤ በተመሳሳይ 2016 ዓ.ም ከሶስት መቶ አርባ አምስት ሺህ በላይ ዜጎች ደህንነታቸው፤ መብታቸውና ክብራቸው ብሎም ጥቅማቸው ወደሚጠበቅበት ሀገራት ለመጓዝ በቅተዋል። ይህ ማለት እነዚህ ዜጎች የት ሀገር እንዳሉ የት ቤት እንዳሉ የተፈጸመው ውል ዝርዝር ሁሉ ይታወቃል ማለት ነው። እነዚህን ሰዎች በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የሚሄዱበት ሀገር መንግሥትም በተመሳሰይ ሁሉንም መረጃ ይይዛል። በዚህ መሰረት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየሀገራቱ ባሉ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች አማካይነት የዜጎቹን መብት በተመለከተ ክትትል ያደርጋል።
ሁለተኛው እንደ ሀገር በርካታ መስዋእትነት እያስከፈለ ያለው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ነው። በዚህ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ሊባል በሚያስችል ደረጃ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው የተሻለ ኑሮን የሚያስቡ ናቸው። እነዚህም እንደ ሀገር በዋናነት በሶስት መስመሮች (ድንበሮች) ማለትም በምሥራቅ፤ በደቡብና በሰሜን ምዕራብ የሚወጡ ናቸው። እነዚህ ፍልሰተኞች ካሉበት ቀዬ ተነስተው ወደ ወረዳዎች ሲወጡ ከዛም በየደረጃው ወደ ዞንና ክልል ከተሞች አልፎም አዲስ አበባ ወይም በሚወጡበት ቦታ እስኪደርሱ የሚንቀሳቀሱበት መስመር በሙሉ ሕጋዊ ያልሆነ ነው። በዚህ ሂደትም ተሳታፊ የሚሆኑ በርካታ መልማዮች፤ ደላሎች፤ አዘዋዋሪዎች ድንበር አሻጋሪዎች፤ ተቀባዮች ከዛ ደግሞ በዝባዦች እጅ ለመውደቅ ይገደዳሉ። በዚህም በየዓመቱ በግልጽ የተቀመጠ ዳታ ባይኖርም በየወቅቱ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በኢ መደበኛ መንገድ ከሀገር ይወጣሉ።
የደቡብ በር ተጓዦች ከመካከለኛው ኢትዮጵያ ክልል ከሲዳማ ከኦሮሚያ በደላሎች አማካይነት ደቡብ አፍሪካን መዳረሻቸው አድርገው በኬንያ ማላዊ ታንዛንያ አቋርጠው የሚጓዙ ናቸው። በምሥራቅ ጅቡቲን አቋርጠው ባህር ተሻግረው የመንን አልፈው ሳውዲ አረብያና ሌሎች ሀገራትን መዳረሻቸው አድርገው የሚሄዱ ናቸው። በመተማ አሁን በጦርነቱ ምክንያት ቢቋረጥም ሱዳንን እና ሊቢያን አቋርጠው ሜዲትራንያንን ተሻግረው አውሮፓን መዳረሻቸው አድርገው የሚጓዙ ናቸው። ሶስቱ በሮች አብዛኛው ሕገወጥ ስደት የሚፈጸምባቸውና ሕገወጥ አንቀሳቃሾችም በስፋት የሚጠቀሙባቸው በመሆኑ እንጂ ሌሎች ያልተለዩ መውጫ መንገዶችም አሉ። እነዚህ ስደተኞች ከቀዬአቻው ጀምሮ በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በሙሉ ለመብት ጥሰት ብሎም ለተለያዩ ችግሮችና እና ለሞት ይዳረጋሉ።
በመንግሥት በኩል ይህን አስከፊ ችግር ለመቅረፍ እንደ አቅጣጫ የተቀመጠው በአንድ በኩል መደበኛ የፍልሰት መንገዶችን ማስፋፋት ከሙስና ማጽዳት፤ ተደራሽ ማድረግ፤ ኤጀንሲዎችን ማጠናከር ሲሆን፤ በሌላ በኩል በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱትን ለመግታት መሥራት ነው። ምክንያቱም ፍልሰት የማይቆም በመሆኑ አማራጭ መሆን ያለበት በመደበኛነት እንዲጓዙ በማድረግ የፈለጉት ሀገር ሄደው በመሥራት ለራሳቸው ለቤተሰባቸውና በውጪ ምንዛሪ ለሀገር የሚገኘውን ጥቅም ለማረጋገጥ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ ኢ–መደበኛ ፍልሰትን ለመከላከል ምን ምን ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች?
አቶ አብርሃም፡– ኢመደበኛ ፍልሰትን ለመከላከል በቅድሚያ አጠቃላይ አደረጃጀት፣ ሕግ እና አሰራር ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ በተለይም በሊቢያ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ከታረዱ በኋላ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ወንጀለኞችን ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ አዋጆችን አውጥቷል። በተጨማሪ የውጪ ሀገር ስምሪትን ለመምራትም ራሱን የቻለ አዋጅ ፀድቋል። ረቂቅ የፍልሰት ፖሊሲም የተዘጋጀ ሲሆን፤ አደረጃጀትን በተመለከተም በቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ ክልሎችንም ያሳተፈ ምክር ቤት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቋቁሟል። ሀገሪቷ ፌዴራል አደረጃጀት የምትከተል እንደመሆኗ ፍትህ ሚኒስቴር የሚመራው የሚመለከታቸው ተቋማትን የሚያካትት ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት የሚል በአዋጅም ተቋቁሟል።
በክልሎችም በተመሳሰይ ክልላዊ የትብብር ጥምረቶች በመቋቋም ላይ ይገኛሉ። ይህ ሊደረግ የቻለው መደበኛ የሆነውን ፍልሰት ማጠናከርና ኢ-መደበኛ የሆነውን የመቆጣጠር ሥራ በአንድ ተቋም ብቻ ውጤታማ መሆን ስለማይችል ነው። በዚህም ሁሉም የሚመለከታቸው ተቋማት በጋራ እንዲያቅዱ በጋራ እንዲሰሩና በጋራ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያስችል እድል ተፈጥሯል። ለምሳሌ መደበኛ ፍልሰትን ውጤታማ ለማድረግ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አምስት መቶ ሺህ ዜጎችን እልካለሁ ብሎ ቢያቅድ ኢምግሬሽን ይህንን አውቆ የፓስፖርት ዝግጅት ካላደረገ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በተመሳሳይ ዝግጅት ካላደረገ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም አውቆ በየሀገራቱ ያሉ ኤምባሲዎችም በዚሁ ልክ የዜጎችን መብት ለማስከበርና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ዝግጅት ካላደረጉ ውጤታማ መሆን አይቻልም።
በተመሳሳይ መደበኛ ያልሆነውን ፍልሰትንና እሱን ተከትለው የሚከሰቱ ወንጀሎችን ለመከላከል ድንበር አካባቢ ያሉ የፌዴራልም ሆነ የክልል ፖሊሶች የሚሰሩት ሥራ አለ። በዚህ ጊዜ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ሲያውሉ ወንጀለኞች ተብለው የተለዩትን ወደ ሕግ ለማቅረብ ተጎጂዎችን ደግሞ ወደጊዜያዊ ማቆያ ከዛም ወደየቤተሰቦቻቸው ለመመለስ የሚደረገው ጥረት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ትብብርና ቅንጅት የሚፈልግ በመሆኑ ነው።
በአሁኑ ወቅትም በስድስት ተቋማት የሚመራ ስድስት የሥራ ቡድኖች አሉ፤ የሚያስተባብረውም ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት ነው። ከእነዚህም አንደኛው ወንጀል መከላከልና ሕግ ማስከበር ነው። ይህ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሚመራ ሲሆን፤ ደህንነት፣ ኢምግሬሽን እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ያካተተ ነው። ሌላው የውጪ ሀገራት የሥራ ስምሪት በሥራና ክህሎት ይመራል። ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ የሚመራው ደግሞ የተጎጂዎች እና የተመላሾች መብት ጥበቃን እና ወደነበሩበት መመለስን ያካትታል። በትምህርት ሚኒስቴር የሚመራው ደግሞ የምርምር ሥራዎችን የተመለከተ ሥራ ያከናውናል። የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የሚመራው ዳታን የተመለከቱ ጉዳዮችን ይሆናል። ዳያስፖራን ጉዳይ በተመለከተ የዳያስፖራ አገልግሎት የሚመራውም አለ።
አዲስ ዘመን፡– እነዚህ ከላይ የተዘረ ዘሩት አካላት በሚሰሯቸው ሥራዎች የሚጠ በቀውን ውጤት አስመዝግበዋል ማለት ይቻላል?
አቶ አብርሃም ፡- እንደ አጠቃላይ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ለማለት የሚያስደፍሩ ሥራዎች ተከናውነዋል። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት በሕጋዊ መንገድ የተላኩት ሶስት መቶ አርባ አምስት ሺህ ዜጎች አደረጃጀት ተፈጥሮ ሕጎች ወጥተው በተቋማት ቅንጅት በመሰራቱ የተገኘ ውጤት ነው። እነዚህን ዜጎች በሕጋዊ መንገድ መላክ ባይቻል ኖሮ ኢ-መደበኛውን መንገድ በመጠቀም ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸው የማይቀር ነበር። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የውጭ ምንዛሪ ገቢም «ረሚታንስ» በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል። በዚህም ዘንድሮ ብቻ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል።
በሌላ በኩል ወንጀል በመከላከልም ረገድ በጣም አበረታችና ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል። እዚህ ላይ ግንዛቤ ሊያዝ የሚገባው በኢ-መደበኛ የሰዎች ዝውውር ውስጥ የሚሳተፉ አካላት የሚሰሯቸው ወንጀሎች እጅግ የተወሳሰቡና ረዥም ሰንሰለት ያላቸው ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ በርቀት ከምትገኝ አንዲት የገጠር ቀበሌ ወይም መንደር እስከ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎችም መዳረሻዎች የተዘረጋ ነው። መስኩ እንደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ከጦር መሳሪያና ከአደንዛዥ እጽ ቀጥሎ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር ያለበትም ነው። አጠቃላይ በሰዎች መነገድ በዓመት ከአንድ መቶ ሃምሳ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበትም ነው። ይህን ጠንካራ እና ብዙ ቦታዎችን የሚያካትት ሰንሰለት ለመበጣጠስ የተጠናከረና የተቀናጀ ኃይልም ሥራም የሚያስፈልግ ይሆናል። ይህንንም መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች በተወሰነ ደረጃ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል።
በዚህ ረገድ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ይህንን ወንጀል ለመከላከል ብቻ ራሱን የቻለ ባለሙያዎችን ያካተተ ክፍል አቋቁሟል። አቃቤ ሕግም ይህንን ወንጀል ለመመርመር ለመከታተልና ወንጀለኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂ ለማድረግ ራሱን የቻለ አደረጃጀት አቋቁሟል። በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ለዚህ አገልግሎት የሚውል ራሱን የቻለ ችሎት ተቋቁሟል። በዚህም እስከ ናይሮቢና ታንዛንያ ድረስ መስመራቸውን የዘረጉ ከደቡብ የሀገሪቱ ክፍል በሰዎች የሚነግዱ፤ ሰዎችን የሚበዘብዙና ኩላሊት እያወጡ የሚሸጡ ትልልቅ ወንጀለኞች ባለፈው ዓመት በቁጥጥር ስር ውለው ቅጣት ተላልፎባቸዋል። ይህም ሆኖ ወንጀለኞቹ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ በመሆኑ ከሌሎች ሀገራት ጋር በጥምረት መሥራትም የግድ የሚል ይሆናል።
በዚህም ረገድ ባለፈው ዓመት ከጅቡቲ ጋር የጋራ የወንጀል ምርመራ ቡድን ለማቋቋም የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ተችሏል። በዚህም በኢትዮጵያ በኩል ከየክልሉ ጀምሮ ያሉ ወንጀለኞችን ድሬዳዋና ጋላፊ ድረስ የመለየት ሥራ የሚሠራ ይሆናል። በጅቡቲ በኩልም ያሉትን በመለየት የጋራ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ የመረጃና የማስረጃ ልውውጥ ይደረጋል፤ በጋራ ተልእኮ የመፈጸም ሥራም የሚከናወን ይሆናል። ከኬንያ ጋርም ሁለት ጊዜ ንግግሮች ተደርገዋል። ከኬንያ የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ውይይት ተጀምሯል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ እ.አ.አ በ2022 ሃያ ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን በማላዊ ጫካ ውስጥ ታርደው ተገኝተው ነበር። እነሱን በተመለከተ የሀገሪቱ መንግሥት ወንጀል የፈጸሙትን ግለሰቦች ለሕግ ለማቅረብ እየሠራ ይገኛል። ነገር ግን አሁንም ድረስ በርካታ ዜጎች በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ አሉ፡፡ ለእዚህም ከማላዊ ጋር የሁለትዮሽ ንግግር ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። ይህ አጋጣሚ በማላዊ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሀገራት እየተከሰተ ያለ በመሆኑ ዜጎች ባሉባቸው የመተላለፊያና የመዳረሻ ሀገራት ጋር የሚደረገው ውይይት የሚቀጥል ይሆናል። በቅርቡም ከጅቡቲ ጀምሮ እስከ ሳውዲ አረቢያ ያሉ ሀገራትን የሚያካትት በሚኒስትሮች ደረጃ የሚደረግ ውይይት ይኖራል።
ዜጎች ከሀገራቸው ወጥተው የሚሄዱት ሌላ ሀገር ለመውረር ወይም ስጋት ለመሆን አይደለም። አሁን ላሉበት ነገርም የሚዳረጉት በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ነው። ይህንን በተመለከተ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራት የፈረሙት ስምምነት አለ። ስምምነቱ ሀገራት ወደነሱ የገቡ ፍልሰተኞችን እንደ ወንጀለኛ ሳይሆን እንደ ተጎጂ አይተው ጥበቃ እንዲያደርጉላቸው ነው። እዛ ባሉበት ወቅትም በእስር ቤት ሳይሆን በተለየ ማቆያ አቆይተው ከሀገራቸው መንግሥት ጋር በመነጋገር እንዲመልሷቸው የሚል ነው። ይህ እውን እንዲሆን እየተሠራ ይገኛል። በተጨማሪ እንደ ፍትህ ሚኒስቴር ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት በሕግ ጉዳዮች በትብብር ለመስራት ከኬንያና ከደቡብ አፍሪካ ጋር ስምምነት ተጀምሯል። እንደ ሳውዲ ካሉ ከተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለመመለስ የተከናወኑ ተግባራትም ውጤታማ ነበሩ።
አዲስ ዘመን፡– ችግሩን ለመፍታት ከሌሎች አካላት ጋር በትብብር የመሥራት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል ?
አቶ አብርሃም፡– በትብብር ከመሥራት አኳያ በቅድሚያ መታወቅ ያለበት ወንጀለኞቹ ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እስከ ደቡብ አፍሪካ፤ ሳውዲ አረቢያ፤ ጣሊያንና ሌሎች ሀገራትም የተዘረጋ ጠንካራ መስመር ያላቸው ናቸው። ይህም በመሆኑ ከእነሱ በተሻለ የተጠናከረ አቅምና ቅንጅት መፍጠር ካልተቻለ ዜጎች መደበኛ ላልሆነ ፍልሰት መጋለጣቸው አይቀርም። በመሆኑም ተቋማት በር ዘግተው ከመሥራት ወጥተው ቅንጅት መፍጠር የሚጠበቅባቸው ይሆናል። ሕግ አስከባሪ አካላት የድንበር ቁጥጥር ላይ፤ ድህነት ቅነሳና ሰላም ማስጠበቅ ላይ መሥራት የሚጠበቅ ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕዝቡ በቂ እውቀትና መረጃ እንዲኖረው የግንዛቤ ፈጠራ ትኩረት የሚፈልግ ሥራ ነው። ይህንንም መሰረት በማድረግ በየዓመቱ እንደ ሬዲዮ ቴሌቪዥንና ጋዜጣ ያሉ መደበኛ የሕዝብ መገናኛ መንገዶችን እና ሌሎችንም በመጠቀም በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የሀገራዊ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ስለነበሩ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር የሕዝብ ንቅናቄ ሥራዎች እንዲከናወኑ አድርገዋል።
በአሁኑ ወቅት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመሰጠቱም ሕጎች እየወጡ ይገኛል። ለመጀመሪያ ጊዜም እንደ ሀገር የስደት ፖሊሲ ረቂቅ ተዘጋጅቷል። በሀገሪቱ እስካሁን ድረስ ሽብርን ሌብነትን ሙስናን እና ሌሎችንም ለመከላከል የሚያስችል ሀገራዊ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ አለ። ነገር ግን እነዚህ ወንጀሎች በሀገር ላይ እያመጡ ያሉት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ በሰው የመነገድና ሰውን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ራሱን የቻለ ረቂቅ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ አምና ተጠኗቋል። ይህን እንዴት እንከላከል? እንዴት ግንዛቤ እንፍጠር? እንዴትስ ጣልቃ መግባት ይቻላል? የሚለውን ሁሉ ያካተተ ነው። ከዚህም ባለፈ በየወቅቱ ለሕግ አስከባሪ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ይሰጣል። ስልጠናውም ምርመራ እንዴት ይደረጋል? ተጎጂዎችን ከተጠርጣሪዎች እንዴት መለየት ይቻላል? በሚሉትና ሌሎች ቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ሕጉንም የሚጨምር ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላው ትልቁ አጀንዳ የሀገር ውስጥ የሥራ እድሎችን ማስፋፋት ነው። የሀገር ውስጥ የሥራ እድል እየተስፋፋ ሲመጣ ከሀገር ለሥራ ብለው የሚሰደዱ ዜጎችን ቁጥር መቀነስ ይቻላል። በተጨማሪ ከስደት ተመላሾችን በሀገር ውስጥ በሚፈጠረው የሥራ እድል ቦታ በመስጠት ተመልሰው እንዳይሄዱ ማድረግ ያስችላል። እነዚህ ሥራዎች በተለያዩ ማሕቀፎች በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። በ2014 ዓ.ም አዋጅ ቁጥር 1263 ሲወጣ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተፈጠረበት ዋናው ምክንያት ይኸው ነው። ነገር ግን እየደረሰ ካለው ችግር አኳያ አሁንም ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ።
አዲስ ዘመን፡– ወንጀለኞቸ ሲያዙ የሚወሰድ የቅጣት እርምጃ ምን ያህል ውጤታማ ሆኗል ማለት ይቻላል ?
አቶ አብርሃም ፡– አዋጅ ቁጥር 1178 / 2012 ዓ.ም በዚህ ወንጀል የተገኘን እስከ ሞት የሚያደርስ ቅጣት ሊተላለፍበት እንደሚችል አስቀምጧል። ነገር ግን ዋናዎቹ ወንጀል አድራጊዎች ሲታሰሩና ሲቀጡ አይታይም። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኪዳኔ የሚባል ከሊቢያ ጀምሮ የራሱ እስር ቤት የነበረው፤ የራሱ ታጣቂ ቡድን የነበረው ከኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች የሚሄዱን በሊቢያ በረሃ እየዘረፈ አካል እያጎደለ ገንዘብ የሚሰበስብ ነበር። እሱና ግብረ አበሮቹ ኤርትራውያን ጭምር ተይዘው እሱም በሀገራችን ፍርድ ቤቶች ተፈርዶበት ተላልፎ ተሰጥቶቷል። አምናም ናይሮቢ ሆነው መስመር ዘርግተው የሚሰሩ ከአስር በላይ ግለሰቦች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደርጓል። ይህም ሆኖ ከወንጀሉ ስፋት አኳያ በተለይም ዋናዎቹን ወንጀለኞች ተጠያቂ የማድረጉ ነገር ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ አብርሃም ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም